ነገን በዛሬ መሻገሪያ

0
175

ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

“ገንዘብ በእጅህ ሲገባ ያጣህበትን ጊዜ አስብ” የሚሉት ጃፓኖች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት የምጣኔ ሀብት እድገት ጀምረው በግማሽ ክፍለ ዘመን ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ ተመድበዋል:: ይህም የሆነዉ ለቁጠባ ልዩ ትኩረት በመስጠታቸዉ ነዉ::

በኢትዮጵያ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ከሚያገኘው ገቢ ወጭን በማብቃቃት እየቆጠበ ይገኛል:: ቁጠባ  የቆጣቢውን ፣ የማህበረሰቡን እና የሀገርን ምጣኔ ሀብት ያሳድጋል::

ቁጠባ ለነገ የተሻለ ሕይወት ፣ለእርጅና ዘመን፣ ወደ ፊት ለሚያጋጥሙ የገንዘብ እጥረት፣ ለትምህርት ፍላጎት፣ ሊያጋጥም ለሚችሉ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥፘዊ አደጋዎች… መቋቋሚያ የሚሆን የምናስቀምጠው ገንዘብ ነው:: ምንም እንኳን የእያንዳንዱ ግለሰብ ቁጠባ የሚመነጨው ከፍጆታ ከሚተርፈው ገቢ እንደሆነ የብዙዎች ሃሳብ ቢሆንም ወጭን በማብቃቃት ዝቅተኛ ገቢ ያለው ሰውም መቆጠብ እንዳለበት ይመከራል::  የሰው ልጅ ሠርቶ ከሚያገኘው ቀንሶ ማስቀመጥን አላማዬ ላለው መዳረሻው ቁጠባን ስንቁ አድርጎ መያዝ ከጀመረ ዘመናትን አስቆጥሯል:: የፋይናንስ ተቋማት ባልነበሩበት ጊዚያት እንኳን ገንዘብ በየስርቻው ያስቀምጥ ነበር:: እቁብን እና በመሳሰሉት ተለምዷዊ ስርዓቶች መቆጠብ ለዘመናት አብሮት ዘልቆ ቆይቷል::

ሰዎች በተሻለ መልኩ እንዲቆጥቡ ደግሞ የፋይናንስ ተቋም መኖር መሰረታዊ ጉዳይ ነው:: የፋይናንስ ተቋሙ ሕጋዊነት፣ ተደራሽነት እና አስተማማኝነት ለቆጣቢው ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታ ነው:: የተሻለ ሕይወት ለመምራት የሚረዳንን ገንዘብ ማግኘት የምንችለው በዘመናዊ መንገድ ስንቆጥብ ነው::

የጣና ማይክሮ ፋይናንስ የኦፕሬሽን ክፍል ኃላፊ ይሄነው አንዳርጌ  በበኩላቸው “ቁጠባ ነገን በማሰብ ያለውን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ነው:: የሰው ልጅ ከእለት ፍጆታው ቀንሶ የሚያስቀምጠው ሀብት በእርጅና ዘመን፣ ለድንገተኛ አደጋ እና ለህክምና አገልግሎት ጥቅም ላይ ይውላል” ሲሉ አስረድተዋል::

ጣና ማይክሮ ፋይናንስ አዲስ አበባን  ጨምሮ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ቅርንጫፎችን ከፍቶ ዜጎች እንዲቆጥቡ እና የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል:: ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ዘጠኝ ሺህ የሚጠጋ የቁጠባ ደንበኞች እንዳሉት የተናገሩት አቶ ይሄነዉ  ለ846 ተበዳሪዎች የብድር አገልግሎት እንደሰጠ እና  ከ156 ሚሊዮን ብር በላይ ለብድር አገልግሎት እንዳዋለም ለበኩር ጋዜጣ ተናግረዋል::  በቀጣይ አርሶ አደሩ እንዲጠቀም በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል:: መስፈርቱን አሟልተው የሚመጡ የመንግስት ሠራተኞች የብድር አገልግሎት እያገኙ መሆኑንም ጠቁመዋል:: መስራት ፈልገው ምንም ገንዘብ ለሌላቸው ወገኖች ሠርተው የሚለወጡበት መንገድ እየተመቻቸ ነው  ብለዋል:: የፋይናንስ ችግር ላለባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ችግራቸውን ለመፍታት አላማው አድርጎ እየሰራም ይገኛል:: ማሕበረሰቡ ወደ ተቋሙ በመምጣት የቁጠባ ባህሉን ማሳደግ እና የብድር አገልግሎት ማግኘት እንዳለበትም አስረድተዋል::

አቶ ገዳሙ ተረፈ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው:: ቁጠባ የክፉ ቀን መሻገሪያ ነው ይላሉ:: ቁጠባ ከትንሽ ገንዘብ ነው የሚጀምረው የሚሉት አቶ ገዳሙ ተርፎን ሳይሆን ካለን ገቢ ላይ ቀንሰን ነገን በማሰብ ነው ይላሉ:: ቁጠባ ለልጆች ማስተማሪያ ለቤት መስሪያ እና ለችግር ጊዜ የሚደርስ ሀብት ነው:: ቁጠባ በእጅጉ አስፈላጊ እና መሰረታዊ ነገር ነው ይላሉ:: አቶ ገዳሙ ከጣና ማይክሮ ፋይናንስ ቆጣቢ እና ተበዳሪ ናቸው:: ወደ ጣናው ማይክሮ ፋይናንስ ከመሄዳቸው በፊት የቁጠባን ምንነት እና የብድርን አገልግሎት በውል ያልተረዱ እንደነበር አጫውተውናል:: የሚሰሩትን ቤት ለማጠናቀቅ እና ለሌሎች መሰረታዊ ፍጆታዎች ከጣና ማይክሮ ፋይናንስ ብድር እንዳገኙ ነግረውናል:: ብድሩ ለችግሬ መፍትሄ ሆኖኛል በቀጣይም ይበልጥ ለቁጠባ አነሳስቶኛል ባይ ናቸዉ:: የሰራተኞች ትጋት ፣የደንበኛ አያያዘቸው፣ የመረጃ አሰጣጣቸው፣ፈጣን እና ቀልጣፍ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል:: በጊዜው የሚፈልጉትን ብድር በማግኘታቸው ይበልጥ ተደስተዋል:: እንደ አቶ ገዳሙ ገለጻ በቀጣይ ተቋሙ በደሞዝ እስኬል የሚያበድርበት የገንዘብ መጠን ከፍ ቢል የሚል ሀሳባቸውን አጋርተውናል::

ሌላው የጣና ማይክሮ ፋይናንስ ተጠቃሚ እና ቆጣቢ ደግሞ አቶ ሰለሞን ጥበቡ ናቸው:: ቁጠባ እጅግ ለሰው ልጅ መሰረታዊ ነገር መሆኑን ይናገራሉ:: ገንዘብን በአግባቡ እና በስርዓት መቆጠብ እንዲሁም ዘመናዊ አሰራርን መከተል እንደሚገባ አመላክተዋል:: በጣና  ማይክሮ ፋይናንስ እየቆጠቡ የብድር ተጠቃሚ መሆናቸውን ነግረውናል:: በአሁኑ ጊዜ በየወሩ የሚቆጥቡት አቶ ሰለሞን በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ ለመቆጠብ አስበዋል፤ እንዲሁም አክሲዮን ለመግዛትም በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ነግረውናል:: የቁጠባን ጠቀሜታ በመረዳት ብዙ ጓደኞቻቸውን እንዲቆጥቡ እና ወደ ፋይናንስ ተቋሙ እንዲቀላቀሉ ማድረጋቸውን ነግረውናል:: ከጣና ማይክሮ ፋይናንስ ተበድረው ቤታቸውን ሠርተው እንዳጠናቀቁም በማከል:: ወደፊት ተቋሙ የካፒታል መጠኑን ከፍ በማድረግ የሕብረተሰቡን ችግር መፍታት የሚችልበትን መንገድ መፍጠር እንዳለበት ሐሳባቸውን ሰጥተዋል::

ቁጠባ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው በመሆኑ የተቆጠበውን ገንዘብ  ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮችን እየፈታሁ ነው ብለዋል:: በመቆጠቤ ለእኔ እና ለልጆቼ ለወደፊት ዋስትና የሚሆን ሀብት እያፈራሁበት ነውም ብለዋል::

በኢትዮጵያ ሀገር ወዳድ ግለሰቦች ሐሳብ አመንጭነት እና አነሳሽነት ከ 2 ሺህ 550 በላይ በሚሆኑ ባለሀብቶች ተደራጅቶ ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ህጋዊ ፍቃድ አግኝቶ የቁጠባ እና ብድር አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ተቋም ነዉ ጣና ማይክሮ ፋይናንስ::  ከባንክ የብድር አገልግሎት ማግኝት የማይችሉትን እና ዝቅተኛ የሕብረተሰብ ክፍሎችን  በማገልገል ላይ እንደሆን አቶ ይሄነው ተናግረዋል:: በቀጣይ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ክልሎች አገልግሎት ለመስጠት ያቀደ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ባሕር ዳር ከተማን ጨምሮ በአማራ ክልል በከፈታቸው ቅርንጫፎች በአካባቢው ለሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የቁጠባ እና የብድር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል::

ለአብነትም የጥቃቅን ንግድ ሥራ የቡድን ብድር፣ የአነስተኛ ንግድ ሥራ የግል ብድር፣ የፍጆታ ብድር፣ የግንባታ ሥራ ብድር እና የግብርና ሥራ ብድር ተጠቃሾች ናቸው:: ማይክሮ ፋይናንሱ በኢትዮጵያ ውስጥ እምነት የሚጣልበት እና ተመራጭ በማድረግ በዝቅተኛ እና በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን አምራች ዜጎችን ማህበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት  እየተንቀሳቀሰ ይገኛል::

አሁን ላይ እየተሰጠ ያለው ብድር ውስን በመሆኑ በቀጣይ በማጠናከር በሰፊው ለመስራት መታቀዱንም ተገልጿል::

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር  በላይነህ አስማረ “ቁጠባ ለፈጣን ፍጆታ የማይውል፣ ለወደፊት ጥቅም ላይ የሚውል ፣ ለቀጣይ ለኢንቨስትመንት ዝግጁ የምናደርግበት እና የተሻለ ሕይወት የምንመራበት መንገድ ነው ” ይላሉ:: እንደ መምህሩ ማብራሪያ ነገ ኢንቨስት የምናደርው ዛሬ የምንቆጥበው ገንዘብ ነው ፤ነገር ግን  በኢትዮጵያ የቁጠባ ባህል የዳበረ አለመሆኑንም ጠቁመዋል:: የኢትዮጵያ ቁጠባ ከጥቅል ሀገራዊ ምርቷ (GDP) ከዓመት ዓመት ቢለያይም ከ10 እስከ 20 በመቶ እንደሆነ እና  ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑን ነዉ የሚያነሱት:: ሌሎች የዓለማችን ሀገራት ከ50 በመቶ በላይ ከሀገሪቱ ጠቅላላ ሃብት በቁጠባ የሚያበረክቱ መኖራቸውን ነው የሚያብራሩት:: ለአብነትም አየርላንድ፣ ጃፓን፣ ኳታር፣ ሲንጋፖር፣ ኖርዌይ ፣ በዓለማችን ከፍተኛ የቁጠባ ባህል ያዳበሩ ሀገራት ናቸው ብለዋል::  ጅቡቲ ፣ኮንጎ፣ ዛምቢያ እና ጋቦን የተሻለ የቁጠባ ባህል ያዳበሩ የአፍሪካ ሀገራት መሆናቸውን ያነሱት መምህር በላይነህ ይህም የሆነው የተሻለ ግንዛቤ እና እውቀት ስላላቸው እንዲሁም የቁጠባን ጠቀሜታ ስለተረዱ ነው ይላሉ:: ያለ አግባብ ወጭን በማስቀረት እና ብክነትን በመቀነስ መቆጠብ ነገን የተሻለ ማድረግ ይገባልም ብለዋል:: ቁጠባ ለግለሰብም ሆነ ለሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ከፍተኛ ድርሻ ስላለው ማንኛውም ሰው ከሚያገኘው ገቢ በትንሹም ቢሆን ለቀጣይ መቆጠብ እንዳለበት ይመክራሉ::

 (መልካሙ ከፋለ)

በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here