ክልላዊ ፈተናዎች እና የተማሪዎች ዝግጅት

0
331

ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቁ እና ተወዳዳሪ ትውልድን ለማፍራት ታሳቢ ተደርጎ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ ወደ ተግባር ተገብቷል:: ምንም እንኳ  አዲሡ ሥርዓተ ትምህርት በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ቢደረግም የፈተና ሥርዓቱ ግን በዚያው ዓመት አልተጀመረም:: በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በ2016 ዓ.ም ተጀምሯል::

ሥርዓተ ትምህርቱ የፈተና አሰጣጥ ሂደቱን ቀይሮታል:: ባለፉት ዓመታት ክልላዊ ፈተና ለስምንተኛ ክፍል እንዲሁም  ሀገራዊ ፈተናዎች ለ10ኛ እና ለ12ኛ ክፍል  ሲሰጥ ቆይቷል:: በ2015 ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ፈተና  እንዲቀር ተደርጓል::  የስምንተኛ ክፍል  በክልል ደረጃ  እንዲሁም የ12ኛ ክፍል መልቀቂ ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሰጥተዋል::

በአሁኑ ወቅት አዲሡ ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎች ስድስተኛ፣ ስምተኛ እና 12ኛ ክፍል ላይ ይሰጣሉ:: ሥርዓተ ትምህርቱ የተቀየረው ቀድመው መሟላት የነበረባቸው እንደ መጻሕፍት እና ሌሎች መማር ማስተማሩን ውጤታማ ያደርጋሉ፤ ሥርዓተ ትምህርቱም ይዞት የተነሳውን የትምህርት ጥራት ከዳር ለማድረስ ያግዛሉ የተባሉ ግብዓቶች ባልተሟሉበት ሁኔታ መሆኑ በተማሪዎች ዘንድ መረበሽን፣ በመምህራን ዘንድ ጊዜ ብክነትን ማሳደሩ በኲር በተለያዩ ጊዜያት የሠራቻቸው ዘገባዎች እማኝ ናቸው::

ከግብዓት አለመሟላቱ በተጨማሪም በአማራ ክልል ከባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ የተከሰተው የሠላም መናጋት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ፣ ትምህርት የጀመሩትም በጸጥታ ስጋት ምክንያት እያቋረጡ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ በተደጋጋሚ አስታውቋል:: እስካሁንም ድረስ ትምህርት ቤቶችን ከፍተው ተማሪዎችን እንደ አዲስ በመመዝገብ እየተቀበሉ ያሉ ትምህርት ቤቶች ባሉበት ወቅት ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎች እንዴት ይሰጣሉ? የሚለው የብዙኃኑ ጥያቄ ነው::

ከግንቦት ወር መግቢያ ጀምሮ የክልሉ ትምህርት ቢሮን ጨምሮ የተለያዩ ዞኖች፣ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳድሮች ቀዳሚ ትኩረታቸው ከሰኔ 4 እስከ ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የሚሰጡት ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎች ሆነዋል:: የደብረ ብርሐን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ በ2016 ዓ.ም 2ሺህ 729 የስድስተኛ ክፍል እና 3ሺህ 102 የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችን ያስፈትናል::

የመምሪያው ኃላፊ መቅደስ በዙነህ ለአሚኮ እንደገለጹት ከሰሞኑን ተፈታኞች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው:: ከሳምንቱ የትምህርት ቀናት በተጨማሪ ቅዳሜ እና እሑድን በመጠቀም ይዘቶችን በአግባቡ ለመሸፈን ይሠራል:: የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርት በማዘጋጀት በተጠናከረ ሁኔታ መስጠት እንዲሁም የመለማመጃ ፈተና መስጠት ላይም ትኩረት ተደርጎ ይሠራል::

የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ታደሰ ሸዋፈራ የስድስተኛ፣ ስምንተኛ እና 12 ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን ለማብቃት ለሁለት ወራት የሚቆይ የተቀናጀ ዘመቻ መጀመሩን መምሪያው የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ባካሄደበት ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም አስታውቋል:: ፈተናው እንደ ትምህርት አጀማመራቸው በሁለት ዙር እንደሚሰጥም መምሪያው አስታውቋል ሲል የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ አስታውቋል::

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያም በ2016 ዓ.ም ይሰጣሉ በተባሉ ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል። የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ደስታው ዓለሙ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የግል ተፈታኞችን ጨምሮ ከ22 ሺህ በላይ የስድስኛ፣ የስምንተኛ እና የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተው መመዝገባቸውን ገልጸዋል። ተማሪዎችን በሥነ ልቦና ማዘጋጀት፣ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሸፈኑ የትምህርት ይዘቶችን መሸፈን እና ተማሪዎችን ለፈተና ዝግጁ ለማድረግ በልዩነት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀሪ ወራትም ለተፈታኝ ተማሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች የባከነውን ትምህርት  ማካካስ እና ለፈተና የማዘጋጀት ሥራ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የፈተና መስጫ ማዕከላትን ደኅንነት ማረጋገጥ፣ ተማሪዎችን ለፈተና ማዘጋጀት እና መጓጓዣ/ትራንፖርት/ ማመቻቸት ከወዲሁ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ሆነው ሊሠራባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን በጎንደር ከተማ ገምግሟል። በዚህ ወቅት የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ እየሩስ መንግሥቱ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በክልል ደረጃ የሚሰጠውን የስድስተኛ ክፍል ፈተና የሚወስዱ ተፈታኞችን ጨምሮ የስምንተኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በዚህም መምህራን የተለያዩ ጥያቄዎችን እያዘጋጁ በመጠየቅ የተማሪዎችን ዝግጁነት ሊያረጋግጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ቤተ መጽሀፍቶችን ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ በሁሉም ቀናት ክፍት በማድረግ ተማሪዎች አንብበው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እያደረጉ ያሉ ትምህርት ቤቶችን አመስግነዋል:: ተሞክሮው በሁሉም አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል። ፈተናውን ያለምንም ችግር ለማጠናቀቅ ከማኅበረሰቡ ጋር መግባባት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here