“ስሜ ግን ዘላለም ዝነኛ ሆኖ ይኖራል”- ከሞናሊዛ ጀርባ

0
245

የጥበብ ሥራ ትልቁ አቅሙ ዘመንን በሰው ልብ ውስጥ መሻገሩ እና ዓለም አቀፉዊነቱ ነው። ጥንት የተሰሩ የጥበብ ሥራዎችን ዛሬም ድንበር እና ወሰን ሳይገድበን እንነጋገርባቸዋለን፤ እንመሰጥባቸዋለን እንዲሁም እንመረምራቸ ዋለን። በየዘመናቱ እንደ አዲስ የሚደንቁ ትውልድ የሚቀባበላቸው፤ ለሌላ የጥበብ ሥራ መነሳሳት የሚፈጥሩ፤የጥናት እና ምርምር አድራጊዎችን ቀልብ የሚስቡ የጥበብ ሥራዎች በዓለም ቅርስነት ተመዝግበው አሉ። “ጠቢብ ይሄይስ እም ጠቢብ” (ከጠቢብም ጠቢብ ይበልጣል) እንደሚባለው ለቆጠራ የሚያታክቱ የጥበብ ሥራዎች በዓለም ጉያ ውስጥ ቢኖሩም ሳይደበዝዙ፣ እንደገና ምስጢራቸው ጥልቅ እየሆነ የሚሄዱት ውስን ናቸው።

ከጣሊያን ተነስታ ኢትዮጵያዊያን ሙዚቀኞች የፍቅር ሐሳብ ውስጥ አርፋለች። በዘፋኞች በኩል ደግሞ ወደ ሕዝቡ ልቡና ገብታለች። በጥላሁን ገሰሰ፣ በቴዎድሮስ ካሳሁን፣ በበዕውቀቱ ሰውመሆን በኩል በትውልድ ቅብብሎሽ የውበት መለኪያ ተደርጋ ተወስዳለች። የቁንጅና መስፈሪያ ሚዛን፣መጥሪያ ቃል ሲታጣለት እሷ ትጠራና በቃ አንቺማ ቁርጥ እሷን ነሽ ተብሏል።

ይህች ሴት የውበት ምሳሌ መሆኗ አይደለም የሚደንቀው፤ የስዕል ስራ እንጂ። ሞናሊዛ ትባላለች። የስዕሏ አባት ጣሊያናዊው ሊዮናርዶ ዳቬንቺ በዓለም መድረክ ላይ ስሙ በሦስት ነገሮች ጎልቶ ይጠቀሳል። የተሐድሶ ዘመን ድንቅ ከያኒ ነው። አዲስ የእሳቤ  መንገድ የፈጠረ ሰው ነበር። አዲስ ስልትን የቀየሰ ሳይንቲስትም ጭምር ነው።

ይህ ድንቅ የጥበብ ሰው ካበረከታቸው ሥራዎቹ መካከል በዘርፍ ሰዓሊነቱ ፣በስዕል ደግሞ ሞናሊዛ ጎልታ የወጣችው ለምንድን ነው? ውስጧስ ምንድን ምሥጢር አለና ነው እያደረች አዲስ የምትሆነው?

ሊዮናርዶ የሞናሊዛን ስዕል መሳል የጀመረው ጣሊያን ፍሎረንስ በሚኖርበት ጊዜ  እ.ኤ.አ በ1503 ነበር። ከአስር ዓመታት የበለጠ ጊዜ ሥራውን ለማጠናቀቅ እንደወሰደበት ድርሳናት ይናገራሉ። የሞናሊዛ ስዕል ከስዕልነት ባለፈ የአንዲት ሴት ምስል ነው የሚለው አርት ኒውስ ድረገጽ ሞናሊዛ የፍሎረንሱ ነጋዴ ፍራንሲስኮ ሚስት ሊዛ ግራንዲ ናት በማለት የታሪክ መዛግብትን ይጠቅሳል። ሊዮናርዶ ስዕሉን ለሊዛ ግራንዲ ከመስጠት ይልቅ ወደ ፈረንሳይ በሄደበት ጊዜ ለሀገሪቱ ንጉሥ ፍራንሲስ ቀዳማዊ እንደሰጣቸው (እንደሸጠላቸውም የሚናገሩ አሉ) ተጽፏል።

በዚህ ምክንያትም የጣሊያናዊው ሊዮናርዶ ስዕል ሞናሊዛ የፈረንሳይ ሀብት ሆና የብዙዎችን ቀልብ በምትስብበት ፓሪስ ከተማ ሎቬሪ ሙዚየም ውስጥ እንድትቀመጥ ተደርጓል። ሰዓሊው ከዚህ ቀደም እንደሰራቸው ሥራዎች ምንም የስዕል መግለጫ ወይም ፍንጭ ስለ ሞናሊዛ አለማስቀመጡ እንቆቅልሹን የበለጠ አጥብቆታል። ለምሳሌ እ.ኤ.አ ከ1489 እስከ 1491 ዘ ሌዲ ዊዝ አን ኤርሚ እና ከ1474 እስከ 1478 ጀንቨራ ዲ በንሲ እንዲሁም ጊንፕሮ በተሰኙ ስራዎቹ ላይ የግርጌ መግለጫዎችን አስቀምጧል።  ሊዮናርዶ ሞናሊዛን ለምን ሊገልጻት አልፈለገም? ለምን ምስጢር እንድትሆን ፈለገ የሚሉት ዛሬም ድረስ የሚያነጋግሩ ጉዳዮች ናቸው።

ሞናሊዛ በሊዮናርዶ ሕይወት ውስጥ የምንጊዜም የጥበብ ሥራው ተደርጋ ተቀምጣለች። ቢቢሲ በዘገባው የሞናሊዛን ከሙዚየም መሰረቅ ተከትሎ የተረዳናቸው ሐቆች በሚል ባሰፈረው ጽሑፍ ምንም እንኳን ሞናሊዛ ምርጥ ስዕል ተብላ ብትታሰብም ከተሰረቀችበት እ.ኤ.አ 1911 በፊት ከሌሎች የስዕል ስራዎች የተለየች አልነበረችም ይላል።

ጣሊያናዊው አናጺ እና ቀለም ቀቢ ቬኔንዞ ፔሩጊያ በ1911 በፈረንሳይ ሎቬሪ ሙዚየም ውስጥ በእንጨት ሥራ ተሰማርቶ ነበር።በደሀ ቤተሰብ ውስጥ ያደገው ይህ የ20 ዓመት ወጣት  ለተሻለ ሕይወት ነበር ወደ ፈረንሳይ ፓሪስ  የተጓዘው። ፈረንሳይ በደረሰበት ጊዜም ሀገሪቱ ከጀርመን ጋር ጦርነት ለመጀመር ጫፍ ላይ ነበረች። በወቅቱም ጣሊያን ከጀርመን ጋር ሕብረት ታደርጋለች በሚል የፈረንሳይ ሕዝብ ስጋት ነበረበት። አናጺው ቬኔንዞ መገፋት እና በጥላቻ ዓይን መታየት አልቀረለትም። የስራ ባልደረቦቹም ሳል ማካሮኒ-የበሰበሰ ማካሮኒ እያሉ ይሰድቡት ነበር። ይህም ብቻ አልነበረም። አናጺው የሚቀባው ቀለም በካይ የሊድ ንጥረ ነገር ያለበት በመሆኑ ሁለት ጊዜ መበከል ገጥሞት ሆስፒታል ደርሶ ተርፏል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት የሊድ ንጥረ ነገሩ የሰው ልጅ ውሳኔ ላይ ትልቅ ሚና ያለውን የአዕምሮ ክፍል (ፕሪ ፍሮንታል ኮርቴክስን) እንዲጎዳ ያደርጋል። በዚህ ምክንያትም አናጺው የመወሰን ችግር ስለገጠመው የሞናሊዛን ስዕል ሰርቆ ወሰዳት የሚል መላ ምት የሚያስቀምጡ አሉ። እ.ኤ.አ በ1910 ቬኔንዞ ጎቤር በተባለ የመስታዎት ፋብሪካ ውስጥ በመስራት የሎቬር ሙዚየም በሌቦች እንዳይሰረቅ የበኩሉን ድርሻ ተጫውቷል። በሙዚየሙ ውስጥ በሚሰራበት ጊዜም ምን ያህል የጣሊያን የስዕል ስራዎች እንዳሉ ተመልክቷል። አብዛኞቹ ስዕሎች ከመቶ ዓመታት በፊት የተዘረፉ የጣሊያን ሀብቶች መሆናቸውንም አረጋገጠ። የፈረንሳዩ ንጉሥ ፍራንሲስ  ቀዳማዊ  ከሊዮናርዶ የገዟትን የሞናሊዛን ስዕልም የተመለከታት በዚህ ወቅት ነበር። በሙዚየሙ ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው የጣሊያን የስዕል ስራዎች በፈረንሳይ ተዘርፈዋል በሚል ስሜት የሀገር ተቆርቋሪነት አድሮበት ስዕሉን ሰርቆ መውጣቱም ይነገራል።

በዘመኑ ታዋቂ የነበረው ስፔናዊው ሰዓሊ እና ቀራጺ ፓብሎ ፒካሶ በሞናሊዛ ስዕል መጥፋት ከተጠረጠሩት መካከል አንዱ ነበር።60 የሚሆኑ ሰዎች በስርቆት ወንጀል ተጠርጥረውም ነበር። ጋዜጦች ይህንን ስዕል የተመለከተ ወይም የሚመልስላቸው ሰው ቢኖር ሽልማት እንደሚሰጡ ማስታወቂያዎችን ይነግሩ ነበር፤ ሕዝቡ ግን በወቅቱ የሞናሊዛ ስዕል ይህን ያህል የታወቀ ባለመሆኑ ይቀልድ እና ያሽሟጥጥ ነበር። ዝነኛው ፓብሎ ፒካሶ ከዚህ ቀደም በሙዚየሙ ውስጥ ቅርሶችን ከሰረቀው ገጣሚ ጉሊያም አፖሊናሬ ጋር ወዳጅ በመሆኑ ምክንያት ነበር የተጠረጠረው።

ቢቢሲ በዘገባው የሞናሊዛ ስዕል ፖሊስ አፍንጫ ስር ነበር ይላል። የፈረንሳይ ፖሊስ ቬኔንዞን ቤቱ ድረስ በመሄድ ፍተሻ ቢያደርግለትም እንኳን የጣት አሻራ ምርምራ አላደረገለትም፤ትንሽ ጠባብ ክፍሉን በሚገባ አልፈተሸም ነበር በማለት ያስታውሳል። ቤቱን በሚገባ ቢፈትሹት ኖሮ አንዲት ቁም ሳጥን ውስጥ የሞናሊዛን ስዕል ያገኙት ነበር ሲል ያትታል።

ከሰረቃት ሁለት ዓመታት በኋላ ቬኔንዞ ሞናሊዛን ወደ ጣሊያን ፍሎረንስ መልሶ ይዟት ሄደ። በዚያም ለሕዝብ ዕይታ እንድትበቃ እያንቀሳቀሰ አሳይቷታል። በወቅቱ ገበያ አምስት መቶ ሺህ ሊሬ ሊሸጣት ሞክሮ ነበር። ይህ ገንዘብ በአሁኑ ጊዜ ሁለት ሚሊየን ዬሮ እንደሚያወጣ ይገመታል።ስዕሉን ከሚገዙት ሰዎች ጋር በሚነጋገሩበት ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ።ቬኔንዞ አንድ ዓመት ከ15 ቀናት ተፈርዶበት እንዲታሰር ተወሰነ። ለሰባት ወራት በእስር ቤት ቆይቶ ፍርድ ቤት ቀርቦ “የሞናሊዛን ፈገግታ በድጋሚ ወደ ጣሊያን አመጣሁት፤የሀገሬ ሰዎችን የፊት ፈገግታም መልሼዋለሁ” ሲል ተናገረ።

ቬኔንዞ ከእስራት ከተፈታ በኋላ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ተሳትፏል። ከጦርነቱ በኋላም የቀደመውን ስሙን ቀይሮ ፔትሮ ተብሎ ወደ ፈረንሳይ ተመለሰ። በ1913 እ.ኤ.አ የሞናሊዛ ስዕልም ወደ ፈረንሳይ ሙዚየም ተመልሳ ሎቬሪ  ሙዚየም ውስጥ ተቀመጠች። ጥይት የማይበሳው  ማስቀመጫ መስታዎት ውስጥም እንድትቀመጥ ተደረገ። ቬኔንዞ ስሙን ቀይሮ ፔትሮ ፔሩጊያ ተብሎ ፈረንሳይ በሚኖርበት ጊዜ ሚስቱን ሞናሊዛ ወደ ምትገኝበት ሙዚየም ወስዶ አስጎብኝቷታል። በሙዚየሙ ውስጥ ሳሉም “እነዚህ የምትመለከቻቸው ጣሪያዎች ሁሉ ይረግፋሉ፣ ስሜ ግን ዘላለም ዝነኛ ሆኖ ይኖራል” በማለት ለሚስቱ ነግሯታል።

የሞናሊዛ ጉዳይ ገናና እና ዝነኛ የሆነው እውነትም ከተሰረቀች በኋላ ብዙኀን መገናኛ በፈጠሩት አጀንዳ ነው ማለት ይቻላል። የሰረቃት ሰውም አንድም ገንዘብ ለማግኘት በሚል ወይም የሀገሬን ሀብት ወደ ሀገሬ ልመልስ በሚል ሊሆን ይችላል። በስርቆት ከተወሰደችበት ጣሊያን ወደ ፈረንሳይ ሎቬሪ ሙዚየም ስትመለስ በሁለት ቀናት አንድ መቶ ሺህ ሰዎች ጎብኝተዋታል።

ሳይንስ ኤቢሲ ድረገጽ ላይ ሸሪያ ሰቲህ ባሰፈረው ሐሳብ “ ሞናሊዛ ዝነኛ የሆነችው ከተሰረቀች እና ከሕዝብ ዕይታ ከተደበቀች በኋላ ነው” በማለት ጽፏል። በዚህም ሞናሊዛ በታሪክ አጋጣሚ ዝናን ያገኘች ስለመሆኗ ይናገራል። ሊዮናርዶ ሞናሊዛን ወንድ እና ሴትን ወካይ ሆና እንድትታይ አድርጓል፤  በዚህም  ሞና ሴትን ይገልጻል፤ሊዛ ደግሞ ወንዶችን እንዲወክል ስለመደረጉ ሸሪያ ጽፏል።

የሞናሊዛ ፈገግታ ብዙ ተብሎለታል። ደስታ፣ ኀዘን፣ ምስጢር፣ ትካዜ፣ መሳቀቅን የመሳሰሉ ድብልቅልቅ ስሜቶችን ይጭርና ከፊቷ ዘወር ሲሉ ሁሉም ይጠፋል በማለት በስዕል ስራው የሚገረሙ ብዙዎች ናቸው። እ.ኤ.አ በ2021 የሞናሊዛ ስዕል 900 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ዋጋ ተተምኖላታል። በፈረንሳይ ሀብትነት የተመዘገበችው ሞናሊዛ የቅጂ መብት ጥበቃም ይደረግላታል። ማተም እና ማባዛትም ለሀገሪቱ መንግሥት ብቻ የተፈቀደ መብት ነው። በ1452 እ.ኤ.አ በጣሊያን  ቪንሴ የተወለደው ሊዮናርዶ በግንቦት ወር 1519 በፈረንሳይ ሕይወቱ አልፏል። የሞናሊዛ ስዕል 77 ሴንቲ ሜትር በ 53 ሴንቲ ሜትር  በሆነ እንጨት ላይ የተሳለ ድንቅ የጥበብ ስራ ነው፡፡

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here