(ልብወለድ)
ደራሲ – ቲሞቲ ሻይ አርተር
ተርጓሚ – አባትሁን ዘገየ
ቤቱን የዝምታ፣ የትካዜ፣ የጭንቀት፣የሀዘን… ድባብ ውጦታል፡፡ አስፈሪውን ድባብ የፈጠረው የሟቿ አስክሬን በልጆቿ መሀል ተጋድሞ ይታያል፡፡ በመጠጥ ሱስ የተጠመደችው እናታቸው ዛሬም እንደ ሁል ጊዜው አብዝታ በመጠጣቷ ሰክራ ከቤታቸው በር አካባቢ ድንገት ወድቃ በመሞቷ ሕፃናት ልጆቿ ያደርጉት ግራው እንደገባቸው ድንጋጤ፣ ፍርሀት፣ ሀዘን … አጥንታቸው ድረስ ዘልቆ እየተሰማቸው ቁጭ እንዳሉ አስክሬኑን ከበው በእንባ ጭጋግ በተሞሉ ዓይኖቻቸው ያስተውላሉ፡፡
መጽሐፉ፣ “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” እንዲል ሞት የሰው ልጆች እጣ ፈንታ በመሆኑ የሁሉንም ቤት ማንኳኳቱ የነበረ፣ ያለ እና የሚኖር ቢሆንም ሟቿ ወይዘሮ ግን ሁል ጊዜ እየሰከረች በሕፃናቱ፣ በወንዱ፣ በሴቱ ስትናቅ፣ ስትዋረድ፣ ስትሸማቀቅ ኖራ ድንገት በተጠናወታት የመጠጥ ሱስ ምክንያት በመሞቷ ሞቷ “ከሞቱ አሟሟቱ” ይሉት ዓይነት ነገር ሆኖባቸው ይቁለጨለጫሉ፡፡
ለወይዘሮዋ ቅንጣት ክብር ኖሮት የማያውቀው ያሰፈሩ ነዋሪም በሕልፈቷ ያዘነ በመምሰል ከንፈሩን መምጠጥ ይዟል፡፡ አንዳንድ በልጆቹ ያለ እናት መቅረት ያዘኑ የጐረቤት ሰዎች መናኛም ቢሆን ልብስ አምጥተው አስክሬኑን አልብሰውታል፡፡ ለልጆቹም ምግብ ቢጤ አምጥተውላቸዋል፡፡
ከሟቿ ሦስት ልጆች የአሥራ ሁለት ዓመት ዕድሜ ያለው ታላቁ ልጇ ያገኘውን ሥራ ሠርቶ ለዕለት ጉርሱ የሚሆን ገቢ ማግኘት የሚሳነው አይመስልም፡፡ ባሥር እና ባሥራ አንድ ዓመት ዕድሜ መካከል የምትገኘው የእሱ ታናሽም ብትሆን ንቁ እና ቀልጣፋ ቢጤ ናት፡፡ የሁለቱም ታናሽ ማጄ ግን ከሁለት ዓመት በፊት ከመስኮት ወድቃ አከርካሪዋ ክፉኛ በመጐዳቱ የአልጋ ቁራኛ ሆናለች፡፡ ይባስ ብሎም እናቷን ድንገት በማጣቷ የመኖር ተስፋዋ የጨለመባት ምስኪን ናት፡፡ እውነታው ይህ ቢሆንም ከሰፈሩ ነዋሪዎች አንዱ ከሚስቱ ጋር መክሮ በመስማማቱ ቅድሚያ ርዳታ የሚያሻትን ማጄን ቸል በማለት ሠርቶ መኖር የሚችለውን የሟቿን የበኲር ልጅ ዮሐንስን በርዳታ ስም ሊወስደው ወስኗል፡፡ የዮሐንስን ታናሽም ለራሱ ጥቅምም ቢሆን ወስዶ ሊያሳድገው ፈቃደኛ የሆነ ሰው ተገኝቷል፡፡ ሆኖም ማጄን የአካል ጉዳቷን በማየት የሚረከባት ጠፋ፡፡ በደረሰባት ጉዳት የተነሳ የሚፈልጋት እንደሌለ የተረዳችው ማጄ በትንሽዬ ፊቷ ላይ ጥልቅ የሀዘን ስሜት እየተነበበባት በእንባ ጭጋግ ውስጥ የእናቷን አስክሬን እየተመለከተች በሀሳብ ትባዝን ይዛለች፡፡
“ስለማጄ ማንም ሊጨነቅ አይገባም፡፡ ወደ ድሆች ቤት ውሰዷት!” አለ ቆመው ከሚመለከቷት ሰዎች አንዱ ጭካኔ በተሞላበት ሻካራ ድምፅ፡፡
“የድሆች ቤት እኮ ለታመመ ሕፃን የሚሆን አይደለም፤ አስቀያሚ ነው” ሲል መለሰ በሁኔታው ያዘነ አንድ ሰው፡፡
“ቤቱ ላንተ ወይም ለእኔ ልጆች ርግጥ ነው አይሆንም፡፡ ሆኖም ለዚች ምስኪን የተቀደሰ ቦታ ነው፤ ንፅህናዋ ተጠብቆ፣ ተስማሚ ምግብ እየተመገበች፣ እየታከመች የምትኖርበት ቅዱስ ቦታ ነው፡፡ ከነበረችበት አንጻር ሲታይ በርግጥም ግሩም ቦታ ነው፡፡ አንድ ሌላ ሰው ጉዳዩን አቃልሎ ተናገረ፡፡
**
ሴትዮዋ በሞተች በሁለተኛው ቀን የቀብሯ ሥነ – ሥርዓት ተፈጸመ፡፡ ከቀብሩ በኋላ የማጄን ወንድም እና እህት ቀደም ሲል ቃል የገቡት ሰዎች ወሰዷቸው፡፡ ባንጻሩም ማጄ ብቻዋን ቀረች፡፡
“ማጄን እዚህ ብቻዋን ትቶ መሄድ በእሷ ላይ መፍረድ ወይም መጨከን ነው” አለ አንደኛው አጠገቡ ወደ ቆመች ሴት እየተመለከተ፡፡
“ወደ ድሆች ቤት ወሰዷት፤ ከእሱ የተሻለ አማራጭ የላትም!” ወይዘሮዋ ወደ ሰውየው እየተመለከተች መለሰችለት፡፡
ሰውየው ለደቂቃዎች ቆሞ ሲያስብ ቆየና በረዥሙ ተነፈሰ፡፡ ከዚያም ልጅቷ ወደተኛችበት ጐጆ ሄደ፡፡ ማጄ በብዙ ትግል እና ስቃይ ከተኛችበት ቀና አለችና አልጋው ላይ ተቀመጠች፡፡
ከዚያም ሰዎች ከደቂቃዎች በፊት ወጥተው የሄዱበትን በር ትመለከት ጀመር፡፡ በሩን ባስተዋለች ቁጥር ምንነቱን በውል ያላወቀችው ፍርሀት እና ሽብር ይንጣት ገባ፡፡ ከሲታ ነጭ ፊቷ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ገረጣ፡፡
ከዚያም ያለ የሌለ አቅሟን አሟጣ በኃይል ተነፈሰችና፣ “ኦ! አቶ ቶምሰን! እባካችሁ እዚህ ብቻየን ትታችሁኝ አትሂዱ! ስትል ጮኻ ተማፀነች፡፡
