በእግር ኳሱ ዓለም እጅግ ስማቸው ከናኘ ክለቦች መካከል ቀዳሚው ነው፤ በርካታ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ደጋግሞ በማንሳት የሚቀድመው የለም፤ በታሪክ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ወርደው ከማያውቁ ሦስት የስፔን ክለቦች ውስጥም አንዱ ነው፤ኃያሉ የስፔን ክለብ በሀብት መጠንም ፈርጣማ ከሚባሉት ክለቦች አንዱ ነው፣ በአራቱም የዓለም ማዕዘን የሚገኙ የባለተሰጥኦ የእግር ኳስ ኮከቦች ህልም እና መዳረሻ ጭምር ነው- ሪያል ማድሪድ እግር ኳስ ክለብ። ሪያል ማድሪድ ከስፔን ውጪ በርካታ ሚሊዮን ደጋፊ ያለው ቀዳሚ የዓለማችን ክለብ ነው።
የዋናዋ ከተማዋ ክለብ እ.አ.አ በ1902 ነው “ማድሪድ” የሚል ስያሜን ይዞ የተመሰረተው። ይህ ስያሜም እስከ 1920 በፈረንጆች የጊዜ ቀመር አቆጣጠር ድረስ ቀጥሏል።
የስም ለውጥ የተደረገው በንጉሥ አልፎንሶ 12ኛ ዘመን ነው። ንጉሣዊ (Royal) ከሚለው የእንግሊዘኛ ቃል በመውሰድ ከፊት “ሪያል” የሚል ተጨማሪ ቅጥያ ተሰጥቶት “ሪያል ማድሪድ” የሚል ስያሜን እንዲይዝ ተደርጓል። ክለቡም የንጉሣውያን ቡድን ነው የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል።
ከ11 ዓመታት በኋላ ግን የንጉሣውያኑ ቤተሰብ መንግሥት ሲፈርስ ክለቡ ችግር ስለገጠመው ማድሪድ ወደ ሚለው የቀድሞ ስሙ መመለሱን የስፖርቲንግ ኒውስ መረጃ ያስነብባል። በክለቡ መለያ ባጅ ላይ የነበረው የዘውድ አርማም እንዲነሳ ተደርጓል። እ.አ.አ በ1941 የስፔን የእርስ በእርስ ጦርነት ካለቀ በኋላ “ሪያል ማድሪድ” የሚለውን ስያሜ ድጋሚ አግኝቷል።
ምንም እንኳ ስፔን ውስጥ ሪያል ሶሲዳድ፣ ሪያል ቢትስ፣ ሪያል ቫላዶሊድ እና ራያል ቫልካኖ የመሳሰሉት ክለቦች ከፊት “ሪያል” የሚል ቅጥያ ቢኖራቸውም ችግሩ የፀናው ግን በኃያሉ ክለብ ብቻ እንደነበር በታሪክ ማህደሩ ተመዝግቧል። ምክንያቱ ደግሞ ከእግር ኳስም በዘለለ ፖለቲካዊ ትርጉም ስለነበረው ነው ይላል መረጃው።
በጄነራል ፍራንኮ አገዛዝ ዘመን ካታሎናዊያን ዐይናችሁን ላፈር ሲባሉ ሪያል ማድሪዶች ደግሞ አፈር አይንካችሁ የተባሉበት ጊዜ ነበር። ለዚህ ማሳያ ደግሞ አልፍሪዶ ዴስቲፋኖ በጄነራል ፍራንኮ ጎትጓችነት ለሪያል ማድሪድ እንዲፈርም መደረጉን ታሪክ ያወሳል። የቀድሞው የስፔን መሪ የሪያል ማድሪድን ስኬት የካታሎኑን ክለብ ባርሰሎናን ደግሞ ውድቀት ከሚፈልጉ ሰዎችም ቀዳሚው ነበር።
በ1980ዎች በነጭ መለያ የሚታወቀው የስፔኑ ኃያል ክለብ በርካታ ባለተሰጥኦ ወጣት ኮከቦችን በአካዳሚው በመፈልፈል ለዓለም አስተዋውቋል። በወቅቱም ያለ ተቀናቃኝ አምስት የላሊጋ፣ ሁለት የንጉሥ ዋንጫ እና ሁለት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ አሳክቷል። በ1990ዎች መጀመሪያ ግን ክለቡ የአቋም መውረድ ገጥሞት እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ።
የፈረንጆች ሚሊኒየም ከገባ ጀምሮ ግን በሳንቲያጎ ቤርናቢዮ አዲስ የእግር ኳስ አብዮት ተፈጥሯል።የቀድሞው ፖለቲከኛ ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ አዲሱ የሪያል ማድሪድ ፕሬዝደንት በመሆን ትልቅ ለውጥ አምጥተዋል። ዚነዲን ዚዳንን፣ ሊዊስ ፊጎን፣ ዴቪድ ቤካምን፣ ሮናልዶ ናዛሪዮ ዴሊማን፣ ሮቤርቶ ካርሎስን እና የመሳሰሉትን በማስፈረም ጋላክቲኮ የሚባለውን ስብስብ ፈጥሯል።
በዚህ ወቅት ክለቡ በስፔንም በአውሮፓም አስፈሪ የሆነበት ዘመን ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሪያል ማድሪድ ፈርጣማ የገንዘብ ክንዱን እና ወርቃማ ታሪኩን በመጠቀም በየጊዜው የተለያዩ ወርቃማ ባለተሰጥኦ ኮከቦችን ያስኮበልላል፤ እያስኮበለለም ነው።
በአውሮፓ ምድር የሪያል ማድሪድን ያህል በዋንጫ የተንቆጠቆጠ እና ዝነኛ የሆነ ክለብ ማግኘት ይከብዳል። 36 የላሊጋ፣ 20 የንጉሥ፣ እና 15 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ማሳካት ችሏል። በተጨማሪም ለቁጥር የሚታክቱ ሌሎች ክብሮችንም መጎናጸፉን የታሪክ ማህደሩ ያሳያል። በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ሪያል ማድሪድ 15ኛ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫውን ነው ያሳካው።
የአውሮፓ ሻምዮንስ ሊግ ውድድር በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አማካኝነት የሚዘጋጅ የውድድር መድረክ ነው። ከተጀመረ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ተሻግሯል። እ.አ.አ 1955 በቀድሞ አጠራሩ “የአውሮፓ ዋንጫ”በሚል ስያሜ ነበር የተጀመረው።
በ1992 እ.አ.አ ግን የቀድሞ ስያሜውን በመቀየር “የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ” ስያሜን በመያዝ ውድድሩ እየተከናወነ ይገኛል። ግዙፉ የእግር ኳስ መድረክ ባለፉት 21 ዓመታት ሳይቋረጥ ተከናውኗል። በመድረኩም 32 ክለቦች ይሳተፉበታል። የተሳታፊ ክለቦቹ ቁጥር ግን ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ወደ 36 ከፍ እንደሚል የአወዳዳሪው አካል መረጃ ያመለክታል።
የዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ መድረክም ከሳምንት በፊት በዌምብሌ ስቴዲየም የተደረገ ሲሆን ሌላ የፍፃሜ ጨዋታ ተመሳሳይ አሸናፊ ክለብ ተመልክተናል፡፡ ሪያል ማድሪድ የጀርመኑን ክለብ ቦርሺያ ዶርትሙንድን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ክብሩን ተጎናፅፏል።
የጀርመኑ ክለብ እ.አ.አ ከ2011/12 የውድድር ዘመን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በታላቁ መድረክ ፍጻሜ ቢደርስም የመድረኩን ንጉሥ ማስቆም ባለመቻሉ ዘንድሮም ህልሙን ሳያሳካ ቀርቷል።
የአውሮፓው ንጉሥ ክለብ በ1955/56 እ.አ.አ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የመድረኩን ዋንጫ ያሳካው። በወቅቱ በተከታታይ አምስት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳትም እስካሁንም ባለ ክብረወሰን ነው። ከፈረንጆች ሚሊኒየም ጀምሮ ባሉት አራት ዓመታትም በተከታታይ በበላይነት ዋንጫውን አሳክቷል።
ሪያል ማድሪድ ባለፉት አስር ዓመታት ብቻ አምስት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አንስቷል። ፍጻሜ ደርሶ የተሸነፈው በሦስት አጋጣሚዎች ብቻ ነው፡፡ እ.አ.አ በ1980/81 በሊቨርፑል፣በ1963/64 በኢንተርሚላን እና በ1962/63 በቤኔፊካ ተሸንፎ ዋንጫውን ማጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከእነዚህ ጊዜያት ውጪ ሪያል ማድሪድ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ደርሶ ዋንጫውን ተነጥቆ አያውቅም፡፡
በየጊዜው በርካታ ባለተሰጥኦ ተጫዋቾች የማይነጥፉበት ሳንቲያጎ ቤርናቢዮ ዘንድሮም በአስደናቂ ወጣት ኮከቦች በመታገዝ 15ኛውን የመድረኩን ዋንጫ አንስቷል። ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ደግሞ አምስተኛ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫውን ሲያነሳ ከሪያል ማድሪድ ጋር ሦስት ጊዜ እና ከኤስሚላን ጋር ደግሞ ሁለት ጊዜ የመድረኩን ዋንጫ ወስዷል።
