ግጭቱ የሕዝቡን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አደጋ ውስጥ አስገብቶታል

0
159

አማራ ክልል ሰላም ከራቀው አንድ ዓመት ሊደፍን የአንድ ወር ዕድሜ ነው የቀረው። ችግሩ ታዲያ ክልሉን ዘርፈ ብዙ ዋጋ እያስከፈለው ነው። ከምንም በላይ ደግሞ በሰሜኑ ጦርነት ከደረሰበት እጅግ ከባድ ውድመት ሳያገግም ለዳግም ግጭት መዳረጉ የክልሉን ችግር ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ችግሩን ለመቆጣጠር በሚል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዐሥር ወራት ይሆናል። እጅግ ባጠረ ጊዜ ችግሩን ለመቆጣጠር እንደሚያስችለው መንግሥት በወቅቱ በተደጋጋሚ ቢገልጽም ግጭቱ ግን እንደቀጠለ ነው።

በግጭቱ በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል፤ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፤ በዚህም ማሕበራዊ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ሕዝቡ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቷል። ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ሐሳባቸውን ለበኩር ያካፈሉት የባሕር ዳር ከተማ ኗሪዋ ደግሞ ችግር ከበረታባቸው መካከል አንዷ ናቸው። ወይዘሮዋ እንዳሉት በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ነብሰ ጡር ነበሩ። ግጭቱ በባሕር ዳር በበረታበት በዚያ ወቅት ደግሞ (ጊዜውን የጠበቀ ቢሆንም) ሌሊት ላይ ምጥ እንደመጣባቸው ነው ያስታወሱት።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ምንም አይነት የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ባለመኖሩም “ድጋሚ ላስታውሰው የማልፈልገው አስቸጋሪ ጊዜ ነበር” ይላሉ። ምንም እንኳን የእንቅስቃሴ ገደብ ቢኖርም ከጎረቤት የሚያውቁት የግል የጤና ተቋም በመኖሩ የገጠማቸውን ችግር እንደተሻገሩት ያስታውሳሉ። “እኔ ዕድለኛ ነኝ፣ ሌሎች እናቶችስ እንዴት ይሆኑ? ችግሩን የሚያውቀው የደረሰበት ነው” ብለዋል። በመሆኑም ካለፈው በመማር ሁሉም ወገን ለሰላም መስፈን የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ሌላው ከጎንደር ሐሳቡን ያካፈሉን ኗሪም የባሕር ዳሯን ነዋሪ ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ ይጋራሉ። መንገድ በመዘጋጋቱ ምክንያት የሕክምና ቀጠሮ እንዳለፈው በማንሳት በዚህም ከባድ የጤና እክል እንደገጠማቸው ነው የነገሩን።

ነዋሪው እንደሚሉት ግጭቱ የሰዎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ተፈጥሯዊ መብት ነፍጓል፤ የከተማዋን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴም በእጅጉ እንዲቀዛቀዝ አድርጎታል:: ከምንም በላይ ደግሞ ምትክ የለሹን ሕይወት ነጥቋል:: በመሆኑም ካሳለፍነው ችግር በመማር ለሰላም መስፈን ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግጭቱ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲቆም ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ሀገራት በተደጋጋሚ ጥሪ ካደረጉ ውለው አድረዋል። እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት በማመላከትም ሁሉም ወገኖች ግጭቱን በውይይት ለመፍታት ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ደግሞ ግጭቱ ያስከተለውን ውድመት በተመለከተ በተደጋጋሚ እያስታወቁ ከሚገኙ ተቋማት መካከል ዋነኛው ነው። እየደረሰ ያለው ሰብዓዊ ችግር በእጅጉ እንዳሳሰበውም በተደጋጋሚ አስታውቋል። ኮሚሽኑ ከሰሞኑም በተለይ በአማራ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተመለከተ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ኢሰመኮ በሪፖርቱ የግጭት ተሳታፊ አካላት በማናቸውም የግጭት ሂደት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊነት ሕጎች ጥሰትን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ፣ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ፣ በሲቪሎች ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡም ጥሪ አድርጓል። በግጭቱ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊነት ሕጎችን በጣሱ አካላት ላይ የወንጀል ምርመራና የክስ ሂደት እንዲጀመር  አሳስቧል።

ሀገራችን የብሔር ፌደራሊዝምን መከተል ከጀመረች ብዙ ዐሥርት ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ይህ አወቃቀር ታዲያ የከፋ መዘዝ እንደሚያስከትል በርካቶች የዘርፉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ቆይተዋል፤ ከዚህ በተጨማሪም መሰል አወቃቀር የሚከተሉ ሀገራት የገጠማቸው ስብራት ሲነገር ቆይቷል:: ለአብነትም ደቡብ አፍሪካ እና ሩዋንዳ ትምህርት የሚወሰድባቸው ሀገራት ናቸው:: ይሁን እንጂ ተግባራዊ የመፍትሔ ርምጃ ባለመወሰዱ ለዘመናት የተዘራው ብሔር ተኮር መርዝ ሀገራችንን አጣብቂኝ ውስጥ ካስገባት ውሎ አድሯል::

ግሎባል ታይምስ የተሰኘዉ ጋዜጣ ቅኝ ገዥዎች አፍሪካውያንን በብሔር እና በጐሳ ስለከፋፈሏቸው፣ ሀገር በቀል ተቋሞቻቸውን ስላወደሙባቸው እና እሴቶቻቸውን ስለሸረሸሩባቸዉ የሰከነ ሀገረ መንግሥት ለመመስረት መቸገራቸውን ያስነብባል:: አፍሪካውያን ታዲያ የራሳቸው ሀገር በቀል ፖለቲካዊ መፍትሄ ባለመሥራታቸው፣ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አህጉር ባለማቆማቸው… የእርስ በእርስም ሆነ የጎረቤት ሀገራት ጦርነት ይቀሰቀሳል ነው ያለው::

በሌላ በኩል ብሔርተኝነት በወለደው ጦስ በአንድ ጀንበር አንድ ሚሊዮን ገደማ ዜጋዋን ያጣችው ሩዋንዳ ዜጋ ተኮር መዋቅር በማቆም በእርቅ እና በብሔራዊ መግባባት አክማ ችግሯን ተሻግራለች:: ደቡብ አፍሪካም በኔልሰን ማንዴላ ፊታውራሪነት በነጮች እና በጥቁሮች መካከል የነበረውን የገዥ እና የተገዥ ግንኙነት በማረቅ በይቅርታ የሁሉንም አሸናፊነት ያረጋገጠ መፍትሄ ማምጣት ችላለች::

ሀገራችንም ታዲያ ከገጠማት ችግር ለመውጣት መሰል ተሞክሮዎችን መውሰድ እንዳለባት ነው የሚነገረው፤ የአፍሪካ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አሜሪካ እና መሰል ሀገራትም ብቸኛው የችግሩ መሻገሪያ መንገድ ፖለቲካዊ ውይይት መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ጠቁመዋል::

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here