“አይደለም የእኔ ውድ ልጅ!” አለ አቶ ቶምሰን ወደ አልጋዋ እያመራ ደግነቱን አግዝፎ በሚያሳይ መልካም ድምፅ፡፡ ከዚያም ወደ እሷ ዝቅ ብሎ፣ “ብቻሽን አንተውሽም” አላት፡፡ በመቀጠልም የጐረቤት ሰዎች ካመጡላት ጨርቅ ንጹሑን መርጦ ጠቀለላትና በጠንካራ እጆቹ አቅፎ ካልጋዋ አንስቶ በቤቱ እና በደሳሳው ጐጆ መሀል በሚገኝ መሿለኪያ ይዟት ሄደ፡፡
ከደረቱ አስጠግቶ አቅፎ እንደያዛት ቤቱ ደረሰ፡፡ ባለቤቱ የምታየውን ባለማመን “ምንድነው ይዘህብኝ የመጣኸው?!” ስትል ጮሀ ጠየቀችው፡፡
“ትንሽ ታገሽኝ! ስለሁሉም ነገር በቂ ማብራሪያ እሰጥሻለሁ” ካንቺ የሚጠበቀው ትዕግሥት እና ደግነት ብቻ ነው” አላት፡፡ ጆይ ቶምሰን ይህን ተናግሮ የቤቱን የመጀመሪያ ክፍል አልፎ በመሄድ ልጅቱን አልጋ ላይ አጋደማትና በቁጣ ወደምትትንቀለቀለው ሚስቱ ሄዶ ፊት ለፊቷ ቆመ፡፡
“ያቺን በሽተኛ ቀበጥ ልጅ ቤት ድረስ ይዘህብኝ መጣህ?! እኔ ይሄን አላምንም! እኮ እንዴት?!… ለምን?!…” ራሷን መቆጣጠር እስኪሳናት ድረስ የቁጣ ነባልባል ፊቷ ላይ እየነደደ ደጋግማ ጠየቀችው፡፡
“አንዳንዴ የሴቶች ልብ በጭካኔ ብዛት ካለትም የጠነከረ እንደሚሆን እገነዘባለሁ” አለ ጆይ ለስለስ ባለ ድምፅ፡፡ ሴት ልጅ አልፎ አልፎም ቢሆን እንዲህ ዓይነት የጭካኔ ባህርይ እንደሚንፀባረቅባት ከልምድ የሚያውቀው ጆይ ቶምሰን ሚስቱ እንዲህ እንደዛሬው በቁጣ በምትገነፍልበት ጊዜ ቁጣዋ እስኪበርድላት ድረስ ዝም ማለትን ይመርጣል፡፡ ሆኖም ዛሬ ለስለስ ባለ ድምፅም ቢሆን ምላሽ ሰጣት፡፡
“ሴቶች የእናንተን የወንዶችን ግማሽ ያህል እንኳን ጨካኞች አይደለንም” አለች ባለቤቱ ወይዘሮ ቶምሰን ባሏን እያስተዋለች፡፡
“ በቀብር ሥነ- ሥርዓቱ ላይ ሴቶች በዚች ምስኪን ሕፃን ላይ ፊታቸውን ሲያዞሩባት እና በዚያ ያረጀ ጐጆ ብቻዋን ትተዋት ሲሄዱ አስተውያለሁ” ሲል ስለሴቶች ጨካኝነት በምሳሌ ሊያስረዳት ሞከረ፡፡
“ዮሐንስ እና ካቴ የት ነበሩ?” ባለቤቱ ወንድም እና እህቷ የተዋትን ሌላ ማን ሊጨነቅላት ይችላል” በሚል ስሜት ባሏን ጠየቀችው፡፡
“ጆንስ ዮሐንስን ጋሪው ላይ አስቀምጦ ይዞት ሄደ፡፡ ካቴ ደግሞ ከወይዘሮ ኤሊስ ጋር ሄደ፡፡ ሆኖም ማንም ምስኪኗን ማጄን ሊወስድ አልፈለገም፤ በህመሟ የተነሳ፡፡ ሁሉም ወደ ድሆች ቤት ወሰዷት እያለ ነው ሲጮህ የነበረው…”
“እና አንተ ለምን እንድትሄድ አልተውሀትም? ወደዚህ ያመጣሀት ለምንድ ነው?”
“ወደ ድሆች ቤት ለመሄድ መራመድ አትችልም፡፡ ሰው አቅፎ ሊወስዳት ግድ ይላል፡፡ የእኔ እጆች ደግሞ እሷን ለማቀፍ ጠንካሮች ናቸው፡፡”
“ታዲያ ለምን ወደ ድሆች ቤት አትወስዳትም? ወደዚህ ለምን አመጣሀት?” ሚስቱ በጥያቄ አጣደፈችው፡፡
“ወደዚያ ለመሄድ የቤቱ ባለቤቶች ፈቃድ መገኘት አለበት? ሊቀበሏት ፈቃደኛ መሆናቸው ሳይረጋገጥ እሷን ይዞ መሄድ ተገቢነት የለውም፡፡”
“እና መቼ ነው ሄደህ ፈቃደኛ ስለመሆናቸው የምትጠይቃቸው?” ትዕግሥት ባጣ ስሜት ጠየቀችው፡፡
“ነገ!” ሲል መለሰላት፡፡
“ለምን እስከ ነገ ትጠብቃለህ? ዛሬ ጠይቀህ፣ ዛሬ አስፈቅደህ፣ ዛሬ ወስደህ ለምን አታስገባትም?”
“ይህቺን እናቷን በሞት የተነጠቀች ህመምተኛ ህፃን ላንዲት ሌሊት ቤታችን ብናሳድራት ምን ችግር አለው? ፈጣሪም ቢሆን ለህፃናት ርህራሄን፣ ደግነትን… አትንፈጓቸው፤ እኔም ዋጋችሁን አልነፍጋችሁም ነው የሚለው፡፡ እናም ይህን መልካም ተግባር ፈጽመን ከፈጣሪ ሞገስ ብናገኝ ምናለበት?…” ጆይ ሚስቱን ሊያሳምን ጣረ፡፡
አቶ ጆይ የልጅቷ በሰዎች ዘንድ ይህን ያህል መጠላት እና መገፋት ልቡን ክፉኛ ነካው፡፡ እናም ሳያስበው፣ “ለምን!… ለምን?!… በዚች ምስኪን ፍጡር ይሄን ያህል ሁላችሁም ትጨክኑባታላችሁ?!” ሲል ከጣሪያ በላይ ጮኾ ጠየቀ፡፡ ራሱን መቆጣጠር ተስኖት በከፍተኛ የሀዘን ስሜት እንደተዋጠ ጮኾ ሁሉንም እንዲህ ሲወቅስ ዓይኖቹ እምባ አጋቱ፡፡ ሆኖም እምባውን ሚስቱ እንድታይበት ስላልፈለገ ፊቱን ዞረና ጀርባውን ሰጣት፡፡ በባሏ ሁኔታ የተደናገጠችው ወይዘሮ ቶምሰን የሰናፍጭ ታህልም ብትሆን ርህራሄ ያደረባት መሰለች፡፡
“እስኪ ተመልከቻት!… እስኪ ስለ እሷ መልካም ነገር ተናገሪ!… እናቷን አጥታ፣ ጤና አጥታ፣ ሰው አጥታ… ብቻዋን የቀረች ምስኪን ስለ መሆኗ እስኪ አስቢ!… ስቃይዋ፣ ህመሟ፣ በሕይዎቷ የሚያጋጥማት የልብ ስብራት… እስኪ ይህን ሁሉ አስቢው!“ አለ ጆይ በሀዘኔታ ማጄ ወደተኛችበት ክፍል እየተመለከተ፡፡
ወይዘሮ ቶምሰን ቃል አልተነፈሰችም፡፡ በዝምታ ዓይኖቿን ማጄ ወደተኛችበት ክፍል ወርወር አደረገችና በሩን ገፋ አድርጋ ገባች፡፡ ጆይ ሚስቱ ለምስኪኗ ህፃን ርህራሄ እንዳደረባት ስለተገነዘበ አልተከተላትም፡፡ ከሕፃኗ ጋር ብቻዋን መተው የተሻለ መስሎ ስለተሰማው ቆሞ ወደበሩ ይመለከት ጀመር፡፡ ጥቂት ቆሞ እንደቆየ ከቤቱ አጠገብ ወደምትገኘው ሱቁ ሄደና የቀኑ መምሸት እስኪገላግለው ድረስ በዚያው ቆየ፡፡
