ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም
በባህል እና ልማድ ውስጥ በርካታ ሀብቶች አሉ:: እነዚህን ሀገረሰባዊ ሀብቶችን መንዝሮ መጠቀም ለሀገር ዕድገት እና ስልጣኔ ፋይዳው የጎላ ይሆናል:: ሀገር በቀል ዕውቀቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ምሁራን በሳይንሳዊ መንገድ ጥናት ሊያደርጉባቸው እንደሚገባ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከሰሞኑ ገልጾም ነበር::
ሀገራችን ከምትታወቅባቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶች መካከል የባሕል ሕክምና፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ ቁጠባ፣ ባሕላዊ የአስተዳደር ሥርዓት፣ የዘመን አቆጣጠር፣ ዕደ ጥበብ እና የእርቅ ሥርዓት ተጠቃሽ ናቸው። ለሀገር ግንባታ ጉልህ ሚና ያላቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶች ትኩረት ባለማግኘታቸው ተገቢውን ጥቅም ሳይገኝባቸው ቆይቷል። በመሆኑም ሀገር በቀል ዕውቀት ለሀገራዊ ችግሮች መፍትሔ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል የሚል እሳቤ ከዚህም ከዛም እየመጣ ነው::
የሀገር በቀል ዕውቀት አስፈላጊነት የቅንጦት አይደለም። አንዳንድ ሀገሮች ለሀገር በቀል ዕውቀት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተዋል፤ በእጅጉ እየተጠቀሙበትም ይገኟል።
የቻይና እና የህንድ ተሞክሮ
ቻይና በተለያዩ ግዛቶቿ የቀርቀሃ ተክልን በባሕላዊ መንገድ በማልማት የደን ሽፋኗን ጨምራለች፤ ዜጎቿም የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመሥራት ገቢያቸውን ማሳደግ ችለዋል።
ቻይና በሌላ በኩል በባሕላዊ ሕክምናዋ ትታወቃለች። አኩፓንክቸር የተሰኘው ሕክምና አንዱ ነው። ይህ ሕክምና ደረቅ መርፌን በመጠቀም የተለያዩ ህመሞችን ማከም ያስችላል::
ህንድ የሀገር በቀል ዕውቀቶችን ከሳይንስ ጋር በማዛመድ ጥቅም ላይ ታውላለች:: ከእነዚህ ውስጥ በግብርናው ዘርፍ የሰብል ዘር ሳይበላሽ ለረዥም ጊዜ አንዲቆይ በኒም ቅጠል ሸፍኖ ማስቀመጥ አንዱ ስልታቸው ነው። በተመሳሳይ የአየር ፀባይ ሁኔታን የመተንበይ ማለትም ከባድ ዝናብ ወይም ድርቅ ሊከሰት የሚችልበትን ዕድል በባሕላዊ መንገድ የማወቅ ጥበብ አላቸው ይላል ሳይንስ ዳይሬክት ድረ ገጽ። ነገር ግን ይህ ጥበብ ሚስጥራዊ መሆኑን ድረ ገጹ ገልጿል::
በሀገራችን ስለሀገር በቀል ዕውቀት ጉዳይ በሕገ መንግሥታችን የተቀመጠ አንቀጽ ባይኖርም እንኳ በአዋጅ ቁጥር 482/2006 የተጠቀሰ ሐሳብ አለ። በተጨማሪም ሀገራችን የፈረመችውን ዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ስምምነት (Biodiversity Convention, 1992) መሠረት በማድረግ በተዘጋጀው ብሔራዊ የብዝኃ ሕይወት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ስለሀገር በቀል ዕውቀት ጉዳይ መጠቀሱን የባሐል እና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ከኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሀገር በቀል ዕውቀቶች ፎረም ምስረታ በአዳማ ከተማ አካሂዷል። የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ሁለንተናዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው የተበታተነውን አቅም በማቀናጀት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሌላ ሀገር ያልተዋስናቸውን እና የእኛ መገለጫዎች የሆኑ የፖለቲካ እና የአሥተዳደር ዘይቤዎችን ጨምሮ ባሕላዊ እውቀቶቻችንን በአግባቡ መጠቀም የሰላም ግንባታችንን ለማፋጠን እንደሚረዳ ጠቁመዋል። የፎረም ምስረታው በየዘርፉ በተናጠል በርካታ ሥራዎችን ሲሠሩ ለቆዩ ባለሙያዎች የጋራ አቅም እንደሚሆንም ተናግረዋል።
ከሁሉም በላይ ሀገር በቀል ዕውቀቶች በተሻለ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ምሁራን በሳይንሳዊ መንገድ ጥናት ሊያደርጉባቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በሚኒስቴሩ የባሕል እና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ በበኩላቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶች ዘመኑን የዋጀ ጠቀሜታ እንዲሰጡ የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል። በተለይም በሀገር በቀል ዕውቀቶች ላይ ሳይንሳዊ ጥናት ተደርጎባቸው በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ “ምሁራን የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው” ነው ያሉት።
ሀገር በቀል ዕውቀቶች የማኅበረሰቡ አስተሳሰብ መገለጫ፣ የፍልስፍና እና የኪነ ጥበብ መሠረት በመሆናቸው ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፎረም መመሥረት ማስፈለጉን ገልጸዋል። በተመሰረተው ፎረም 13 ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት የተካተቱ ሲሆን ከእነዚህም ሦስቱ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም የሀገር በቀል ዕውቀትን በትምህርት ዘርፉ በማካተት አዲሱ ትውልድ እንዲረዳቸው ምሁራኑ ርብርብ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ሽመልስ ዘውዴ (ዶ.ር) ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለቴክኖሎጂው ዘመን ምቹ እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ለመወጣት መዘጋጀቱን ተናግረዋል:: በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በአሥተዳደራዊ ሥራ፣ በጤና እና በሌሎች ዘርፎች ያሉ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ጥቅም ላይ ማዋል ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል። እነዚህ ዕውቀቶች እንዳይዘነጉ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነት በመጨመር አዲሱ ትውልድ አበልፅጎ እንዲጠቀምባቸው የማስገንዘብ ሥራ ይሠራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል::
የሀገር በቀል ዕውቀት በጠበብት ወይም የአካባቢ ባለሙያዎች የተያዘ ዕውቀት ነው። የዕውቀቱ ባለቤቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ታቅፈው የሚኖሩ በመሆኑ በግል የያዙት ዕውቀት የማኅበረሰብ ዕውቀት አካል ነው። ይህ ዕውቀት የአካባቢውን ማኅበረሰብ፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ አያያዝ እና ጥበቃ ሥርዓት የሚጠቁም ሲሆን፣ ዕውቀቱ በብዙኃኑ ሲሰርፅና ሲስፋፋ ወደ ተቋማዊ የማኅበረሰብ ዕውቀት የመሸጋገር ዕድል አለው። ማኅበረሰቡ ዕውቀቱን ቀስ በቀስ የጋራ ዕውቀት ስለሚያደርገው በአንድ የአካባቢ ጠበብት ብቻ የተያዘ ዕውቀት ሆኖ አይቀርም።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም