በ2023 እ.ኤ.አ በዓለም ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ ሰዎች ይፋ የሚደረጉበት የፎርብስ መጽሄት ከ30 ዓመት በታች በአፍሪካ ተጽእኖ መፍጠር የቻሉ ሰዎች ውስጥ አንዱ አድርጐ አውጥቶታል፣ ዶ/ር ኦሊቨር ኡሺማ::
ትውልድና እድገቱ በአፍሪካዊቷ ሀገር ሩዋንዳ የሆነው ዶ/ር ኦሊቨር በትምህርት ቤት ቆይታው በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ እና በባዮሎጂ የትምህርት ዘርፎች ያለው የላቀ ዕውቀት እና ውጤት በቱርክ ጠቅላላ ሕክምና የትምህርት እድል እንዲያገኝ አስቻለው::
በትምህርቱ ከጠቅላላ ሕክምና ዘርፍ ውስጥ የጭንቅላት እና የጀርባ አጥንት ጉዳዮችን የሚያጠናው (የኑውሮ ኦንኮሎጂ)፣ ኑውሮሎጂ ኢንፌክሽን የሚፈጥሩ በሽታዎች እና የሕብረተሰብ ጤና ምርምሮችን ይሠራል::
በምርምሩ በርካታ የሕክምና ምርምር ሂደቶች ላይ ያሉ ጽሁፎችን ጽፎ ለማህበረሰቡ ለማቅረብ የተለያዩ የጋዜጣ ድርጅቶች እና የብዙኃን መገናኛዎችን በር ቢያንኳኳም ክፍያ እንዲከፍል ስለተጠየቀ ሳይሳካ እንደቀረ ያስታውሳል::
በ2018 እ.ኤ.አ “ኦሊ ኸልዝ ማጋዚን” የተሰኘ ለትርፍ ያልተቋቋመ ግብረ ሰናይ ድርጅት አቋቋመ:: ኦሊ ማጋዚን በ2019 የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ ዘር፣ ሀይማኖት፣ ፆታ እና ማንነት ሳይለይ የሚገድል ስለነበር በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በእስያ ያሉ ወጣቶች በጤና ምርምር ዘርፍ የራሳቸውን አቅም እንዲያሳድጉ ጥረት አደረገ::
የኦሊቨር ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት እ.ኤ.አ በ2019 ኒውሮ ኦንኮሎጂ (ከጭንቅላት እና ስፓይናል ኮርድ ጋር የተያያዘ) ጥናቶች እና ምርምሮችን ያካተተ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ኮንግረስ በቱርክ አደረገ:: ዝግጅቱ ከ300 በላይ የሕክምና ተማሪዎች እና በጤናው ዘርፍ ያሉ ከአውሮፓ እና ከእሰያ ተሳትፈዋል::
ግብረሰናይ ድርጅቱ የሚያተኩረው የወጣቶችን ሕይወት መቀየር በመሆኑ በ2019 በደቡብ ኮሪያ በተደረገው እና 74 ከዓለም ከተውጣጡ ባለተሰጥኦ ወጣቶች መካከል የክብር እንግዳ በመሆን ተሳተፈ::
በ2020 ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ከሀርቫርድ የጤና ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ስለበሽታው ግንዛቤ የሚፈጥሩ የተለያዩ ጽሑፎችን በ26 ቋንቋዎች በመተርጐም እንዲሰራጭ አደረገ :: ለዚህ ተግባር 500 የሕክምና ተማሪዎችን፣ ዶክተሮችን እና በጤናው ዘርፍ ያሉ ባለሙያችን አሳትፏል፤ ወጣቶችን ሊስብ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት ስለ በሽታው የማሳወቅ ተግባሩን ተወጥቷል፤ በዚህም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወጣቶች ድምፅ ኮቪድ 19ን ከታገሉ ምርጥ 10 ወጣቶች አንዱ አድርጎ በመምረጥ ዕውቅና እንደሰጠው ዘኒው ታይምስ ድረ ገፅ አስነብቧል::
በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕክምና ዘርፍ መማር የሚፈልጉ ወጣቶችን ከማገዝ ባለፈ በ2022 እ.ኤ.አ በሀገሩ ሩዋንዳ በአዕምሮ ጤና ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር ለማስቻል ከዳና ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ለዐሥር ሺህ የሁለተኛ ደረጃ እና የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ስልጠና እዲሰጥ አድርጓል:: በ2023 ደግሞ ከአዕምሮ ጤና ጋር በተያያዘ ከኦሊ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር ተባብሮ የሚሠራ እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ አዕምሮ የጤና ችግር ያለባቸውን የሚመረምር እንዲሁም ከሩዋንዳው ጭፍጨፋ በኋላ የአዕምሮ ጤና ላይ እንደ ግለሰብም ሆነ ማሕበረሰብ የሚኖረውን ተፅዕኖ የሚያስተምር “ናቪጌት ዘብሬን” የተባለ ፕሮጀክትን አስጀምሮ እየሠራ ይገኛል::
እንደ ኦሊቨር ገለፃ በሩዋንዳ በ1994 እ.ኤ.አ የነበረው የዘር ጭፍጨፋ ከ14 እስከ 18 ዓመት ባለው እድሜ ክልል ከሚገኙ ወጣቶች 10 ነጥብ ሁለት ከመቶው የአዕምሮ ጤና ችግር እንዲኖርባቸው አድርጓል::
የኦሊቨር የምርምር ሥራው በዓለማችን የሳይንሳዊ ምርምሮች በሚፃፍበት ዘላንሴት መጽሔት ላይ ከ100 በላይ የተለያዩ ጽሁፎችን ለሕትመት በቅተውለታል::
ከዚህ በተጨማሪም የምርምር ሥራዎቹ በመካከለኛ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ባሉ ሀገራት ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን በምርምር ማገዝ እና የልምድ ልውውጥ ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸት በየአካባቢያቸው ያለን ችግር በቀላሉ እንዲፈቱ ለማስቻል ያግዛሉ::
እ.ኤ.አ በ2021 ከአንድ ሺህ አመልካቾች ውስጥ በመመረጥ የክሊንተን ዓለም አቀፍ ዩንቨርሲቲ መግባት የቻለው ኦሊቨር በ2023 ደግሞ ከዓለም አቀፉ የጭንቅላት ምርምር ማዕከል እና ዳና ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር አራተኛው ዓለም ዓቀፍ ኮንግረስ በሩዋንዳ ኪጋሊ “ሞደርን ሪቮሊውሽን ፎር ፊውቸር ኒውሮ ሳይንስ ኤንድ ኑውሮሎጂ” ኮንፍረንስን እንዲካሄድ አድርጓል::
የኦሊቭር ድርጅት ጤናማ ዓለም ለመፍጠር እንደሚተጋ ይገልፃል:: በዚህም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተለይም በአፍሪካ ያሉ በጤና ዘርፍ መመራመር ለሚፈልጉ ልጆች የነፃ የትምህርት እድሎችን በአውሮፓ እና በአሜሪካ እንዲያገኙ የሚያግዝ ነው::
የተረሱ የሚመስሉ በምድር ወገብ አካባቢ የሚከሰቱ በሽታዎችን እንዲታወሱ በማድረግ እና ወጣቶች በተለይ የጤና ትምህርት እና ምርምር እንዲያደርጉ በማገዝ ላይ ይገኛል::
ኦሊቨር እንደሚለው በነጮች ምድር ሲማር ነገሮችን ከመቀበል ባለፈ ለነገሮች የመፍትሄ አቅራቢ ለመሆን የሚታትር ሊሆን እንደሚገባ አስተምሮታል::
የሰዎች አመጋገብ፣ በቀን ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ እና ስሜት ተደማምረው ጤናማ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ያስችላል፤ በዚህም ጤናማ ማሕበረሰብ መፍጠር እንደሚቻል ይናገራል:: ሁሉም ሰው በተለይ አፍሪካዊያን በየ አካባቢያቸው ያለውን ችግር መፍታት ከቻሉ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችል ለውጥ ማምጣ እንደሚችሉ ይናገራል::
የሕዝብን የጤና ሁኔታ ለማሻሻል ከመድኃኒት ይልቅ መከላከሉ ላይ መሥራት እና የኑሮ ሁኔታን መጠበቅ የተሻለ እንደሆነ የመረጃ ምንጫችን ለሆነው ለፎርብስ መፅሄት ገልፆ ፤ ለዚህም በተለይ በወጣትነት ዕድሜ ወቅት በትጋት ከተሠራ በጎልማሳነት ጤናማነት እንደሚመጣ ነው ያብራራው::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም