ፓሪስ በጉጉት የምትጠብቀዉ

0
221

በአትሌቲክስ ስፖርት ስኬታማ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንዱ ነው፣ በመጨረሻዎቹ መቶ ሜትሮች ተፎካካሪዎቹን ወደ ኋላ በመተው እንደ አቦ ሸማኔ በመፈትለክ ይታወቃል፤ በዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር 12ኪሎ ሜትርን ስድስት ጊዜ እና አራት ኪሎ ሜትርን አምስት ጊዜ በማሸነፍ ባለክብረወሰን አትሌት ነው፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናም ልክ እንደ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ በተከታታይ አራት ጊዜ ማሸነፍ ችሏል፤ በአፍሪካ ጨዋታዎች፣ በቤት ውስጥ እና ሌሎችም ውድድሮች ታላቅ አሻራውን አስቀምጧል፤ የብዙ አትሌቶች ህልም የሆነውን ኦሎምፒክን ሦስት ጊዜ አሸንፏል፤ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ) “ቀነኒሳ አንበሳ” ብሎም አቀንቅኖለታል- አትሌት ቀነኒሳ በቀለ።

ከአበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩጽ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረ ስላሴን እና የመሳሰሉትን እግር ተከትሎ በኢትዮጵያ ምድር የበቀለ ድንቅ አትሌት ነው። ቀነኒሳ በትውልድ ቅብብሎሽ የተሻገረውን ገድል ማስቀጠል የቻለ ጀግና አትሌት ጭምር ነው። በትውልዱ ካሉ አትሌቶች መካከል ቀነኒስ አስደናቂ አትሌት መሆኑን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል።

ይህ የ42 ዓመቱ ጎልማሳ ዘንድሮም በፓሪስ ጎዳናዎች ታምር ሊሠራ ቀናቶችን እየተጠባበቀ ይገኛል። በ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ ውድድር ኢትዮጵያን ከሚወክሉ አትሌቶች መካከል አንዱ ነው። አትሌቱ ከዚህ በፊት በኦሎምፒክ በተሳተፈባቸው አስር እና አምስት ሺህ ርቀቶች ሳይሆን በማራቶን ከአንጋፋ እና ወጣት አትሌቶች ጋር ትንቅንቅ ያደርጋል።

ቀነኒሳ በቀለ በ2004 እ.አ.አ ነበር ግሪክ አቴንስ ላይ በተደረገው ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሎምፒክ የተሳተፈው። በወቅቱ ኢትዮጵያውያን የማይዘነጉት አኩሪ ገድል ፈጽሟል። ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ ዙፋኑን ለተተኪው ቀነኒሳ ያስረከበበት በመሆኑ በብዙዎች ኢትዮጵያውያን አዕምሮ የማይጠፋ አስደናቂ ትዕይንት እንደነበር አይዘነጋም።

በአስር ሺህ ሜትር ታላቁ ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ ቀነኒሳ እና ስለሺ ስህን ተጋግዘው የሀገራችንን ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገዋል። በወቅቱ ቀነኒሳ በቀለ ውድድሩን በበላይነት ሲያጠናቅቅ ስለሺ ስህን ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፤ ሻለቃ ኃይሌ አራተኛ ደረጃን ይዞ መጨረሱ የሚታወስ ነው።

በአምስት ሺህ ሜትር ርቀትም የተሳተፈው ቀነኒሳ የብር ሜዳሊያን ይዞ መጨረሱን ታሪክ ያወሳል። ከአራት ዓመታት በኋላ ደግሞ በቻይና በተደረገው የ2008ቱ የቤጂንግ ኦሎምፒክ በአስር እና አምስት ሺህ ሜትር ርቀቶች ለሀገሩ የወርቅ ሜዳሊያ አምጥቷል። አትሌት ጥሩነሽ ዲባባም በቤጂንግ በሁለቱም ርቀቶች ልክ እንደ ቀነኒሳ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማምጣቷ የሚታወስ ነው።

እ.አ.አ በ2010 በስኮትላንድ ኤደንበርግ በተደረገው የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር አትሌት ቀነኒሳ ጉዳት ገጥሞት እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚያን ጊዜ የጀመረው ጉዳቱ በአትሌቲክስ ህይወቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮበታል።

ዝመተኛው አትሌት በ2012ቱ የለንደን ኦሎምፒክም የተሳተፈ ሲሆን በተወዳደረበት የአስር ሺህ ሜትር ውጤት ሳይቀናው አራተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል። ወንድሙ ታሪኩ በቀለ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያስነብባል።

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከለንደን ኦሎምፒክ በኋላ ባሉት ሁለት የኦሎምፒክ መድረኮች ግን አልተሳተፈም። በ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ በማራቶን ለመሳተፍ ዝግጅት ቢያደርግም በብሄራዊ ቡድኑ ሳይካተት ቀርቷል። መጀመሪያ ላይ ፌዴሬሽኑ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የሚሳተፉትን አትሌቶች ሲያሳውቅ ቀነኒሳም አብሮ ተካቶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ብዙም ሳይቆይ ግን አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ እና ኦሎምፒክ ኮሚቴው ድጋሚ በሀገር ውስጥ የማጣሪያ ውድድር በማድረግ ብሄራዊ ቡድኑን የሚወክሉትን አትሌቶች መርጠዋል። ቀነኒሳ በቀለ ግን የሀገር ውስጥ ማጣሪያው አግባብ አይደለም በሚል በውድድሩ ሳይካፈል ቀርቷል። የቶኪዮ ጉዞውም ሳይሳካ ቀርቷል።

ቀነኒሳ በቀለ ከሌሎች የረጅም ርቀት ውድድሮች ወደ ማራቶን ፊቱን ያዞረው በ2019ኙ የፓሪስ ማራቶን ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በማራቶን በተሳተፈበት መድረክ በቀድሞዎቹ አትሌቶች ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ እና በኬኒያዊው የቀድሞ አትሌት ፖል ቴርጋት ተይዞ የነበረውን የቦታውን ሰዓት በማሻሻል ጭምር ነው ያሸነፈው።

በፈረንሳይ ፓሪስ ጎድናዎች የተጀመረው የቀነኒሳ የማራቶን ገድልም በተለያዩ የማራቶን ውድድሮች ተደጋግሟል። በ2015 እ.አ.አ በለንደን ማራቶን ለመሳተፍ ዕቅድ የነበረው ቢሆንም በጅማት ጉዳት ምክንያት መሳተፍ አልቻለም። ከ11 ወራት በኋላ ግን በ2016ቱ የለንደን እና የበርሊን ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፏል።

በ2024ቱ የለንደን ማራቶን አትሌቱ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ አይዘነጋም። እ.አ.አ በ2019 የበርሊን ማራቶን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ጭምር አሸንፏል። ያስመዘገበው ሁለት ሰዓት ከአንድ ሰከንድ ከ41 ማይክሮ ሰከንድ በርቀቱ ከኢሉድ ኪፕቼጌ እና ከቀድሞው አትሌት ኬልቪን ኪፕተም ቀጥሎ ሦስተኛው ምርጥ ሰዓት ነው።

እስካሁን በተወዳደረባቸው ዋና ዋና የዓለም የማራቶን መድረኮች በርካታ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል፡፡ በበርሊን ማራቶን ሁለት የወርቅ እና አንድ የብር ሜዳሊያ አሸንፏል። በለንደን ማራቶን ደግሞ ሁለት የነሐስ እና አንድ የብር ሜዳሊያ ማሸነፍ ችሏል። ቀነኒሳ በቀለ ፈታኝ በሆነው በኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ከ12 ዓመታት በኋላ ይመለሳል።

ከጉዳት ጋር ታግሎ በመጨረሻ በፓሪስ ኦሎምፒክ ለመወዳደር ቀናትን የሚጠብቀው አትሌት ቀነኒሳ ገና ከወዲሁ ትልቅ የማሸነፍ ግምት ተሰጥቶታል። የረጅም ጊዜ ተቀናቃኙ ኢሉድ ኬፕቼጌም በፓሪስ ኦሎምፒክ የሚሳተፍ ይሆናል።

የ39 ዓመቱ ኬኒያዊ እና የቀነኒሳ ፉክክር ከ2003 እ.አ.አ በፓሪስ የዓለም ሻምፒዮና የጀመረ ሲሆን በወቅቱ ኪፕቼጌ ሲያሸንፍ ቀነኒሳ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ነበር ያጠናቀቀው።

ኬኒያዊ አትሌት በ2016 የሪዮ እና በ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ የቀነኒሳን አለመኖር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በተከታታይ ሁለት ኦሎምፒኮችን አሸንፏል። የረጅም ርቀት አትሌቱ ዘንድሮ ካሸነፈ ደግሞ በኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር በተከታታይ ሦስት ጊዜ ያሸነፈ የመጀመሪያው አትሌት ይሆናል።

ፓሪስ የቀነኒሳ የዕድል ከተማው ናት ማለት ይቻላል። ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአስር ሺህ ሜትር ወርቅ የወሰደባት፣ ማራቶንን አንድ ብሎ ሲጀምር ያሽነፈባት እና በሀገር አቋራጭ እና ሌሎች ውድድሮች ያሽነፈባት ከተማ ናት- ፓሪስ።

ዘንድሮም ለአራተኛ ጊዜ በኦሎምፒክ ለመሳተፍ እና ለማሽነፍ ዝግጅቱን ጨርሶ የውድድሩን መጀመር እየተጠባበቀ ይገኛል። ይህም ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን እርሱን የሚያደንቁ ሌሎች የአትሌቲክስ ቤተሰቡም በጉጉት የሚጠብቁት ነው።

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በማራቶን በወቅታዊ ብቃታቸው እና በዝናቸው አሉ ከሚባሉ አትሌቶች ጋር በፓሪስ ብርቱ ፍክክር የሚያደርግ ይሆናል። ቀነኒሳ ባለው ወቅታዊ አቋሙ ከኢትዮጵያዊው ሲሳይ ለማ ቀጥሎ ሁለተኛው ምርጡ የሀገራችን የፓሪስ ኦሎምፒክ ተመራጭ መሆን ችሏል።

በ25 ዓመታት የዓለም አቀፍ ውድድር ቆይታው ብዙ በመሮጥ በሻለቃ ኃይሌ የሚበለጥ ቢሆንም በኦሎምፒክ፣በዓለም ሻምፒዮና እና በሀገር አቋራጭ ውድድሮች በየርቀቱ ፈጣን ስዓቶችን ጭምር በማስመዝገብ የተሻለ ታሪክ አለው። ሁለት ሰዓት ከአንድ ሰከንድ ከ41 ማይክሮ ሰከንድ በ2019ኙ የበርሊን ማራቶን ያስመዘገበው ፈጣን ሰዓት ነው።

ከ199-2024 እ.አ.አ ለ25 ዓመታት በሩጫው ዓለም ሲቆይ 23ቱን ዓመት በተሟላ ጤና በመሮጥ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል። አትሌቱ በአጠቃላይ 13 ጊዜ ማራቶን ሮጧል፤ አራት የወርቅ፣ አንድ የብር እና ሦስት የነሐስ ሜዳሊያዎችንም ሰብስቧል።

በተሳተፈባቸው ሦስት የኦሎምፒክ መድረኮች ደግሞ ሦስት ወርቅ እና አንድ ብር ለሀገሩ አምጥቷል። በአጠቃላይ የአትሌቲክስ ህይወቱ 173 ዓለም አቀፍ ውድድሮችን አከናውኗል። 111 የወርቅ፣ 24 ብር እና ዘጠኝ የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 144 ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ችሏል።

በፓሪስ ኦሎምፒክ በማራቶን ውድድር ከቀነኒሳ በቀለ በተጨማሪ ሲሳይ ለማ እና ዴሬሳ ገለታም ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ይሆናል። ታምራት ቶላ እና ኡሱዲን መሀመድ ደግሞ በተጠባባቂነት ተይዘዋል። ከኢትዮጵያውያን የማራቶን ተወዳዳሪዎች ቀነኒሳ በቀለ የተሻለ ምርጥ ሰዓት ያለው አትሌት መሆኑን የዓለም አተሌቲክስ አሰነብቧል።

ቀነኒሳ በቀለ ሀምሌ 19 በሚጀመረው የፓሪስ ኦሎምፒክ ምን አይነት ውጤት ያስመዘግባል የሚለውን አብረን የምናየው ይሆናል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here