ካርሎ አንቸሎቲ በ2013 እ.አ.አ ነበር አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆን ተክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤርናቢዮ የደረሰው፡፡ የአንጋፋውን አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲን ያህል የመድረኩን ዋንጫ ያነሳ አሰልጣኝ የለም፡፡
ካርሎ አንቸሎቲን የሚከተለው የቀድሞው ሌላኛው የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን ነው። ፈረንሳያዊው አሰልጣኝ ሦስት ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ በማንሳት ሦስታት (ሀትሪክ) ሠርቷል።
የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጉርዲዮላ እና የቀድሞው የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ሮበርት ፓይስሊ በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ጊዜ ዋንጫውን ማንሳታቸውን ታሪክ ያወሳል። ፕሬዝደንት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር እነርሱ ብቻ የሚነግሱበት ውድድር እንደሆነ ተናግሯል። “ሪያል ማድሪድ እና የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጠበቀ ወዳጅነት አላቸው፤ ተጫዋቾች ይመጣሉ፣ይሄዳሉ፤ ቢሆንም ይህ ውድድር የእኛ ነው” ብሏል ፕሬዝደንቱ።
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ኤስሚላን ከሪያል ማድሪድ በግማሽ አንሶ ሰባት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ይከተላል። ሊቨርፑል እና ባየርሙኒክ ደግሞ እኩል ስድስት ጊዜ ዋንጫውን በመውሰድ ባለታሪኮች ናቸው። የካታሎኑ ክለብ ባርሴሎና ደግሞ አምስት ጊዜ የመድረኩን ዋንጫ ማንሳቱ በታሪክ ተመዝግቧል።
የሪያል ማድሪድ ተጫዋቾች በሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች በርካታ ግቦችን በማስቆጠር የሚስተካከላቸው የለም። የቀድሞው የሎስብላንኮዎች ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ101 ጨዋታዎች 105 ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚው ባለታሪክ ተጨዋች ነው። ካሪም ቤንዜማ እና ራውልም በርካታ ግቦችን በማስቆጠር በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን የሚያገኝ፣ በበርካታ አጋር ድርጅቶች የሚታጀብ እና ከትኬት ሽያጭም ረብጣ ሚሊዮን ዩሮዎች የሚታፈስበት ውድድር በመሆኑ ተሳታፊ ክለቦች ባሳዩት አቋም ልክ ሽልማት ይበረከትላቸዋል። በዚህ ግዙፍ የአውሮፓ መድረክ ከማጣሪያው ጀምሮ ለሚሥተፉ ክለቦች የሽልማት ገንዘብ ይበረከትላቸዋል።
ዘንድሮ ከባለፉት ዓመታት አንፃር የሽልማት መጠኑ ከፍ ያለ ሲሆን አሸናፊው ክለብ ሪያል ማድሪድ 25 ሚሊዩን ዩሮ ገንዘብ ተበርክቶለታል። ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ላጠናቀቀው ለጀርመኑ ክለብ ቦርሺያ ዶርትሙንድ 18 ሚሊዮን ዩሮ፣ ግማሽ ፍፃሜ ድረስ ለተጓዙት 15 ሚሊዮን ዩሮ ገንዝበ ተበርክቶላቸዋል።:
ስፖርቲንግ ኒውስን፣ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ድረ ገጽን እና ቢቢሲ ሰፖርትን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም