ለሱዳን የተኩስ አቁም ጥሪ

0
157

በቀድሞው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሚመራው የዴሞክራሲ ደጋፊ ፓርቲዎች ጥምረት የአመራር ስብሰባ በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ውስጥ ተደርጓል።

ታጋዱም  በመባል የሚታወቀው የሲቪል ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት የለውጥ ነፃነት ኃይሎች ፣ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲሁም የማሕበራት ተወካዮች፣ አክቲቪስቶች እና በርካታ ገለልተኛ የታጠቁ ቡድኖችን ያጠቃልላል። በጉባኤው በርካታ ፖለቲካዊና ድርጅታዊ አጀንዳዎች ላይ ውይይት መደረጉን የተጋዱም ሚዲያ ገልጿል።

የጥምረቱ አመራር አካሉ ባካሄደው ስብሰባ ጦርነቱን ውድቅ በማድረግና በማስቆም፣ ዘላቂ ሰላምን  እና ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሕዝባዊ አገዛዝን በማስፈን የሚያምኑትን አባላትን በማሰባሰብ ባለፈው ታኅሳስ ወር አብዮት፣ ነፃነት፣ ሰላምና ፍትሕ በሚል መሪ ቃል ስብሰባ አካሂዶ ነበር።

እንደ ሱዳን ትሪቡን ዘገባ ከሆነ ታጋዱም የሱዳንን ወታደራዊ ጁንታ ወይም ተቀናቃኙን የፈጥኖ ደራሽን ድጋፍ ሰጪ ኃይሎችን የማይደግፉትን ሱዳናውያንን ለመወከል ይፈልጋል።

የታጋዱም ተቺዎች ደግሞ ጥምረቱን ለፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች በጣም ቅርብ ነው ሲሉ ይደመጣሉ። የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አር ኤስ ኤፍ) መሪ መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ጉብኝት ካርቱምን ከለቀቁ በኋላ ታጋዱም እና አር ኤስ ኤፍ በጥር ወር 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ስብሰባ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። በወቅቱ ጥምረቱ የሌላውን ተዋጊ ፓርቲ መሪ የሠራዊቱን ዋና አዛዥ እና የጊዜያዊ አስተዳደሩን መሪ አብደል ፈታህ አል – ቡርሃንን ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። ሆኖም አል – ቡርሃን ከታጋዱም ጋር በሱዳን ውስጥ እንደሚገናኙ በአደባባይ ተናግረዋል።

የቀድሞው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሲቪል ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች አስተባባሪ (ታጋዱም) መሪ አብደላህ ሃምዶክ በወቅታዊው ግጭት ውስጥ አድሎአዊ ውንጀላዎችን በማንሳት ገለልተኝነታቸውን አረጋግጠዋል::  ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት ከሁለቱም ወገኖች ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ስድስት መቶ የሚጠጉ ተሳታፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ከተማ የታጋዱም የመክፈቻ ስብሰባ እና ለሦስት ቀናት በቆየው ዝግጅት መክፈቻ ላይ ሃምዶክ አምስት ቁልፍ ጉዳዮችን ዘርዝዋል:: የፀጥታ ማሻሻያ፣ ሰብዓዊ ርዳታ፣ ጤና፣ ትምህርት እና ከጦርነቱ በኋላ ያሉ ዝግጅቶች  በተለይም በሰብዓዊ ጉዳዮች እና የጥላቻ ንግግሮች ላይ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ሃምዶክ የታጋዱምን የማያዳላ አቋም አፅንዖት ሰጥተው አስረድተዋል:: “ከሰማዕታት ቤተሰቦች፣ ከሲቪል እና ከወታደራዊ እንዲሁም ወደዚህ ጦርነት ሳይወድዱ ከተሳቡት ጋር እንቆማለን። ይህ መግለጫ የፀረ ጦርነት ጥምረት ከሱዳን ጦር ይልቅ ለፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ኃይሎች (RSF) ያደላል የሚሉ ውንጀላዎችን የተመለከተ ሲሆን ይህ ግንዛቤ ከጦር ኃይሉ አዛዥ ጋር ሊነጋገሩ የሚችሉትን የሰላም ድርድር በተመለከተ እንቅፋት ሆኖበታል” ብለዋሏል።

በመክፈቻው ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ዓለም አቀፍ መልዕክተኞች እና መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል። ሃምዶክ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በሱዳን ያለውን ግጭት ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀዋል።

ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው ጦርነት ያስከተለውን አስከፊ መዘዝ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር በምሬት ተናግረው የሺዎች ሕይወት መጥፋት፣ ሚሊዮኖች መፈናቀላቸውን እና ያስከተለውን ከፍተኛ ውድመት ጠቅሰዋል። የሱዳን ስደተኞችን የተቀበሉ ሀገራትን አመስግነው ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የቀድሞው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በሱዳን እየተካሄደ ያለው ግጭት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ከፍተኛ ውድመት እና የሰብአዊ መብት ረገጣ ማድረሱን አስረድተዋል። በጣም አሳሳቢው ጉዳይ  የረሃብ አደጋ እንደሆነ ተናግረው መፍትሔ ካልተበጀለት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ሊቀጥፍ ይችላል ብለዋል።

የሰብዓዊ ዕርዳታ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲደርስ በሁለቱም ወገኖች ላይ ግፊት እንዲደረግ፣ ምግብ እና መድኃኒት በሰላማዊ ሰዎች ላይ እንደ መሣሪያ መጠቀማቸውን እንዲያቆሙ ክልላዊ እና ዓለም አቀፍ ማሕበረሰቦችን በአስቸኳይ ተማጽነዋል። ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በአስቸኳይ የተኩስ ማቆም እና ወደ ሲቪል አገዛዝ ለመሸጋገር ድርድር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የታጋዱም መሪ ጦርነቱ መራዘሙ ያስከተላቸውን አስከፊ መዘዞች አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን ጦርነቱ የሰዎችን ሕይወት ከመቅጠፉ ባሻገር ለትውልድ መጥፋት እና የሱዳንን ሕዝብ ለውርደት እንደሚዳርግ ገልጸዋል። በደኅንነት ቦታ ላይ ያሉም ለግጭቱ ቀጣይነት ከመከራከር እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙም ጠይቀዋል።

በሀገሪቱ ላይ የህልውና ስጋት የሆኑት የጥላቻ ንግግሮች እያደጉ መምጣታቸውን ጠቁመው በዘረኞች ላይ ጥብቅ እና ቆራጥ ምላሽ እንዲሰጥም አሳስበዋል።

ሃምዶክ ጦርነቱን ለማስቆም እና በጦርነቱ ላይ የጋራ ግንባር ለመፍጠር የሲቪል ኃይሎች በንቃት እየሠሩ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ለተቃዋሚዎች  ማለትም ለሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄ (ኤስ ኤም ኤል)፣ የአብደልዋሂድ አል-ኑር፣ የባአት ፓርቲ፣ የኮሚኒስት ፓርቲን ጨምሮ ለተለያዩ የሲቪል እና የፖለቲካ ኃይሎች ግብዣ ቀርቧል።

ሃምዶክ የጦር ሠራዊቱ እና የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች አዛዦች ጦርነቱን ማቆም በሚቻልበት መንገድ ላይ ለመወያየት ከታጋዱም አመራር ጋር እንዲገናኙ ጋብዘዋል:: ከሄሜቲ ጋር የተደረገው ስብሰባ የእነዚህ ቀጣይ ጥረቶች አካል ሲሆን የቡርሃንን ምላሽ አሁንም በመጠባበቅ ላይ ነው።

ሃምዶክ የርዕዮተ ዓለም እና የፖለቲካ ልዩነቶችን በተሻገረ ጦርነቱን ለማስቆም እና የሱዳንን መንግሥት ህልውና ለማረጋገጥ ታጋዱም የሲቪል ኃይሎችን ወደ አንድ ለማድረግ እና ሰፊ ጥምረት ለመፍጠር ወሳኝ እርምጃን እንደሚወክል አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ማስተባበሪያው ሁሉንም ሀገራዊ ጉዳዮች ለመፍታት የጠረጴዛ ውይይት ሐሳብ ያቀረበ ሲሆን ጦርነቱን ለማስቆም እና የሱዳንን ሕዝብ ደኅንነትና ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ያላሰለሰ ጥረት ለማድረግ ቃል ገብቷል።

ከሰሞኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት  እንዳስታወቀው በሚያዝያ 2023 አጋማሽ ላይ በሱዳን ጦር ኃይሎች (ኤስ ኤፍ ኤ) እና በፈጥኖ ደራሽ የድጋፍ ሰጪ ኃይሎች (አር ኤስ ኤፍ) መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ከስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ሱዳናዊያን ቤታቸውን ጥለው ተሰደዋል።

ከፍተኛው የተፈናቃዮች ቁጥር በደቡብ ዳርፉር 11 በመቶ፣ በናይል ወንዝ 10 በመቶ እና በምሥራቅ ዳርፉር 10 በመቶ ግዛቶች ነው። የስደተኞች ድርጅት የስደተኞች መከታተያ ማትሪክስ (IOM DTM) የመስክ ቡድን አባላት እንደተናገሩት ተፈናቃዮቹ ከ12 ግዛቶች የተፈናቀሉ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ 53 በመቶው 3.6 ሚሊዮን የሚሆኑት ከካርቱም ግዛት የተፈናቀሉ ሲሆን ደቡብ ዳርፉር 14 በመቶ፣ አጅ ጃዚራህ 10 በመቶ፣ ሰሜን ዳርፉር 9 በመቶ፣ መካከለኛው ዳርፉር 4 በመቶ እና ከሌሎች ግዛቶች የተፈናቀሉ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ (ዩ ኤን ኤች ሲ አር) እንደገለጸው ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ድንበር አቋርጠው ተሰደዋል። ከእነዚህም መካከል አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ወደ ጎረቤት ሀገራት፣ 660 ሺህ ሰዎች ወደ ደቡብ ሱዳን፣ 579 ሺህ ሰዎች ወደ ቻድ እና 500 ሺህ ሰዎች ወደ ግብፅ ተሰደዋል።

እየጨመረ በሚሄደው የረሃብ እና ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት በሚቀጥሉት ወራት ከፍተኛ የሞት መጠን ይመዘገባል ተብሎ ተሰግቷል።

በመጋቢት እና ሚያዚያ ወራት 860 ሺህ የሚጠጉ ሱዳናዊያን በኮርዶፋን፣ በዳርፉር እና በካርቱም በአመጽ እንዲሁም በቢሮክራሲያዊ እና አስተዳደራዊ እክሎች ሳቢያ ሰብዓዊ እርዳታ አላገኙም ነው የተባለው።

ከሰሞኑ በአል ፋሸር እና አካባቢው በነበረው ግጭት ሰዎች ለከፋ ሰብዓዊ ችግር እየተጋለጡ ነው:: ጦርነቱ በሁሉም ሱዳናዊያን የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። የሟቾች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው። የእርዳታ ሠራተኞችም መስዋዕት እየሆኑ ነው::

የሱዳን ሕዝብ ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት ጭካኔ የተሞላበት ግፍ እየደረሰበት ነው። የሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ በሆነችው በኤል ፋሸር ደግሞ እየተባባሰ ነው:: በርካቶች ተፈናቅለዋል። የጦርነቱ መሪዎች ወደ ሰላም ካልተመለሱ በተለይ በኤል ፋሸር በሚኖሩ 800 ሺህ ሰላማዊ ዜጎች ላይ አስከፊ መዘዝ ያስከትላል ነው የተባለው።

በጦርነቱ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ የሚተማመኑበት ሰብዓዊ እርዳታ ሊያልፍ አልቻለም።

በኤል ፋሸር የተደረገው ጦርነት በሲቪሎች ላይ ያሳደረው አስከፊ ተጽዕኖ በሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት እጅግ አሳዛኝ ምሳሌ ነው። ባለፈው ዓመት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፤ ቤተሰቦች ተለያይተዋል፤ የመኖሪያ ቤቶች እና የሲቪል መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፤ ዋና ከተማዋ እና የሱዳን የልብ ምት በመባል የምትሞካሸው ካርቱም ወድማለች። ዘግናኝ ግፍ እና በደል እየተፈፀመ ነው። የአስገድዶ መድፈር፣ የማሰቃየት እና ብሔርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እየታዩ ነው:: ሱዳን ዛሬ በዓለም ላይ ትልቁ የመፈናቀል ቀውስ ማዕከል ሆናለች:: አብዛኛው ሕዝብ የጤና አገልግሎት ማግኘት አልቻለም። ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ  ሆነዋል::

በተለይ በካርቱም፣ በዳርፉር እና በኮርዶፋን የአስገድዶ መድፈር፣ የግዳጅ ጋብቻ፣ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ባርነት እና የሴቶች እና የልጃገረዶች ሕገ ወጥ ዝውውር ክስ መመዝገቡ ቀጥሏል። በተለይ በሀገር ውስጥ እና በአጎራባች ሀገራት መጠለያ ፍለጋ ጦርነት ካለባቸው አካባቢዎች በመሸሽ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ለአደጋ ተጋልጠዋል። ይሁን እንጂ የዚህ ቀውስ ትክክለኛ መጠን ገና ያልታየ ሲሆን ይህም በመገለል፣ በበቀል ፍርሀት እና በብሔራዊ ተቋማት ላይ እምነት በማጣት ምክንያት ከፍተኛ ሪፖርት አለመደረጉ ተጠቅሷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሱዳን ዳርፉር ግዛት የዘር ማጥፋት እያንዣበበ ቢሆንም የዓለም ትኩረት ግን የሩሲያ – ዩክሬን እና የእስራኤል – ሃማስ ጦርነት ላይ ብቻ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያ ለቢቢሲ ገልጸዋል። በሱዳን ኤል ፋሽር ከተማ ውስጥ ሰዎች በጎሳ ማንነታቸው ምክንያት የጥቃት ዒላማ መሆናቸውን ነው ባለሙያዋ የተናገሩት።

ሂውማን ራይትስ ወች በበኩሉ  በዳርፉር የዘር ማጥፋት ስጋት እንዳለ አስታውቋል። በማሳሊት ብሔር እንዲሁም አረብ ባልሆኑ ማኅበረሰቦች ላይ የዘር ማጽዳትና ኢሰብዓዊ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል። የመብት ጥሰቱን እየፈፀሙ ይገኛሉ የተባሉትም ተጠያቂ እንዲደረጉ መጠየቁን ቢቢሲ ዘግቧል።

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here