ክረምቱን ለሰላም እና ለልማት!…

0
155

ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

“ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ፣

ወፍጮው እያገሳ መስከረም ዘለቀ” እንዲል አርሶ አደሩ፣ እርሻ እና ክረምት የተያያዙ ናቸው። ክረምቱ በብዛት  በተፈጥሯዊዉ ዝናብ ምክንያት ለእርሻ ዝግጁ ሆኖ ሰብል  ይሸፈናል። መሬትም አረንጓዴ ጎፈሬዋን ትነቅሳለች። ውኃማ አካላትም ይሞላሉ። ክረምቱ ለግብርናው  መሰረት ይሆናል። የደረቀው ለምልሞ፣ የተዘራው አሽቶ፣ መሬቱም ወርዝቶ የሚታይበት ወቅት ነው።  አንዴ ክረምቱ ካለፈ፣ ላላፈ ክረምት ቤት አይሰራም ነው የሚባለው።

አርሶ አደሩ ‘‘ በሰኔ እናት ልጇን የማታነሳበት ወቅት ነው’’ ሲል ይበይነዋል።  ይሄን አስፈላጊ ወቅት በተገቢው  መንገድ ተጠቅሞ ለማልማት ሰላሙ ዋነኛው አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ክረምቱን ከተፈጥሯዊዉ የመብረቅ ጉርምርምታ እና የዝናብ  ድምፅ ውጪ ሰው ሰራሹ የመሳሪያ ድምፅ የማይሰማበት ማድረግ ያስፈልጋል።

በግልፅ እንደሚታወቀው በአማራ ክልል ያለው ቀውስ ሰው ሰራሽ  በመሆኑ፣ ሰው ያባብሰዋል አሊያም መፍትሄ ይሰጠዋል።  ስለዚህ ከማባባስ ይልቅ ለማሻሻል፣ ነገሩን በስክነት መላ እንዲበጅለት ከተካረሩ አካሄዶች ወጥቶ መወያየት እና መሰረታዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ ያስፈልጋል። ስመ ጥሩው ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ኢትዮጵያ ምን አይነት አስተዳድር ያስፈልጋታል? ሲል በ1960ዎቹ መባቻ አካባቢ ባሳተሙት መጽሐፍ  ግጭት ሲነሳ በመንግሥት በኩል በፍጥነት የጎደለውን መሙላት አስፈላጊ ነው ይላሉ። አብነት ሲያነሱም የ1953 የመፈንቀለ መንግሥት ሙከራ መክሸፍ የዘውዳዊዉን መንግሥት   በትምክህት እንዲቆም፣ ምንም ሳያሻሽል በሥልጣኑ እንዲቆይ እንዳደረገው ይገልጻሉ።  በአሸናፊነት መንፈስ ያለምንም ማሻሻያ የቀጠለው  የአፄ ሃይለስላሴ  መንግሥት ከአስራ ሦስት ዓመት በኋላ ተሰባብሮ ወደቀ።

ቀድሞ የ1953ቱን የመፈንቀለ መንግሥት ሙከራ መነሻን በማጤን የፖለቲካ እና የአስተዳደር ማሻሻያ ቢደረግ ኑሮ በኢትዮጵያ የሰከነ፣ ሕዝብን የሚጠቅም፣ የተሻሉ ተቋማትን የሚያዋልድ  አብዮት ወይም ለውጥ ይመጣ ነበር። አሁንም  ችግሩን መፍታት እንጅ ችግር አቅራቢዎችን  በጠላትነት መፈረጅ አይበጅም፡፡  መነጋገር፣ ራስን በየዘርፉ መገምገም፣ የማሻሻያ ሐሳቦችን፣ ንግግር እና ድርድርን ማድረግ አርሶ አደሩ ክረምቱን ለእርሻው እንዲያውል ማገዝ ያስፈልጋል።

ለተፈጠረ ግጭት ሁሉ ጠብመንጃ ምላሽ አይሆንም። የሰው ደም ሳይፈስ በመነጋገር፣ በመወያየት እና በመደራደር መግባባት፣ መተማመመን እና አብሮ መጓዝ ስለሚቻል ሰላምን ለማምጣት አሁን ካሉበት መንገድ ወጥቶ ርቆ መጓዝ ተገቢ ነው። ሁሉም አካል ጠርዝ እና ጠርዝ ከመቆም መቀራረብን፣ ነገሩን ማለሳለስን እና መወያየትን  መምረጥ ይኖርበታል።

እርቅ እና ስምምነት እንዲመጣ መደማመጥ የግድ ይላል። አለበለዚያ ጫፍ እና ጫፍ ሆኖ ገመድ በመጎተት የሚመጣ ድል የለም። ሰላም ሊመጣ  የሚችለው ፍትሐዊነት ሲሰፍን፣ አካታች እና አሳታፊ ሥርዓት ሲዘረጋ  ነውና ለዚህ ሁሉም ወገን መትጋት ይገባዋል፡፡

ሁሉም ሲያሸንፍ ሁሉም ሰላም ይሆናል። ልማቱም ይቀላጠፋል። የተናፈቀው ሰላምም እንደ ክረምቱ መሬት ይለመልማል። በክረምቱ  ተማሪ፣ መምህሩ፣ ዳኛ እና አርሶ አደሩ ለአዲሱ ዓመት ሰፊ ዝግጅት አድርገው 2017 ዓ.ም 2016 ዓ.ምን እንዳይመስል ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል- መጪውን ክረምት ለልማት እንዲውል የሰላም  መስፈን  ጠቃሚ ጉዳይ ነውና።

 

በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here