ዘርዓ ያዕቆብ

0
315

“ዘርዓ ያዕቆብ  ከንጉሥ ኢዛና ወዲህ ኢትዮጵያ ካየቻቸው ታላላቅ መሪዎች አንዱ እና እርሱን ተከትለው ከነገሡት ከዳግማዊ ምኒልክ እና ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ውጪ የሚተካከለው የሌለ ንጉሥ መሆኑ አያጠያይቅም” ያለው በኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ግንባር ቀደም የሆነው ተመራማሪ ኤድዋርድ አለንዶርፍ ነው።

ዘርዓ ያዕቆብ ለእምነቱ ቀናኢ ንጉሥ እና የሥነ ጽሁፍ  አፍቃሪ ብቻ ሳይሆን  ቆራጥ እና የተካነ ወታደርም ነበር። ከዛግዌ በኋላ ተቋርጦ የነበረው ሰሎሞናዊው ስርወ መንግሥት ወደ ከፍታው ጫፍ የደረሰው በእርሱ ረዥም የንግሥና ዘመን እንደነበር ይነገራል።

ዐፄ ዳዊት ካሏቸው ልጆች አራተኛ ልጅ የሆነው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ በ1426 ዓ.ም በአባቱ ዙፋን ላይ ተቀምጧል። እርሱ እንደቆረቆራት የሚነገርላትን ደብረ ብርሀን ከተማን መዲናው በማድረግ የአገዛዝ ዘመኑን ቁስጥንጢኖስ በሚል ስመ መንግሥት ጀምሯል።

በኢትዮጵያ ከባእድ አምልኮ እና ጥንቆላ ጋር የተያያዘ ማንኛውም ድርጊት እንዲቆም ጥብቅ አዋጅ በማውጣት አግዷል። በሌላም በኩል በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካህናት ትክክለኛ አስተምህሮ እንዲያስተምሩ እና የተለያዩ ሀይማኖታዊ መጻሕፍትን እንዲፅፉ በማድረግ የለውጥ እርምጃዎችን ወስዷል።

በሌላ በኩል “የኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል መፅሀፉ ሐሪ አትክንስ እንደገለፀው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ትኩረቱን በቤተ ክርስቲያን ላይ ሳይገድብ መንግሥታዊ መዋቅሩን እንደገና ማደራጀት ችሏል።

በኢትዮጵያ ደካማ ነገሥታት ስር የነበረውን የመንግሥት አወቃቀር እንደገና በማደራጀት የተዋጣለት ሥራ የሠራ ታላቅ ንጉሥ ነበር። የተለያዩ ማህበራዊ ለውጦችን እውን በማድረግ፣ ከውጭ ኃያላን ጋር ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት በማደስ ብዙ ጥረቶችን አድርጓል።

የአካባቢ ገዥዎች ለመንግሥቱ እንዲገብሩ የሚያደርግ አዲስ አወቃቀር በመፍጠር እና ሹም ሽሮችን በማከናወን ጠንካራ የመንግሥት ሥርዓት ለመዘርጋት ባደረገው ጥረት ከዚህ በፊት የተዝረከረከውን አሠራር መልክ አስይዟል። አንዳንድ የቤተ መንግሥት የማዕረግ ስሞችን እና የሹም ሽር አወቃቀሮችን እውን አድርጓል። በተጨማሪም የሥርዓተ ንግሡን ሁኔታ አሻሽሏል።

ሐሪ አትክንስ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ በተሰኘ መጽሐፉ ላይ እንዳስቀመጠው የኢትዮጵያ መንግሥት አዳዲስ ጠቅላይ ግዛቶችን በመመደብ፣ ደኅና አስተዳዳሪዎች በመሾም እና አዲስ የግብር ደንቦችን በመስጠት የኢትዮጵያን መንግሥት አቋም አሻሽሏል። ሀገሪቱ በባላባቶች ስትገዛ ሳለ፣ ባላባቶቹ በአንድ አነስተኛ ንጉሥ ስር ነበሩ። በዚህ አይነት ካሚያስተዳድሩት ነገሥታት መካከል የበላይነት የሚኖረው አንዱ ነው። ይህም በኢትዮጵያ የነገሥታት ንጉሥ ወይም ንጉሠ ነገሥት ተብሎ ይጠራል። በየጠቅላይ ግዛቱ ገዥዎችን የሚሾመው ንጉሡ ነው። እነዚህ ገዥዎች  በየጠቅላይ ግዛቱ የጦር መሪዎች ከሆኑ ራስ ወይም ሹም እየተባሉ ይጠራሉ። እነርሱም በልብስ፣ በጨው፣ በብረት እና በምግብ መልክ ለንጉሡ ግብር ይሰበስባሉ። በዘመኑ የተቀረፀ ዘመናዊ የገንዘብ ሥርአት ባይኖርም በምትኩ የንግድ ልውውጡ ይከናወን የነበረው በአሞሌ ጨው ወይም በብረት እንዲሁም ዕቃ በዕቃ በመለዋወጥ ነበር። በዚህ አይነቱ ዘመናዊ አወቃቀር በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያውያን ኑሮ ከአውሮፓውያን ጋር የሚመጣጠን ነበር።   አስተዳደሩን የተማከለ የማድረግ ሙከራው ከነባር የክፍለ ግዛት መሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ቢያስነሳበትም ተቃውሞዎቹን በማኮላሸት የለውጥ እቅዱን መሬት አስነክቷል።

የቤተ መንግሥት የማዕረግ ስያሜዎችን በተመለከተም ፍስሐ ያዜ፣ የ5 ሺህ ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፉ እንደገለፀው ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ የራሱ የፈጠራ ውጤት የሆኑ አዳዲስ የቤተ መንግሥት የማዕረግ ስሞችን ከነበረው እንዲጨመሩ አድርጓል። ለአብነትም እንደ ፊታውራሪ፣ ቀኝ አዝማች፣ ግራዝማች፣ ደጃዝማች፣ ባላምባራስ፣ ጸሐፌ ትዕዛዝ፣ ከንቲባ፣ አፈ ንጉሥ እና መሰል የማዕረግ ስያሜዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ያዋለ አርቆ አሳቢ ንጉሥ መሆኑን ፅፏል።

የፍርድ ሥርዓቱንም ሆነ አጠቃላይ የማዕረግ ስሞችን እና አወቃቀሮችን ዘመናዊ ለማድረግ የቻለው ታላቁ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዘርዓ ያዕቆብ የመንግሥት አወቃቀሩ ከሌሎች የኢትዮጵያ ነገሥታት የተለየ መሆኑን ፍስሐ ያዜ ከትቦታል።

የሥርዓተ ንግሥናውን ሀኔታ በመቀየር ረገድም ዘርዓ ያዕቆብ አስገራሚ ታሪክ አስመዝግቧል። እነዚህን ዘርፈ ብዙ የለውጥ እርምጃዎች ካደረገ በኋላ ተቋርጦ የቆየው የሰለሞናዊውን ስርወ መንግሥት ልማድ ወደ ቀድሞ ሁኔታው መመለሱን ለማረጋገጥ የንግሥና ሥርአቱን አክሱም ፂዮን በጳጳሱ ቀቢነት እንዲከናወን ወስኗል። ይህ ውሳኔውም ብዙዎችን ያስገረመ እና ያስደሰተ ከመሆኑ በተጨማሪ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አትርፎለታል። በመሆኑም ወደ አክሱም ከመሄዱ በፊት የየአካባቢው ግዛቶችን የሚያስተዳድሩ ገዥዎችን መርጦ በመሾም በየግዛቶቹ አሰማርቶ እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል።

ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ለሲመተ በዓሉ አክሱም ከተማ እንደገባ ሕዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ ሆታ እና ጭፈራ እንደተቀበላቸው ይነገራል። ንጉሡ በተዘጋጀለት እስከ ቤተ ክርስቲያኗ በር በተዘረጋ ስጋጃ በክብር ሲራመድ ግራ እና ቀኝ ወርቅ እየበተነ ያልፍ እንደነበር ፍስሐ ያዜ ፅፏል።

መሪራስ አማን በላይ “የኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ” በተሰኘ መጽሀፋቸው ላይ እንደገለፁትም ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ በአቡኑ……ተቀብቶ ዘውድ በመጫን ያማረ የንግሥና በዓሉን ፈፅሞ ወደ መዲናው ደብረ ብርሃን ሲመለስ በአባቱ ንጉሥ ዳዊት የተጀመሩ አብያ ክርስቲያናትን እንዲጠናቀቁ ትእዛዝ እየሰጠ ማለፉን ፅፈዋል።

በርካታ ፀሀፊዎች ከዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ  በኋላ ያሉትን የሀገራችንን ነገሥታት በአንቱታ በመጥራት እንደፃፉ የሚገልጸው ፍስሐ ያዜ ይህን ያስጀመረው ዘርዓ ያዕቆብ እንደሚሆን ግምቱን በማስቀመጥ ከዚህ በኋላ ያለውን ታሪክ በአንቱታ እንደሚፅፍ ይናገራል፤ እኔም የእርሱን መንገድ ለመከተል መርጫለሁ።

የዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ሌላው የሚታወቅበት ጉዳይ ታላቅ የሽነ ጽሑፍ አብዮት የተነሳበት ዘመን መሆኑ ነው። እንደ ሐሪ አትክንስ በዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ልዩ ልዩ መጻሕፍት ተጽፈዋል፤ በግዕዝ፡፡ በዚህ የተነሳም ዘመኑ ታላቁ የግዕዝ ቋንቋ ዘመን ተብሏል። በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመንም  ቋንቋው ከፍተኛ የእድገት ዘመን ላይ የደረሰበት እንደሆነም ተገልጿል። በወቅቱ በኢትዮጵያ የሕዳሴ ዘመን ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። በርካታ መጻሕፍት የተፃፉበት እና በግዕዝ ቋንቋ የተተረጎሙበት ዘመን ነው። የቅዱስ ላሊበላ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የቅዱስ ተክለ ሀይማኖት እና የቅዱስ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የመሳሰሉ ቅዱሳን እና የመነኮሳት የሕይወት ታሪኮች በግዕዝ ተጽፈዋል። በተጨማሪም ንጉሡ ራሳቸው ታላቅ መንፈሳዊ ፀሀፊ ነበሩ። በመሆኑም ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ካበረከቷቸው በርካታ መጻሕፍት መካከል “መፅሐፈ ብርሃን” እና “መፅሐፈ ምእላድ” ዝነኞቹ ናቸው። ነገር ግን በዚህ ዘመን በግዕዝ ቋንቋ ከተፃፉት እጅግ መሰረታዊ ከሚባሉት ሥራዎች አንዱ “ፍትሐ ነገሥት” ነው። ዋና ትኩረቱም በሲቪል እንዲሁም በቀኖና ሕግጋት ላይ ነው። መፅሃፉ መነሻው ግብፅ ሲሆን በግዕዝኛ ተተርጉሞ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በዘርዓ ያዕቆብ ዘመን እንደ ነበር ይነገራል። በመቀጠል አንድ በአይሁድ ታሪክ፣  ስለእስክንድርያ፣ ስለእስልምና እና ስለኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክ የተፃፉ መጻሕፍት በግዕዝ እንደተተረጎሙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ተቋርጦ የቆየውን በኢትዮጵያ እና በአውሮፓውያን መካከል የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲመለስ አድርገዋል። በተያያዘም የኢትዮጵያን ግዛት ከባርካ ወንዝ እና ከምፅዋ ጀምሮ ወደ ደቡብ እስከ ኢፋት፣ ፈጠጋር እና ባሌ ድረስ በማስፋት ሉዓላዊ ዳር ድንበሯን አስከብረው የገዙ ታላቅ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ናቸው።

ታላቁ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ለ36 ዓመታት ኢትዮጵያን አስተዳድረው በ1460 ዓ.ም  አርፈው፣ አፅማቸውም በጣና ሀይቅ በሚገኘው ደቅ እስጢፋኖስ ገዳም በክብር ተቀምጦ ይገኛል። ከንጉሡ ሞት ጋር ተያይዞ የወረራ እና የመስፋፋት ዘመን የተባለለት የመጀመሪያው የሰሎሞናውያን ዘመን አብቅቷል፡፡ እኛም በዚሁ አበቃን።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here