እኩልነት በፍትሐዊ ልማት እና ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ ይገባል

0
168

በሕግ ፊት እኩል የመታዬት መብት በፍርድ ቤት እኩል መዳኘት ብቻ ሳይሆን እኩል መልማትን፣ ሰብዓዊ መብት መጠበቅን እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትንም እንደሚያጠቃልል ተገለፀ፡፡

ዜጐች በመንግሥት ላይ ያላቸውን አመኔታ እንዳያጡ መብት እና ጥቅሞቻቸውን የሚያስከብሩላቸውን ሕግጋት የሚያስከብሩ አሰራሮች ሊዘረጉና ሊተገበሩ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፓሬሽን ከኢፌዲሪ የሕገ መንግሥት እና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል የስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘውዴ ደምሌ ጋር በእኩልነት መብቶች እና አተገባበራቸው ዙሪያ የስልክ ቃል ምልልስ አድርጓል፡፡

የዜጐችን የእኩልነት መብት አስመልክቶ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 25 “ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸው ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ ጥበቃ  ይደረግላቸዋል” የሚለውን ሀሳብ እንዲያብራሩ የተጠየቁት ዳይሬክተሩ ሁሉም ዜጐች በዘር፣ በብሔር፣  በኃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በሀብት፣ በትውልድ፣ በስልጣን ወይም በሌላ አቋም ምክንያቶች ልዩነት ሳይደረግ በእኩልነት የመታዬት እና የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት ያላቸው መሆኑን ለመግለፅ ነው ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አያይዘውም በዚሁ አንቀጽ 25 መሠረት የዜጐች የእኩልነት መብት ማለት በሕግ ፊት እኩል መዳኘት ብቻ ሳይሆን እኩል መልማትን እና ፍትሃዊ ተጠቀሚነትንም የሚያረጋግጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ የሀገራችን ሕገ – መንግሥታዊ ድንጋጌ  በመነሳት አሁን ያለው አተገባበር ምን እንደሚመስል የተጠየቁት ዳይሬክተሩ በጥናት ላይ የተመሠረተ ምላሽ ባይኖራቸውም የዜጐች ሰብአዊ መብት አከባበር፣ ፍትህ አሰጣጥም ሆነ እኩል መልማት እና ተጠቃሚነት በተጨባጭ ጥያቄ ውስጥ መግባታቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ እነዚሁ የአሠራር ክፍተቶች ደግሞ ዜጐች መንግሥት ላይ የሚኖራቸውን አመኔታ ያሳጣሉ ብለዋል፡፡

የሀገራችን ሕገ መንግሥት ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን፣ እኩል የመዳኘት እና የእኩል ተጠቃሚነት መብታቸውን የሚያረጋግጥ ድንጋጌ ያለው ቢሆንም  እንደ ሕግ አስፈፃሚው እና የሕግ አካላት ጥንካሬ፣ አቅም እና ስነ ምግባር አፈፃፀሙ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ይሆናል ነው ያሉት – ዳይሬክተሩ፡፡

ስለሆነም ይህንኑ የዜጐችን የእኩልነት መብት ከዳኝነትም ሆነ ከሕግ ልማት እና ተጠቃሚት አንፃር እየመረመሩ ሕጉ በአግባቡ እንዲተገበር የሚያስችሉ አሠራሮችንና ደንቦች ከማውጣት፣ ከማስተማር እና ቁጥጥር ከማድረግ ጀምሮ ፍትህን በሚያዛቡ ላይ እርምጃ እስከመውሰድ በሚደረግ ክትትል ሕገ – መንግሥቱን ማክበር እና ማስከበር ከዜጐችም ከመንግሥታዊ አካላትም የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

ካልሆነ ፍትህ የሚጓደልባቸው እና አድልኦ ተፈፅሞብኛል የሚሉ ዜጐች የሚፈጠርባቸው ቅሬታ እየጐለበተ ከመንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነትም እየሻከረ ለሕገ ወጥነት እና ስርዓት አልበኝነት  የሚዳርግ በመሆኑ ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈፃሚውና ሕግ ተርጓሚዉ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩበት እንደሚገባ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

 

 (ጌታቸው ስንታየሁ)

በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here