“ጨለማዋ”ን አፍሪካ ከኋላቀርነት እና ከድህነት አረንቋ ለማውጣት በሚል ሽፋን አውሮፓውያን በአፍሪካ ላይ በዓለም ትልቁን የወንጀል ደባ ፈፀሙ። በ1877 ዓ.ም በጀርመኗ በርሊን ከተማ አፍሪካን ለመቀራመት አሜሪካን ጨምሮ ዐሥራ አራት የአውሮፓ ኃያላን ሀገራት መከሩ። ለሦስት ወራት ከመከሩ በኃላ በአጭር ጊዜ አፍሪካን ወርረው በቀላሉ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በእጃቸው አስገቡ።
ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዝን አንበርክካ በማሸነፍ የአፍሪካ የነፃነት ምልክት ሆና ራሷን አስከበረች። በአፍሪካውያን ዘንድ ነጭን የበላይ እና አይሸነፌ አድርጎ የማየት ለረጅም ዘመን የዘለቀውን የተሸናፊነት ስነልቦና ሰበረች። “ዘ ባትል ኦፍ አድዋ” በተሰኘ መፅሐፉ ራይሞንድ ጆናስ “የአድዋ ድል፣ ‘ሁሉም የአፍሪካ አገራት በቅኝ ግዛት ሥር ይጠቃለላሉ’ የሚለውን የአውሮፓዊያን የማይናወጥ እምነት የፈተነ እና ጥያቄ ውስጥ የጣለ ክስተት ነበር” ሲል የፃፈውን ነጥብ ልብ ይሏል!
ይህ ጥቁር ሕዝብ ነጭን በጦር ግንባር ገጥሞ የማሸነፉ ዜና በዓለም ሲሰማ ለጭቁን ሕዝቦች የምስራች ለቅኝ ገዢዎች ደግሞ መርዶ ነበር። በተለይም ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ መወለድ ገፊው ምክንያት የአድዋ ድል ነው።
ኢትዮጵያ ለነፃነቷ ያሳየችውን ተጋድሎ በየአጋጣሚው አድናቆታቸውን ከመግለፅ ተቆጥበው የማያውቁት ከአፍሪካ ስመ ጥር እና ተፅዕኖ ፈጣሪ መሪዎች አንዱ የጋናው ክዋሜ ንክሩማህ ይጠቀሳሉ። በ1952 ዓ.ም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የክዋሜ ንክሩማህን ሀገር ጋናን በይፋ በጎበኙበት ወቅት የጋናው ፕሬዝዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያን እንዲህ ነበር የገለጿት፣
“ክቡርነትዎ፣ የእርስዎ ጉብኝት በእያንዳንዱ ጋናዊ ልብ ውስጥ የጫረውን ክስተት፣ መንፈስ እና ስሜት ብቁ በሆኑ ቃላት ለመግለፅ አልችልም። ኢትዮጵያ በአፍሪካ እንደ አንድ ጥንታዊ እና ነፃ ሀገር ሆና እና በአህጉራችን ቀጣይነት ያለው ነፃ ሀገር ሆና በመኖሯ ምክንያት እንደ አንድ ሕዝብ ሁልጊዜ በእኛ አዕምሮ ውስጥ እንደ አንድ ፖለቲካዊ መነሳሳት ምልክት ሆና ትኖራለች። ኢትዮጵያ በእኛ አዕምሮ ውስጥ የአፍሪካ ነፃነት፣ አፍሪካዊ ሉዐላዊነት፣ ለአፍሪካ ክብርና በራስ መተማመን አንድምታ አላት። ነፃ ባልነበርንበት ጊዜ እንኳ ነፃነቷን እና አንድነቷን ለመጠበቅ ኢትዮጵያ ያደረገችው ትግል በእኛ ዘንድ እንደ ራሳችን ትግል ተደርጎ ይታሰብ ነበር። ኢትዮጵያ ነፃ ሆና እስከኖረች ድረስ እኛም ነፃ መሆን የምንችልበት ተስፋ መኖሩ ሁልጊዜ ይሰማን ነበር።”
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መፈጠርን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኋላ ስንመለከት የፓን አፍሪካ ንቅናቄ ረጅም የትግል ውጤት ሆኖ እናገኘዋለን። ንቅናቄው በዋናነት የተወለደው ከአህጉሪቱ ውጭ በአሜሪካ፣ በካሪቢያን እና በአውሮፓ በሚኖሩ ዲያስፖራዎች አነሳሽነት ነው። የመጀመሪያው የንቅናቄው ጉባኤ የጥቁር ሕዝብ ብዝበዛ፣ ዘረኝነት እና ለጥቁር ሕዝብ ክብር እንዲሁም መነሳት አፅንኦት ሰጥቷል። መሪዎቹም ከአሜሪካ ዲ ቦየስ እና ከካሪቢያን ፓድሞር ይጠቀሳሉ።
የመጀመሪያው የፓን አፍሪካ ጉባኤ በእንግሊዝ መዲና ለንደን 1892 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን ተከትሎም በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ እና በኒውዮርክ ተካሂደዋል። ከሁሉም እጅግ ወሳኙ ስብሰባ እና ንቅናቄው ጫፍ የደረሰበት ወቅት በ1937 ዓ.ም በማንቸስተር የተካሄደው አምስተኛው የፓን አፍሪካ ጉባኤ ነበር። ጉባኤው ከበፊቶቹ በሦስት መሰረታዊ ሁኔታዎች ይለያል። ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ እና ከአፍሪካ የመጡ ብዙ የመብት ተሟጋቾች የተሳተፉበት ነበር።
የመጀመሪያው እንደ ኬንያታ እና ንክሩማህ ያሉ ታላላቅ የአፍሪካ መሪዎች ተገኝተው ንቁ እና ወሳኝ ተሳትፎ ያደረጉበት ነበር። ጉባኤው አፍሪካ ውስጥ ለሚካሄደው የነፃነት ትግል በደንብ የተደራጀ፣ ጠንካራ ንቅናቄን እንደ ዋነኛ ጉዳይ ማድረግን አፅንኦት የሰጠ ነበር።
ፓን አፍሪካኒዝም ከካሪቢያን እና ከአሜሪካ ተሻግሮ አፍሪካውያን ብሔርተኞች ቅኝ ግዛትን የሚፋለሙበት ዋና መሳሪያ ሆነ።
የፓን አፍሪካ ንቅናቄ የተጠናከረው ጋና የመጀመሪያዋ ነፃነቷን ያገኘች የአፍሪካ ሀገር በሆነችበት ወቅት ነበር። ንክሩማህ በ1951 ዓ.ም በጋና መዲና አክራ ውስጥ ጉባኤ በተዘጋጀበት ወቅት በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ገና የቅኝ ግዛትን እየታገሉ ነበር። የአክራው ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር ብሔርተኞችን አንድ ላይ ያሰባሰበ ሲሆን ቅኝ ግዛትን በመታገል ሂደት ውስጥ ትብብር እና አንድነት የጉባኤው ዋና ጭብጥ ነበር።
የአክራው ስብሰባ ንክሩማህ አጥብቆ የሚደግፈውን በፓን አፍሪካ ማዕቀፍ ውስጥ ለብሔር ንቅናቄዎች ጠቃሚ የሆነ የስነ ልቦናዊ፣ ፖለቲካዊ እና ተግባራዊ እመርታ አስገኝቷል። እንዲሁም አክራ ለመጡት ብሔርተኛ መሪዎች የአንድ አፍሪካ መንግሥት መኖር ቅኝ ግዛትን ለመታገል እና ከነፃነት በኋላም ለምጣኔ ሀብታዊ እድገት እና ለፖለቲካዊ ውህደት ቁልፍ መሆኑ ግልፅ የሆነበት ነበር።
ከአክራው ስብሰባ አራት ዓመታት በኋላ በ1955 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ በፓን አፍሪካኒዝም በሚመራ የብሔርተኝነት ትግሎች ነፃነታቸውን ባረጋገጡት የአፍሪካ ሀገሮች (ደቡባዊ የአፍሪካ ሀገሮችን ሳይጨምር) አማካይነት በአዲስ አበባ ከተማ ተመሰረተ። በደቡባዊ የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ ያለው ቀሪው የፀረ ቅኝ አገዛዝ እና የአህጉራዊ ውህደት ትግል በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ድጋፍ ሥር ነፃነታቸውን ባገኙ ሀገሮች ኃላፊነቱ ተወሰደ።
ከአዲስ አበባው የድርጅት ምስረታ ጉባኤ በፊት በሁለት ዋና ዋና ጥያቄዎች ዙሪያ በመላው አፍሪካ ክርክሮች ተደርገው ነበር። አንደኛው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንደተመሰረተ ሙሉ የሆነ አህጉራዊ የፖለቲካ ውህደት መመስረት ወይም በቅድሚያ አዳዲስ ሀገራትን በማጠናከር እና ከዚያም ንዑስ ቀጣናዊ ምጣኔ ሀብታዊ ቡድኖችን በማቋቋም ቀስ በቀስ ውህደቱን ማሳካት ይሻላል? የሚል ነበር። ሁለተኛው ደግሞ ልማትን በመንግሥት በሚመራ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ዕቅድ በኩል ቢፈፀም ይሻላል? ወይስ የውጭ ኢንቨስትመንት ዋነኛውን ሚና በሚጫወትበት አግባብ በነፃ እና በግልጽ ገበያዎች ቢመሰረት እና ቢመራ ይሻላል? የሚሉ ሁለት ጥያቄዎች ለክርክር የቀረቡበት ነበር።
በእነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያም ሁለት የሚቃረኑ እሳቤ ያላቸው ሀገራት (ቡድኖች) ነበሩ፣ የካዛብላንካ እና የሞኖሮቪያ ቡድኖች። በካዛብላንካው ቡድን በማኅበራዊ ዕቅድ ላይ የተመሰረተ ልማትን የሚደግፍ ሲሆን የሞኖሮቪያው ቡድን ደግሞ ገበያ መር ልማትን ይደግፋል። በተጨማሪም ሁለቱ ቡድኖች በውጭ ግንኙነቶች ዙሪያ ግንኙነት ማቋረጥ እና እንደገና ግንኙነት መፍጠር በሚሉ የተለያዩ መንገዶችን ያራምዱ ነበር።
ይህ ክፍፍል የአፍሪካውያንን ኅብረት እንደሚጎዳው ኢትዮጵያ አስቀድማ ስለተረዳች እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም። በወቅቱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት ከተማ ይፍሩ ኢትዮጵያ ሁለቱን ቡድኖች የማስማማትና አፍሪካውያንን በአንድ ድርጅት ሥር የማሰባሰብ ሥራ መሥራት እንዳለባት ለንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ አጥብቀው ተናገሩ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም በአቶ ከተማ ምክረ ሃሳብ ተስማምተው እንቅስቃሴዎችን ጀመሩ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለቱም ቡድኖች በተለያየ ጊዜ ባዘጋጇቸው ስብሰባዎች ኢትዮጵያ እንድትካፈል ጥሪ ቀረበላት። ቀድሞ የደረሰው ጥሪ የሞኖሮቪያ ቡድን ሲሆን በወቅቱ በአፍሪካ ከፍተኛ ተደማጭነት በነበራቸው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ሰብሳቢነት ሁሉም ወገኖች ወደ አንድ ሃሳብ እንዲመጡ በማሰብ በሞኖሮቪያ ቡድን ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ ተካፈለች፡፡ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በስብሰባው ላይ ተገኙ፡፡ ኢትዮጵያም ቀጣዩ የሞኖሮቪያ ቡድን ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ እንዲደረግ ጥያቄ በማቅረብ ተቀባይነትን እንዳገኘች የከተማ ይፍሩ ልጅ መኮነን ከተማ ባሳተመው የአባቱ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ፅፎታል።
የካዛብላንካ ቡድን አባላት ደግሞ በዚያው ሰሞን ስብሰባ ነበራቸው፡፡ የወቅቱ የጊኒ ፕሬዚዳንት አህመድ ሴኩ ቱሬ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ተደረገና ለአፍሪካውያን መለያየት እንደማይበጅና በአንድነት መቆም እንደሚሻል በመወያየት ኢትዮጵያ እና ጊኒ ቀጣዩ ስብሰባ የመላው አፍሪካውያን ስብሰባ እንዲሆን በመስማማት የጋራ መግለጫ አወጡ። በዚህም ቡድኖቹን ለማግባባት ተስማሙ፡፡ ለመሪዎቹ ሁሉ ደብዳቤ ተፃፈ፡፡ ከተማ ይፍሩም የንጉሠ ነገሥቱን ደብዳቤዎች በመያዝ በየሀገራቱ እየዞሩ መሪዎቹን የማግባባት ሥራውን በተሳካ ሁኔታ በአጭር ቀናት ውስጥ ማጠናቀቅ ቻሉ።
በመጨረሻም በግንቦት ወር 1955 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው ጉባኤ ላይ በወቅቱ ነፃነታቸውን ባገኙ 32 የአፍሪካ ሀገራት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመሰረተ፡፡ በኢትዮጵያ አስተባባሪነት ከተማ ይፍሩ የሚመራው ኮሚቴ ያዘጋጀው የድርጅቱ ፖሊሲ እና ቻርተር ፀደቀ። ሁለቱም ቡድኖች በተገኙበት ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ‘አህጉራዊ ውህደትን እንደ መሪ ርዕይ በመያዝ ቀስ በቀስ አዳዲስ ሀገራትን ማጠናከር’ የሚል አስታራቂ አማራጭን በማፅደቅ የድርጅቱ ምስረታ ዕውን ሆነ።
ድርጅቱ የአፍሪካ ሀገራትን አንድነት እና የጋራ ትብብር ማጠናከር፣ ለአፍሪካ ሕዝብ የተሻለ ሕይወትን ማረጋገጥ፣ ሀገራቱን ማስተሳሰር እና ትብብራቸውን ማፋጠን፣ የሀገራቱን ሉዓላዊነት፣ የወሰን ትስስር እና ነፃነታቸውን መጠበቅ እንዲሁም ማንኛውንም አይነት የቅኝ አገዛዝ ከአፍሪካ ምድር ማስወገድ የድርጅት መሪ ዓላማዎች እንደነበሩ ዶ/ር አብደላ ቡጅራ “አፍሪካ ፍሮም ዘ ኦኤዩ ቱ ኤዩ” በሚል ርእስ ባዘጋጁት ጆርናል (መጽሔት) ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ አፍሪካውያኑ በጋራ የሚሰባሰቡበትን መድረክ በመፍጠር ላበረከተችው ሚና ልዩ ዕውቅና ለመስጠት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጆን ኤፍ ኬነዲ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አሜሪካን እንዲጎበኙ በክብር መጋበዛቸው ይታወሳል። ኃያሏ አሜሪካም ለጃንሆይ መላውን የአፍሪካ ሕዝብ ያኮራ በደማቅ ስነ ሥርዓት የታጀበ የክብር አቀባበል ማድረጓንም ልብ ይሏል። ተወዳጁ ፕሬዝደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ንጉሡን በልዩ አክብሮት ከተቀበሏቸው በኋላ ባደረጉት ንግግር “በርካታ አፍሪካውያን ሀገራት ነፃ እንዲወጡ እና እርስ በርስ እንዲተባበሩ የሚያደርገውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ እንዲመሰረት የክቡርነታቸው አስተዳደር (የኢትዮጵያ) የጥረት ውጤት በመሆኑ አሜሪካ ልዩ የክብር እንግዳዋ አድርጋ ስትቀበልዎ በታላቅ ኩራት ነው” ነበር ያሉት።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም