ምርታማነትን ለማስቀጠል

0
152

ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን እየተስተዋሉ የመጡ እና መፍትሔ የራቃቸው የሰላም መናጋቶች የግብርናው ዘርፍ ክፉኛ እንዲፈተን አድርገዋል:: የሰሜኑ ጦርነት በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በርካታ መሬትን ጾም ከማሳደር ባለፈ የተመረተውም ሳይሰበሰብ የባሩድ አረር ቀለብ ሆኗል::

ይህ ጦርነት ምንም እንኳ በሰላም ስምምነት ቢቋጭም የአማራ ክልል ግን ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በከፍተኛ ግጭት ውስጥ እያለፈ ይገኛል:: ግጭቱ በክልሉ ምርት እና ምርታማነት ላይ ይዞት ሊመጣ የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ በመረዳት በኲር ጋዜጣ በተለያዩ ጊዜያት መፍትሔ እንዲፈለግ ትኩረት በመስጠት ሠርታለች፤ እየሠራችም ነው።

አሥር ወራት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንዲያልፍ የተደረገው ክልሉ አሁንም ከአንጻራዊነት የተሻገረ ሰላም እንዳልተፈጠረበት  የክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ አስታውቋል:: ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተገኘ ያለውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀምም የልማት ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም ግጭቱ በዘላቂነት አለመቋጨቱ ግን በክልሉ ግብርና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) አስታውቀዋል::

በተያዘው ዓመት 250 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ በክልሉ በተፈጠረ የፀጥታ ችግር ምክንያት 153 ሺህ ሄክታር ብቻ ማልማት እንደተቻለ የክልሉ እና የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም በመቅደላ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የበጋ መስኖ ስንዴን በጎበኙበት ወቅት  አስታውቀዋል::

ግጭቱ በክልሉ ምርት እና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር ችግሩን በአጭር ጊዜ በሰላማዊ ንግግር በመፍታት ሙሉ ትኩረትን በመኸር እርሻው ላይ እንደሚያደርግ መንግሥት አስታውቋል:: በክልሉ በ2016/17 የምርት ዘመን 5 ነጥብ 18 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ይሸፈናል:: በዓመቱ መጨረሻም 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል::

በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት መፍታት፣ የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በበቂ መጠን እና በወቅቱ ማድረስ፣ የእርሻ መካናይዜሽን ጅምሩን ማስፋት፣ የአፈር አሲዳማነትን ማከም በዓመቱ ለማግኘት የታቀደውን የምርት መጠን ለማሳካት ሊተገበሩ የሚገባቸው የምርታማነት ማስጠበቂያ ተግባራት ሆነው በትኩረት እየተሠራባቸው ይገኛል::

በምእራብ ጎጃም ዞን የጃቢ ጠህናን ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አያና ጥላሁን በስልክ ለበኲር ጋዜጣ እንዳስታወቁት ዘንድሮ አንድ ሄክታር መሬት በበቆሎ፣ ጤፍ እና ስንዴ ይሸፍናሉ። ከዚህም እስከ 50 ኩንታል ምርት ይጠብቃሉ።

በዓመቱ የጠበቁትን ምርት ለማግኘት የድግግሞሽ እርሻን እያከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል። አራት ኩንታል የተለያዩ አይነት የአፈር ማዳበሪያዎችን ለመጠቀም ማቀዳቸውንም ጠቁመዋል። እስካሁንም ሁለት ኩንታል ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ዘንድሮ በአቅርቦት፣ በሥርጭት እና በዋጋ የተሻለ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።

በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ፍሬው ንብረቴ በበኩላቸው በዓመቱ ሁለት ነጥብ አምስት ሄክታር ማሳቸውን በበቆሎ፣ በጤፍ፣ በስንዴ እና በገብስ ለመሸፈን እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ ለበኲር ጋዜጣ በስልክ አስታውቀዋል::

በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በግብርና ግብዓት አቅርቦት ላይ የከፋ ተጽእኖ አሳድሮ ማሳቸውን ጾም እንዳያሳድረው ስጋት ፈጥሮባቸውም መቆየቱን አርሶ አደሩ  ተናግረዋል:: ይሁን እንጂ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ በስርጭት እና በዋጋ ከባለፈው ዓመት ፍጹም የተሻለ ሆኖ እንዳገኙት አስታውሰዋል:: ተደጋጋሚ እርሻ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን የገለጹት አርሶ አደሩ በዓመቱ ከሚያስፈልጋቸው 19 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች የሚሆን ሁለት ኩንታል ማዳበሪያ ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል:: በቀጣይ አጭር ጊዜያት የአፈር ማዳበሪያ እንደሚገባ እና ቀበሌዎች በተሰጠው ተራ መሰረት እንደሚያገኙ ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል::

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በግብርና ልማት ከተሠማሩ ባለሐብቶች ጋር ግንቦት 6 ቀን 2016 መክሯል። በዚህ ወቅት የተገኙት የሞረት እና ጅሩ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ደመላሽ ይፍሩ በዓመቱ ስንዴ እና ጤፍ በስፋት ለማምረት አቅደዋል:: ከእነዚህ የግብርና ሰብሎች እስከ 200 ኩንታል የሚደርስ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል::

የእርሻ ሥራቸውን በትራክተር እንደሚያከናውኑ አርሶ አደሩ ጠቁመዋል:: ግብአትን በተመለከተ ግን የምርጥ ዘር ዓይነቶች ከሁለት ዓመት በኋላ ምርታማነታቸው ስለሚቀንስ ግብርና ምርምር የተሻሻለ የስንዴ ዝርያ  እንዲሁም የአፈር ማዳበሪያም በበቂ መጠን እንዲቀርብ ጠይቀዋል።

የክልሉን ምርታማነት ለማረጋገጥ በክልሉ ግብርና ቢሮ በዓመቱ በትኩረት ይሠራበታል የተባለው የእርሻ ሜካናይዜሽን ነው:: ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በክልሉ መልማት ከሚችለው መሬት ውስጥ 42 በመቶ የሚሆነው ለእርሻ ሜካናይዜሽን ምቹ ነው:: ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በሜካናይዜሽን እየለማ የሚገኘው ከ14 በመቶ አይበልጥም::

ቢሮው የጀመረውን ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች አቅርቦት  ለማስፋት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል:: ለአብነት ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም 40 ትራክተሮችን አሰራጭቷል:: በአጠቃላይ በዓመቱ ለአርሶ አደሩ ያሰራጫቸውን ትራክተሮች ቁጥርም ወደ 148 አሳድጓል::

የአፈርን ኬሚካላዊ ይዘት አማካይ ሊያደርጉ የሚችሉ እንደ ማግኒዥየም፣ ፖታሽየም፣ ካልሽየም ያሉ ንጥረ ነገሮች በከፍተኛ ዝናብ ሲታጠቡ ወይም መጠናቸው ሲቀንስ የሚፈጠረው የአፈር አሲዳማነት በክልሉ ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድርም ተሰግቷል::

ከክልሉ ግብርና ቢሮ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ እንደተገኘው መረጃ ከሆነ በክልሉ ከሚታረሰው 5 ነጥብ 18 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታሩ በከፍተኛ አሲዳማነት የተጠቃ ነው:: ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነውም በመካከለኛ ደረጃ ተጠቅቷል::

ከሀምሳ በመቶ በላይ የምርት መቀነስ የሚያስከትለውን የአፈር አሲዳማነት ማከም የክልሉን የቀደመ ምርታማነት ለማረጋገጥ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን መረጃው ያሳያል:: 623 ሺህ 550 ኩንታል የግብርና ኖራ በማቅረብ 20 ሺህ 785 ሄክታር መሬትን በኩታገጠም ለማከም ታቅዶ እየተሠራ ነው::

ትልቁ እና ወሳኙ የምርት ማሳደጊያ ግብዓት የአፈር ማዳበሪያ ነው:: መንግሥት ከፍተኛ በጀት በመመደብ እና ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ በልዩነት ከሚሠራባቸው የግብርና ግብዓት አይነቶች መካከል ቀዳሚው የአፈር ማዳበሪያ ነው:: በተለይ ባለፈው ዓመት ያጋጠመው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳይከሰት ዘንድሮ ግዥው ቀድሞ መከናወኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል::

ክረምት ከመግባቱ በፊት ሥርጭቱን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ቢሆንም በአማራ ክልል የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ግን ሌላ ፈተና ሆኖ ብቅ ማለቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል:: ያም ሆኖ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭቱ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ዋቢ ነው::

የሰሜን ጎጃም ዞን ለ2016/17 የምርት ዘመን 1 ሚሊዮን 164 ሺህ 854 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ አቅዷል:: ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም 657 ሺህ 31 ኩንታል የቀረበ ሲሆን 549 ሺህ 556 ኩንታል ማሰራጨት መቻሉን ያስታወቁት የዞኑ ኅብረት ሥራ ማኅበር ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሀምሳሰው አቼነፍ ናቸው:: አሁንም 44 በመቶ የሚሆነው አለመቅረቡን እና በቀሪ ወራት በአጭር ጊዜ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል::

በምዕራብ ጎጃም ዞን በምርት ዘመኑ ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሠብሠብ ታቅዷል። ዞኑ ይህንን ያስታወቀው የ2016/17 የምርት ዘመን የክረምት ሥራዎች የንቅናቄ መድረክ ባካሄደበት ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ነው። 246 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ይሸፈናል፤ ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርትም እንደሚጠበቅ የመምሪያ ኀላፊዉ ተስፋዬ አስማረ ተናግረዋል:: ለአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ በማቅረብ እና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ዕቅዱን ለማሳካት ከወዲሁ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል::

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም እንዳስታወቁት በዘንድሮዉ የምርት ዘመን የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን  እና ግብዓትን በሙሉ ፓኬጅ ለመጠቀም ትኩረት ተደርጓል። በዚህ ወቅትም የግብዓት አቅርቦት እና የማሣ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል::

ለ2016 ዓ.ም ግዥ ከተፈጸመው 8 ነጥብ 05 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታሉ ወደ ክልሉ መግባቱን ጠቁመዋል:: ከዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነው ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል:: በተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመጠቀም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል::

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም የግብርና ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል። የምክር ቤት አባላቱም እስካሁን የአፈር ማዳበሪያ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ሚኒስትሩ ግዥ በተፈጸመው እና ወደ ሀገር ውስጥ በገባው ልክ በአጭር ጊዜ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ምን አይነት የክትትል እና የቁጥጥር ሥርዓት ዘርግቶ እየሠራ ነው? ሲሉ ገልጸዋል:: ባለፈው ዓመት የዘጠኝ ወር ሪፖርት ሲገመገም በዓመቱ ምንም አይነት የማዳበሪያ ችግር እንደማይኖር እና በአጭር ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ይደረጋል ተብሎ እንደነበር አባላቱ አስታውሰዋል:: ይሁን እንጂ በወቅቱ እስከ ነሐሴ አጋማሽ ማዳበሪያ ያልደረሳቸው አካባቢዎች ነበሩ፤ በርካታ መሬትም ጾም አድሯል ሲሉ ተናግረዋል:: አሁንም ስርጭቱን በወቅቱ ፈጥኖ ተደራሽ ማድረግ ካልተቻለ ያምናው እንዳይደገም ስጋት አለን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል::

ግብርና ሚኒስቴር ለ2016 ዓ.ም 23 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ አቅዶ በአሁኑ ወቅት 19.4 ሚሊዮን ኩንታል ግዥ መፈጸም መቻሉን ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ሚኒስቴሩ የዓመቱን የማዳበሪያ ግዥ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት አስታውቀዋል:: ሚኒስትሩ ለ2015 ዓ.ም የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ተመድቦ የነበረው 1 ነጥብ 59 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ሲያስታውሱ፣ ለዘንድሮው ዓመት የተመደበው ግን 930 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ተናግረዋል:: ለዘንድሮው የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የተመደበው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር እጅግ ያነሰ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል:: ነገር ግን የበጀቱ ቀድሞ መለቀቅ እና ግዢው ቀድሞ መፈጸሙ ሚኒስቴሩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሆኖ የተሻለ አፈጻጸም ላይ እንዲገኝ አስችሎታል ብለዋል::

16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ደርሷል፤ እስካሁንም 11 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙን ተገልጿል፤ ከዚህም ውስጥ እስከ ግንቦት 5 ቀን  2016 ዓ.ም 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል መሠራጨቱ ታውቋል::

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ  ሰለሞን ላሌ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ሚኒስቴሩ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ በወቅቱ መፈፀሙ የሚበረታታ ነው። የአፈር ማዳበሪያ በጊዜ እና በበቂ መጠን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እና ሕገ-ወጥ ግብይት እንዳይኖር በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል። አሲዳማ መሬቶችን ለማከም ሚኒስቴሩ እያከናወነ ያለውን ሥራም አድንቀዋል::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here