መፍትሄ ለምግብ ብክነት

0
154

ለምግብነት የሚውሉ ምርቶችን የተሻሻለ ማቀዝቀዣ ባለው የአቅርቦት ሰንሰለት ለተጠቃሚው ማድረስ በዓመት ከሚባክነው አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ቶን ግማሽ ያህሉን ማዳን እንደሚያስችል ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ አስነብቧል::

በአሜሪካ የሚችጋን ዩኒቨርስቲ ያካሄደው ጥናት እንዳመለከተው 620 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ለብክነት የሚዳረግ ምግብን ማቀዝቀዣ ባለው የምግብ ሰንሰለት ማዳን ይቻላል:: በዓለማችን 800 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጐች ለረሀብ እንደሚዳረጉ የጠቀሰው ድረ ገፁ በተሻሻለ ማቀዝቀዣ ከብክነት ማዳን የረሀብ ተጠቂዎቹን ከመመገብ ባሻገር የዓለም የሙቀት መጠንን  መቀነስ እንደሚያስችል ነው ባለሙያዎቹ ያሰመሩበት::

ጥናቱ በየአህጉራት ባካሄደው መረጃ የማሰባሰብ እና የማጠናቀር ሥራ በደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ እስያ በተመቻቸ ማቀዝቀዣ 45 በመቶ የምግብ ብክነትን እና 54 በመቶ ተዛማጅ ልቀትን መቀነስ እንደሚያስችል የጥናቱ ውጤት አመላክቷል::

በተጨማሪም ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በተመቻቸ ማቀዝቀዣ የምግብ ብክነትን 47 በመቶ፣ ልቀትን ደግሞ 66 በመቶ የመቀነስ እድል ያላቸው መሆኑን ነው የጠቆሙት- አጥኚዎቹ::

በሌላ በኩል ሀገራት በየቀጣናው ከእርሻ ወደ ጠረጴዛ  ወይም ወደ ጉርሻ የምግብ አቅርቦት ሰንሰለትን መዘርጋት ከተመቻቸ የማቀዝቀዣ ሰንሰለቶች ጋር ሊወዳደር በሚችል መጠን የምግብ ቁጠባን እንደሚያረጋግጥ የጥናቱ ውጤት አመላክቷል::

ከአጥኚዎቹ መካከል ፕሮፌሰር ሸሊሚለር የምግብ ብክነት በሰዎች ከሚፈጠረው የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀቶች ስምንት በመቶ ይይዛል ተብሎ እንደሚገመት ጠቁመዋል:: በአብዛኛው በበለፀጉ ሀገራትም የምግብ ብክነት በቤተሰብ ደረጃ ነው የሚከሰተው::

የተሻሻለ ማቀዝቀዣን በምግብ ሰንሰለት ውስጥ ማካተት የምግብ ብክነት እና ከብክነቱ ጋር በተያያዘ የበካይ ትነት ልቀትን እንደሚያሻሽል ባለሙያዎቹ አረጋግጠዋል::

ለአብነት ስጋ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው ለምግብ ብክነት ይዳርጋል:: ይህን በማቀዝቀዣ ስርአት መደገፍ 43 በመቶ በስጋ ብክነት የሚፈጠር ልቀትን ማስወገድ ያስችላል ነው ያሉት ተመራማሪዎቹ::

 (ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here