የስምንት ዓመቷ ታዳጊ በተለያዩ ሃገራት ስትዘዋወር በድሮን የቀረፀችውን ተንቀሳቃሽ ምስል በፊልም ፊስቲቫል ላይ አቅርባ ከመሸለሟ ባሻገር በዓለም የድንቃድነቅ መዝገብ ስሟ ሊሰፍር መቻሉን ዩፒ አይ ድረ ገጽ አስነብቧል::
በአሜሪካ ኢንዲያና ግዛት “ኢቫንስቪል ዴይ” በተሰኘ ትምህርት ቤት የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ናት፤ ሉዊዛ ሮዬር:: የስምነት ዓመቷ ታዳጊ ለጉብኝት ወደ አውሮፓ፣ ጃፓን፣ አውስትራሊያ እና ደቡብ ኮሪያ ተጓጉዛለች::
በደረሰችባቸው ከተሞች እና በጐበኘቻቸው አካባቢዎችም የማረካትን በሰው አልባ በራሪዋ ካሜራ /ድሮን/ መቅረጿን ተናግራለች:: የቀረፀችውን ተንቀሳቃሽ ምስል የተመለከተችው መምህሯም “ኤዜድ ኢንተርናሽናል” በተሰኘ የፊልም ፌስቲቫል ላይ እንድታቀርበው ገፋፍታታለች:: ታዳጊዋም ተስማምታ ስራዋን በፌስቲቫሉ ላይ ለዕይታ አቀረበች። ይህ የሆነው በ2023 እ.አ.አ ነበር።
በፊልም ፌስቲቫሉ ላይ “ምርጥ አዲስ የድሮን አብራሪ” የሚል ሽልማት ማግኘት በመቻሏ በዕጅጉ ተደሰተች። ስራዋን ለውድድር እንድታቀርብ የገፋፋቻት መምህሯም ጥሩ ባለውታዋ መሆኗን ገልጻለች።
በተለያዩ አገራት ስትዘዋወር በውል በማታወቀው አካባቢ በአውሮኘላን ማረፊያ፣ ፎቆች በሚበዙበት እና የመብራት መስመሮች በተዘረጉበት አካባቢ በድሮን መቅረፅ አስቸጋሪ ሆኖባት እንደነበር ታዳጊዋ ገልጻለች። ያም ሆኖ አስቸጋሪውን ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ ተቀብላ ያከናወነችው ቀረፃ በፊልም ፌስቲቫሉ ገምጋሚዎች ተመርጦ ለሽልማት መብቃቷ እንዳስደሰታት አልሸሸገችም::
የዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ በዓለም በዕድሜ ትንሿ የተንቀሳቃሽ ምስል ቀራጭ “youngest- drone- vidiographer’’ በሚል ስያሜ በክብረ ወሰን መዝገብ ስሟን አስፍሮ የምስክር ወረቀት ሊሰጣት መቻሉንም ድረ ገጹ አስነብቧል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም