በፈረንሳይ እና በእግሊዝ ሀገራት መካከል ከሚገኙት ደሴቶች መካከል በሳርክ ደሴት ላይ በ1956 እ.አ.አ በግንብ የተሰራው የዓለማችን ጠባቧ ባለሁለት ክፍል እስር ቤት መሆኗን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::
የድረ ገፁ ጽሑፍ እንዳመለከተው ዛሬም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው እስር ቤቱ አምስት ኪሎ ሜትር በአንድ ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር ስፋት እና 600 ነዋሪዎች ላለው ደሴት የሚመጥን ተደርጐ መሠራቱ ነው የተጠቆመው::
በደሴቷ ላይ የሚታሰሩ የወንጀል ተጠርጣሪዎች በጠባቧ እስር ቤት የሚቆዩት ለሁለት ቀናት ብቻ ነው:: ከዚያ በኋላ በእስር የሚቆዩ ከሆነ ሰፋ ያለ እስር ቤት በሚገኙበት አጐራባች ጉር ንሴይ ደሴት ይወስዳሉ::
በሳርክ ደሴት የወንጀል ተጠርጣሪ ወይም ወንጀል ፈፃሚ በየዕለቱ እንደማይከሰት ያተተው የድረ ገፁ ጽሑፍ አልፎ አልፎ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ይዞ ለጥቂት ቀናት የሚቆዩትን ታሳቢ በማድረግ ነው ጠባቧ እስር ቤት የተገነባችው::
በደሴቲቱ ላይ ሕግ አስከባሪ አካላት በየዕለቱ የሚጠበቅባቸውን ተግባራት እየፈፀሙ እንደሚገኙ ያስነበበው ጽሑፍ ጠባቧ እስር ቤት በየዕለቱ በሰዎች እንደምትጨናነቅ ሰዎቹም ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ሳይሆኑ ከየማዕዘናቱ የሚሰባሰቡ ጐብኚዎች መሆናቸውን አስምሮበታል::
በሳርክ እስር ቤት በጣም ታዋቂ ከሆኑ እስረኞች አንድሬስ ጋርዴስ ሥራ አጡ የኒውክሌየር ፊዚክስ ሊቅ ይገኙበታል:: ምሁሩ ደሴቷን የራሱ እንደሆነች ነበር የሚናገረው:: ይህንኑ እምነቱን ማንም ስራዬ ብሎ አድምጦት ያገናዘበውም አልነበረም::
ከፊል አውቶማቲክ የጦር መሣሪያ ይዞ ወደ ደሴቷ ያቀናው አንድሮስ ጋርዴስ እግሩ እንደረገጣት ደሴቷን ሙሉ በመሉ መቆጣጠሩንና በሱ ትዕዛዝ ስር መውደቋን ጽፎ በየቦታው ይለጥፋል::
አንድ ሬስ ጋርዴስ ይህንን የተለጠፈውን የተመለከተ በሥራ ላይ በነበረ ፖሊስ በቡጢ ተነርቶ በቁጥጥር ስር ይውላል:: መሣሪያውን ተነጥቆም በጠባቧ እስር ቤት ሊታሰር መቻሉን ነው ድረ ገፁ ያስነበበው።
ዛሬም ጠባቧ እስር ቤት አገልግሎት በመስጠት ላይ ናት። መስኮት ባይኖረውም መብራት እና ማሞቂያ ተገጥሞላታል።
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም