የአማዞን ደን በሞቃታማው የምድር ክልል የአማዞን ወንዝን እና የገባር ወንዞቹ ተፋሰስ የሚያካትት ነው:: አማዞን በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉ ስምንት የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ማለትም ብራዚል፣ ቦሊቪያ፣ ኢኳዶር፣ ኮሎምቢያ፣ ቬንዚዌላ፣ ሱሪናም እና ጉያናን በተለያየ መጠን አቅፏል::
አማዞን በዓለማችን በተፋሰስ ስፋቱ በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው:: የአማዞን ደን በምስራቅ አትላንቲክ ውቅያኖስ በምዕራብ እስከ አንድስ ተራሮችን ያካልላል፣ ስፋቱ በስተምስራቅ ከ320 ኪሎ ሜትር እስከ 1 ሺህ 900 ኪሎ ሜትር በስተምዕራብ የአንድስ ተራሮች ግርጌ ተለክቷል::
የአማዞን የስፋት መጠኑ በቀጣናው ካለው የአየር ንብረት ምቹነት፣ በርጥበት መጠኑም ሆነ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ከማግኘት ጋር የሚገናኝ ነው::
የአማዞን ደን የሰው ልጆች ቀደምት ዝርያ መገኛ ቀጣና ነው:: በመሆኑም ዛሬ ድረስ የቀደምት የሰው ዘር አምሳያዎች ሰፍረው የሚኖሩበት ለመሆኑ ማሳያ ሆኗል::
የአማዞን ጥቅጥቅ ደን 40 ሺህ የእጽዋት ዝርያ መገኛ ነው ተብሎ ተገምቷል:: ከዚህ ውስጥ 75 በመቶ የሚሆነው በዚያው በአማዞን ክልል ብቻ የሚገኝ ማለትም በሌላ ሀገራት ወይም አካባቢ የማይገኙ ናቸው::
የደን ሽፋኑን ጥቂት ዝርያዎች በብዛት ተጽእኖ አድርገውበት መመልከት ቢቻልም በአማዞን ደን 16 ሺህ የእጽዋት ዝርያዎች ከፍተኛውን መጠን ይዘው ይገኛሉ::
የደኑ የታችኛው ማለትም ለመሬት የቀረበውን ክልል የሚሸፍነው ለተለያዩ እንስሳት መኖነት የሚውል ነው:: ሀረግ እና ሌሎች ረዣዥም ዛፎች ላይ ተጠጋግተው የፀሀይ ብርሀን ለማግኘት ወደከፍታ ያደጉ በመሆናቸው ክፍተት አልባ ጥቅጥቅ አድርገውታል::
በአጠቃላይ በአማዞን ደን 390 ቢሊዮን ዛፎች ይዟል ተብሎ በባለሙያዎች ተገምቷል::
የደኑ ስር አፈርን ከመሸርሸር ጠብቆ ይዟል:: የደኑ የላይኛው ቅጠል የሚበዛበት ደግሞ የካርበን መርዛማ ትነትን በማቆር ኦክስጂን በመለገሱ ሕይወት ላለው ፍጥረታት በሙሉ ተፈላጊነቱን የላቀ አድርጐታል::
በዓለማችን መጪውን ዘመን ለሰው ልጆች መኖሪያነቱ አጠያያቂ ያደረገውን የዓየር ንብረት ለውጥን የሚታደግ መሆኑ ግራ ቀኙን አስማምቷል:: በመሆኑም “የምድር ሳንባ” የሚል መጠሪያ የወጣለትን ደን መንከባከብ መጠበቅ ግድ መሆኑ ነው በድረ ገፆች በማደማደሚያነት የሰፈረው::
ለዘገባችን ግሪን ኧርዝ፣ ወርልድ ዋይልድ ላይፍ፣ አማዞናይድ ድረገፆችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም