ዐሥር ወራት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

0
154

በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ ረቂቅ አዋጅ ማጽደቁ ይታወሳል፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ ረቂቅ አዋጅ ነሐሴ 08 ቀን 2015 ዓ.ም ነበር ያፀደቀው። ይህ የሆነው ደግሞ ግጭቱን በመደበኛው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ለመቆጣጠር አልችልም በማለት የአማራ ክልላዊ መንግሥት ለፌደራል መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ነበር።

አዋጁ በመጀመሪያ ለስድስት ወራት እንዲተገበር ውሳኔ ተላለፈ፣ የክልሉ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ባለመመለሱም ለተጨማሪ አራት ወራት  እንዲራዘም ተደረገ። በአጠቃላይ የአማራ ክልል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መተዳደር ከጀመረ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዐሥር ወራትን አስቆጥሯል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ክልሉ አሁንም ድረስ በግጭት ውስጥ ይገኛል። ይህ ደግሞ በሰሜኑ ጦርነት ከባድ ስብራት ያስተናገደውን አማራ ክልል ይበልጥ እንዲጎዳ አድርጎታል። ምትክ የለሹ የሰዎች ሕይወት እየጠፋ ከመሆኑም ባሻገር ከፍተኛ ቁሳዊ ውድመት እየደረሰ ነው። አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ መሠረተ ልማቶች እና መሰል ማሕበራዊ መገልገያዎች ወድመዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በኢትዮጵያ ባለው ግጭት፣ ድርቅ እና መሰል ምክንያቶች ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደሆኑ አስታውቋል። ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ደግሞ በትምህርት ዘመኑ ከስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ይማራሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር። ይሁን እንጂ ምዝገባ በማካሄድ ወደ ትምህርት ገበታ መምጣት የቻሉት የእቅዱን ግማሽ ያህሉ ብቻ ነው:: ወደ ትምህርትቤት የሄዱትም በግጭቱ ምክንያት በስጋት ከርመዋል::

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሀገር አቀፍ ፈተና በቴክኖሎጂ ታግዞ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ በአማራ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት እንደተቋረጠ ነው። በግጭቱ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠር ተማሪ ወደ ትምህርት ገበታ ባልመጣበት ፈተናው በቴክኖሎጂ ታግዞ እንደሚሰጥ መነገሩ በተማሪዎች ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ  ሆኗል።

በተመሳሳይ በግጭቱ ምክንያት በርካታ የጤና ተቋማት ጉዳት ማስተናገዳቸውን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከወራት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል። ከዚህ ባለፈም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰዎችን እንቅስቃሴ በመገደቡ ነዋሪዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ አድርጓል። በዚህም በተለይ ነብሰ ጡሮች እና ሕጻናት ዋነኛ የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን ነዋሪዎችን በማነጋገር በተደጋጋሚ ማስነበባችን ይታወሳል።

የሰዎች እንቅስቃሴ መገደቡም የንግድ እንቅስቃሴውን ክፉኛ ጎድቶታል። ይህም ለሁሉም ነገር መሠረት የሆነው ግብር አሰባሰብ ላይ ችግር ፈጥሯል። ከአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ግጭቱ ክልሉ መሰብሰብ የነበረበትን ግብር እንዳይሰበስብ አድርጎታል። እስከ ግንቦት መባቻ ድረስ የተሰበሰበው ግብርም ከሚጠበቀው ከግማሽ የዘለለ አይደለም::

ግጭቱ የንግድ እንቅስቃሴውን ስላዳከመው የንግዱን ማሕበረሰብ ክፉኛ ጎድቶታል። በመሆኑም ሠርተው የሚጠበቅባቸውን ግብር መክፈል እንዳልቻሉ ነው በንግድ ሥራ የተሰማሩ ነዋሪዎች የሚናገሩት።

የክልሉ የምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት በመሆን ከግብርና ቀጥሎ የሚጠቀሰው ቱሪዝም ፍፁም ሰላምን የሚፈልግ ዘርፍ ነው፣ ክልሉ ደግሞ ዓለም አቀፋዊ ዕይታን የሚስቡ የመስህ ሀብቶችን የያዘ ባለፀጋ ነው። ይሁን እንጂ በክልሉ ዐሥር ወራትን የተሻገረው ግጭት ዘርፉን ክፉኛ ጎድቶታል። ከዚህ ባለፈም በመስህብ ሀብቶች ላይ አደጋን ደቅኗል።

የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ እንዳስታወቀው ግጭቱ ከሰሜኑ ጦርነት ማግሥት እያገገመ የነበረውን የቱሪዝም ዘርፉን እየጎዳው ነው። ዘርፉ ከሌሎች በተለየ ፍፁም ሰላምን እንደሚፈልግ በማንሳት ለሰላም መስፈን ሁሉም ወገን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

በአሁኑ ወቅት በርካታ አገልግሎቶች ኢንተርኔት ላይ ጥገኛ መሆናቸው ይታወቃል። በአማራ ክልል ደግሞ የኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ ዐሥር ወራትን ተሻግሯል። ይህም የክልሉን የንግድ እንቅስቃሴ ክፉኛ ጎድቶታል ይላሉ ሐሳባቸውን ያካፈሉን ነዋሪዎች።

በአጠቃላይ የኢንተርኔት መቋረጡ እንደ ሀገርም እንደ ክልልም ከባድ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ አስከትሏል ባይ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጊዜ ገደብ ማለቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ አውጥቷል። ኮሚሽኑ በመግለጫውም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የታሰሩ ሰዎች እንዲለቀቁ ጠይቋል። ከዚህ በተጨማሪም የሰዎች እንቅስቃሴ ገደብ ሊነሳ፣ ማሕበራዊ እና መሰል አገልግሎቶች፣ በአጠቃላይ ሁሉም አገልግሎቶች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ሊመለሱ እንደሚገባ አሳስቧል። ከግጭቱ ለመውጣት ፖለቲካዊ ንግግር እና ድርድር መፍትሄ ስለመሆኑ ብዙዎች እየተናገሩ ይገኛሉ::

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here