ለግመሎች የትራፊክ መብራት

0
160

ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

 በየዓመቱ በግንቦት ወር በሰሜን ምዕራብ ቻይና ጋንሱ ግዛት በሚንሻ ተራራ ጀርባ ፀሐይ ስትጠልቅ በኮረብታዎች ላይ በግመሎች በመጓጓዝ ለመመልከት በሚሰባሰቡ ጐብኚዎች የሚፈጠረውን መጨናነቅ ለመግታት የትራፊክ መብራቶች መተከላቸውን ቻይና ዴይሊ ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::

የአሸዋ ንጣፍና ቁልል በሚታይበት ጭው ያለ በረሀ  መጓጓዝን በግመሎች ለሚያደርጉ አገልግሎት የሚሰጡ የትራፊክ መብራቶች ተተክለው ይታያሉ:: ለተመልካች ግርምትን የሚያጭሩት የትራፊክ መብራቶች በየከተማው እንደተተከሉት ለተሽከርካሪ እና ለእግረኞች ሳይሆኑ “ለበረሀው መርከብ” መሆኑ ነው የተብራራው::

እ.አ.አ በ2023 በቻይና ጓንሱ ግዛት ሚንሻ ተራራ አካባቢ የጐብኚዎች ቁጥር 20 ሺህ መድረሱ ተጠቁሟል:: በኮረብታው ላይ ለመጓጓዣነት ሁለት ሺህ አራት መቶ ግመሎችም ዝግጁ ሆነው እንደነበር ነው ለንባብ የበቃው::

በኮረብታዎቹ ላይ ለሚጓጓዙ ጐብኚዎች ግመሎችን የሚያከራዩ ግለሰቦች ከየአቅጣጫው ጊዜውን ጠብቀው ይሰባሰባሉ:: ከነዚህ መካከል ለአብነት በአቅራቢያው ግመሎች የሚያረቡ ዛሆ ዊንሎንግ የተባሉ የ42 ዓመት ጐልማሣ 21 ግመሎችን ለኪራይ አቅርበዋል:: ከግመሎቹ ኪራይ ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደሚያገኙም ተገልጿል::

ከየአቅጣጫው በሚሰባሰቡ ጐብኚዎች እና በመጓጓዣ ግመሎች  ከፍተኛ መጨናነቅ ይከሰታል። ይህን የተመለከቱ የአካባቢው ባለሥልጣናትም የዘየዱት መላ  ልዩ የትራፊክ መብራት በበረሀው መካከል መትከልን ነበር::

በእርግጥም መፍትሔው ችግሩን ማቃለል ችሏል:: አረንጓዴ የግመል ምስል ያለበት መብራት ሲበራ ያቋርጣሉ ቀይ መብራት ሲበራ ግመሎቹ ቆመው ግራ ቀኝ አላፊ አግዳሚውን ያሳልፋሉ::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here