ምስኪኗ ማጄ ወደተኛችበት ክፍል ዞሮ ሲመለከት በመስኮት ብርሃን አየ፡፡ ብርሃኑ ትኩረቱን ሳበውና ‘አሁን ነገሮች ወደ መልካምነት ተቀይረዋል’ ሲል አሰበ፡፡ ይህን እያሰላሰለ ዓይኑን ከብርሃኑ ላይ ሳይነቅል ወደ ህፃኗ አመራ፡፡
ማጄ ትራስ ደገፍ ብላ እንደተጋደመች ብርሃኑ ፊቷ ላይ አርፎ ትታያለች፡፡ ወይዘሮ ቶምሰን አልጋው አጠገብ ተቀምጣ ታወራታለች፡፡ ሆኖም ፊቷን ወደ ህፃኗ አዙራ ስለተቀመጠች ስሜቷን ከፊቷ ማንበብ አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ፣ አቶ ቶምሰን ከወይዘሮ ቶምሰን ጋር እንደተግባባች በደስታ ከበራው የህፃኗ ፊት ላይ መገንዘብ ቻለ፡፡ የህፃኗ ዓይኖች ከሚስቱ ፊት ላይ እንዳተኮሩ ተመለከተ፡፡ ማጄ ወይዘሮ ቶምሰንን እየተመለከተች በዝቀተኛ ድምፅ የሆነ ነገር ስታወራ ቆይታ ሸክሙ ከላዩ ላይ እንደወረደለት ሰው ተገላገልሁ በሚል ስሜት በረዥሙ ተነፈሰች፡፡
ጆይ ክፍሉ ውስጥ እንደገባ በቀጥታ ወደ ማጄ አልሄደም፡፡ በእሷ ጉዳይ አስተያየትም ቢሆን መስጠት እንደሌለበት አሰበ፡፡
“ራት በምን ያህል ጊዜ ሊደርስ ይችላል?“ ጆይ ጠየቀ፡፡
“ምንም ያህል ጊዜ አይቆም” ሚስቱ ቀልጠፍ ብላ ከቁጣ በራቀ ድምፅ መለሰችለት፡፡
ጆይ እጆቹን እንዲሁም ፊቱን በመታጠብ አቧራውን እና ድካሙን ካራገፈ በኋላ ወደ ማጄ አልጋ አመራ፡፡ ምስኪኗ ማጄ በፍቅር፣ በክብር፣ በተስፋ ተሞልታ ተመለከተችው፡፡ አስተያየቷ የልብ ምቱን እንዲፈጥን አደረገው፡፡ በመገረም ስሜት ዓየት አደረጋትና አጠገቧ ቁጭ ብሎ ያስተውላት ገባ፡፡ ባስተዋላት ቁጥር ውበቷ አየተገለጠለት ይሄድ ጀመር፡፡ የቱንም ያህል ሀዘን፣ ጭንቀት፣ ብቸኝነት…. ዘልቆ ቢሰማትም ይህ ሁሉ ተደራርቦ የልጅነት ውበቷን ሊሸፍነው እንዳልቻለ ተገነዘበ፡፡
“ስምሽ ማጄ ነው አይደለም?” አጠገቧ ቁጭ እንዳለ ለስላሳ ሚጢጢ እጇን ይዞ ጠየቃት፡፡
“አዎ ጌታየ!” ሙዚቃዊ ቃና በተላበሰ የሚርገበገብ ድምፅ መለሰችለት፡፡
“ህመሙ ከጀመረሽ ብዙ ጊዜ ሆነው?”
“አዎ ጌታየ!” ለጥያቄው በጣፋጭ አንደበት መልስ ሰጠችው፣
“ሀኪም አላየሽም?”
“አሁን መምጣቱን ትቷል እንጂ እየተመላለሰ ይከታተለኝ ነበር፡፡”
“ አሁን ሕመም ይሰማሻል?”
“አልፎ አልፎ፤ ሆኖም አሁን ደኅና ነኝ፡፡”
“መቼ ነው አሞሽ የነበረው?”
“ዛሬ ጧት አንተ ስታነሳኝ እና ስታቅፈኝ ጐኔ እንዲሁም ልቤ ላይ ሕመም ተሰምቶኝ ነበር፡፡”
“አሁንስ አያምሽም?”
“አያመኝም ጌታየ፤ አልጋው ምቹ ስለሆነ አያመኝም፡፡”
“ራት ደርሷል!” ወይዘሮ ቶምሰን ወደ ክፍሉ እየተመለከተች ጮክ ብላ ተናገረች፡፡
ጆይ ዓይኖቹን ከሚስቱ ወደ ማጄ ወርወር አደረገ፡፡ ከዚያም በመስኮቱ ወደ ምትታየው ሚስቱ ሄደ፡፡
“ስለህፃኗ ምን ልታደርግ አስበሀል?” ወይዘሮ ቶምሰን ጠየቀችው፡፡
“ወደ ድሆች ቤት ልወስዳት ስለማሰቤ የነገርሁሽ መሰለኝ እኮ!…” በጥያቄዋ የተከፋ መሆኑን በሚገልጽ ስሜት መለሰላት፡፡
ወይዘሮ ቶምሰን ዓይኖቿን ባሏ ላይ አሳርፋ ለሰከንዶች ቆየችና መሬት መሬቱን መመልከት ጀመረች፡፡ የማጄ ነገር ዳግም ሳይነሳ ራት እየተበላ እያለ ወይዘሮ ቶምሰን ዳቦ ቆርሳ በወተት እንዲሁም ቅቤ አለስልሳ በሻይ ኩባያ አድርጋ ለማጄ ሰጠቻት፡፡ ማጄ በወይዘሮ ቶምሰን ለውጥ በጣሙን ደስ እያላት የተሰጣትን ዳቦ በላች፡፡
“ይጠፍጣል?” ወይዘሮ ቶምሰን ማጄን ጠየቀቻት፤ ምግቡን እንደወደደችው ካበላሏ ተገንዝባ፡፡
ህፃኗ በደስታ ብዛት መናገር ተሳናትና ዝም ብላ ወደ ወይዘሮ ቶምሰን ትመለከት ጀመር፡፡ በነጋታው ጧት ቁርስ እየተበላ፣
“ላንድ ወይም ለሁለት ቀን እዚሁ ትቆይ፤ በጣም ደካማ ናት” አለች ወይዘሮ ቶምሰን ወደ ማጄ እየተመለከተች፡፡
“መልካም ፈቃድሽ ከሆነ ደስ ይለኛል” ጆይ መለሰላት፡፡
“ይህቺን ምስኪን ላንድ ወይም ለሁለት ቀን መታገስ የሚሳነኝ ጨካኝ ሰው አይደለሁም፡፡”
በዚያን ዕለትም ሆነ በተከታዮቹ ቀናት ጆይ ወደ ድሆች ቤት ሳይሄድ ቀረ፤ ወይዘሮ ቶምሰንም ጥያቄ አላነሳችበትም፡፡
የማጄ ጨዋነት፣ ደግነት፣ ትህትና… የአቶ ጆይን ቤት በፍቅር እና በደሰታ ሞላው፡፡ የእንጨት ጋሪ እየሠራ በመሸጥ የሚተዳደረው እና ማጄ ከመምጣቷ በፊት ከሚስቱ ጋር በሆነ ባልሆነው ይጣላ የነበረው አቶ ቶምሰን በቤቱ ሰላም መስፈኑን ሲያይ ፈጣሪ ማጄን የላከለት ያለምክንያት እንዳልሆነ ያስብ ጀመር፡፡ ማጄ ፍቅርን፣ በረከትን፣ ሰላምን ይዛለት እንደመጣች በማሰብ በስስት ሲያያት ወይዘሮ ቶምሰንም የባሏን ስሜት በመጋራት ማጄን በፍቅር እና በእናትነት ዓይን ታያት፣ ትንከባከባት ጀመር፡፡ ለማጄ ፍቅር በለገሰቻት፣ በእናት ዓይን ባየቻት፣ በተንከባከበቻት መጠን ውስጧ በሀሴት እየተሞላ በፍቅር ኃያልነት እየተደመመች ለማጄ አንዲት እናት ለልጇ ልታደርግላት የሚገባትን ፍቅር እና እንክብካቤ እስከ መጨረሻው ሳትነፍጋት ልትይዛት ደጋግማ ራሷ ለራሷ ቃል ገባች፡፡
በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም