አማራ ክልል ለአትሌቲክስ ስፖርት ፀጋውን አብዝቶ የሰጠው ክልል ነው። ምቹ የመሬት አቀማመጥ እና ተስማሚ የአየር ፀባይ አለው። ለዘርፉ የሚሆን ደጋ፣ ወይና አደጋ እና ቆላማ የአየር ፀባይ አለው- አማራ ክልል። ይህን ፀጋ በመጠቀም አሁን ላይ አራት የአትሌቲክስ ማሰለጠኛ ማዕከላት ተከፍተው ተተኪ ስፖርተኞችን እያፈሩ ሲሆን በርካታ ያልተጠናቀቁ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላትም በክልሉ ይገኛሉ።
ተንታ፣ ደጋ ዳሞት፣ ጉና አውስኮድ እና ደብረ ብርሃን የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላት አሁን በሥራ ላይ ያሉት ናቸው። በደቡብ ወሎ ዞን በተንታ ወረዳ አጅባር ከተማ የሚገኘው በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተንታ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል በ2008 ዓ.ም ነበር በደቡብ ወሎ ዞን፣ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ እና በወሎ ዩኒቨርሲቲ በጋራ በሦስትዮሽ ጥምረት ሥራ የጀመረው። እስከ 2013 ዓ.ም ድረስም በፕሮጀክት ደረጃ በርካታ ተተኪ አትሌቶችን አፍርቷል።
በ2014 ዓ.ም ግን ፕሮጀክቱ ወደ ማሠልጠኛ ማዕከል አድጓል። እስካሁንም ክልሉን እና ሀገራችንን የወከሉ በርካታ ተተኪ አትሌቶችን አፍርቷል። በ2013 ዓ.ም ለመስክ ሥራ ወደ ቦታው ባቀናሁበት ወቅት አካባቢው ለአትሌቲክስ ስፖርት ምቹ መሆኑን ተረድቻለሁ።
ከባለሙያዎች ባሰባሰብኩት መረጃ ቦታው ከባህር ወለል በላይ ከሁለት ሺህ 400 እስከ ሦስት ሺህ አንድ መቶ ከፍታ አለው። ይህ ደግሞ የደጋ እና የቆላማ የአየር ፀባይ በመያዙ ለዘርፉ ምቹ እንደሆነ ባለሙያዎች አስረድተዋል፡፡ ወደ ማሠልጠኛ ማዕክል ካደገበት ከ2014 ዓ.ም ወዲህ ባሉት ዓመታት በአህጉር እና ዓለም አቀፍ መድረኮች የተሳተፉ በርካታ አትሌቶችን ማፍራት ችሏል፤ ማሠልጠኛ ማዕከሉ።
ባሳለፍነው የ2015 ዓ.ም ብቻ አራት አትሌቶች በአህጉር እና ዓለም አቀፍ መድረኮች ተሳትፈዋል። ለአብነት በአውስትራሊያ ባትረስት ከተማ በተደረገው የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር ከአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከሉ የተገኙት አቤል በቀለ እና ትነበብ አስረስ ሀገራችንን ወክለዋል። በኮሎምቢያ ካሊ በተደረገው የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና ደግሞ ከዚሁ የአትሌቲክስ ማዕከል የተገኘችው አትሌት ፂዮን አበበ የብር ሜዳሊያ ማሸነፏ አይዘነጋም። እንዲሁም ዛምቢያ ላይ በተደረገው የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና ላይ የአትሌቲክስ ማዕከሉ ፍሬ የሆኑ ሦስት አትሌቶች በውድድሩ ሲካፈሉ አንድ አሠልጣኝም ተመርጦ ወደ ቦታው አቅንቷል። በውድድሩ የተካፈሉት ሰውመሆን አንተነህ፣ ሰላም ምህረት እና መንግስቱ አማረ በውጤት ታጅበው ጭምር ከዛምቢያ መመለሳቸው የሚታወስ ነው።
ዘንድሮ ደግሞ በዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር ሁለት አትሌት እና አንድ አሰልጣኝ እንዲሁም በአፍሪካ ሀገር አቋራጭ ውድድር አንድ አትሌት ሀገራቸውን ወክለው ተሳትፈዋል። ምንም እንኳ የአትሌቲክስ ማዕከሉ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆነውም በርካታ ተተኪ አትሌቶችን ለሀገራችን ማበረከት ችሏል። አሁን ላይ የማሠልጠኛ ማዕከሉ እና የአትሌቶች አቅም እያደገ በመሆኑ በተለያዩ የሀገር ውስጥ መድረኮች እየተሳተፈ ነው። በዘንድሮው የ41ኛው የጃንሜዳ ዓለም አቀፍ ሀገር አቋራጭ ውድድር የተሳተፈው በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተንታ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል አሸናፊ መሆኑም አይዘነጋም።
ባሳለፍነው ዓመት በተከናወነው በ52ኛው የክለቦች እና የክልሎች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ክልሉን በመወከል ተሳትፈው ውጤታማ መሆናቸው ይታወሳል። የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከሉ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በየዓመቱ በሚደረገው የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ውድድር ላይም ሜዳሊያ ውስጥ ገብቶ ማጠናቀቁም የሚታወስ ነው። በቅርቡ በአሰላ ከተማ በተካሄደዉ 4ኛዉ የኢትዮጵያ ማሠልጠኛ ማዕከላት የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ላይ በሁለቱም ፆታዎች በበላይነት ማጠናቀቁ አይዘነጋም።
እንደ ታላላቆቹ አትሌቶች ሀገሩን በመወከል በዓለም አቀፍ ውድድሮች መሳተፍ እና ውጤታማ መሆን ህልሙ መሆኑን የነገረን አትሌት አየለ አማረ ህልሙን ለማሳካት የሚያስችለውን ስልጠና እያገኝ መሆኑን ተናግሯል።
አትሌቱ ዕድሜያቸውን ታሳቢ ያደረገ ሥልጠና እየወሰድን ነውም ብሏል። ይህ ማለት ግን በማዕከሉ ነገሮች አልጋ በአልጋ አለመሆናቸውን አትሌት አማረ ይናገራል። የመሮጫ መም (ዋነኛ የማዕከሉ ችግር ነው ብሏል አትሌቱ።
በአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከሉ የረጅም እና መካከለኛ ርቀት አሠልጣኝ የሆነው ኃይሉ አማረ የሠልጣኞች እንቅስቃሴ እና አቀባበል ጥሩ ቢሆንም የስፖርት መሰረተ ልማቶች ጉድለት እንዳለ ግን ያስረዳል። በማዕከሉ የመሮጫ መም ባለመኖሩ ውድድር ላይ እየተቸገርን ነው ብሏል። የሚፈልጉትን ዕቅድ ውጤታማ በሆነ መልኩ በአጭር ጊዜ ለማሳካት አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳረፈባቸው እንደሆነም ጭምር ነው አሠልጣኙ የተናገረው።
በተጨማሪም ለሜዳ ተግባራት የሚውሉ የስፖርት ቁሳቁስ እጥረት እንዳለም አሠልጣኙ ጠቁሟል። እንደ አሠልጣኝ ኃይሉ አማረ ማብራሪያ የጦር ውርወራ፣ የመዶሻ እና አሎሎ ውርወራን ለመሳሰሉት የስፖርት ቁሳቁስ ችግሮች አሉ።
የብዙዎቹ የሀገራችን የትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላት እና ክለቦች ችግር የሆነው የመሮጫ መም ችግር በወሎ ዩኒቨርሲቲ በተንታ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ሠልጣኞች እና አሠልጣኞችም በተደጋጋሚ የሚነሳ መሆኑን የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሀመድ አለባቸው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ይህን ትልቅ ችግር የተገነዘበው ወሎ ዩኒቨርሲቲ የመሮጫ መም ለመሥራት በቀጣይ አዲሱ ዓመት ዕቅድ መያዙን አቶ ሙሀመድ ነግረውናል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባሳለፍነው ግንቦት ወር ለአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላት፣ ፕሮጀክቶች፣ ለክልል እና ለከተማ አሥተዳደሮች የትጥቅ ድጋፍ ሲያደርግ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ለተንታ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከልም የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል። ነገር ግን ይህ በቂ ስላልሆነ አሁንም ከሌሎች ተቋማት ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል ነው የተባለው፡፡
የጅምናዚየም፣ የስፖርት ቁሳቁስ፣ ቋሚ በጀት እና ሌሎችም መሰረት ልማቶችን ለማሟላት ወሎ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ሊያግዙን ይገባል ብለዋል። አሁን ላይ ማሠልጠኛ ማዕከሉ በክለቦች፣ ሥራ አስኪያጆች እና በደላሎች የዕይታ ራዳር ውስጥ ገብቷል። ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋርም ገና ከወዲሁ ውል ወይም ስምምነት እየተፈራረሙ ነው ተብሏል።
ይህ ደግሞ በአትሌቶች እና አሠልጣኞች ዘንድ ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ ሲሆን የበለጠ ለመሥራት ስንቅ እንደሆናቸው ተናግረዋል። በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተንታ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል የመጀመሪያ ዙር ሠልጣኞች አራት ዓመት ሞልቷቸው የሚወጡት በ2017 ዓ.ም መጨረሻ ነው።
ሠልጣኞች በማዕከሉ የሥልጠና ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲወጡ ከወዲሁ የተሻለ አቅም ይዘው እንዲወጡ እየተሠራ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ሙሀመድ አለባቸው ተናግረዋል። ከዚህ ባሻገር ግን ክለቦች ገና ከወዲሁ ወደ ማዕከሉ መጥተው አትሌቶችን እንዲወስዱ ጥረት እያደረጉ መሆኑ ተገልጿል። ንግድ ባንክ፣ መቻል እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን የመሳሰሉትን ታላላቅ የአትሌቲክስ ክለቦች ፍላጎት አሳይተዋል ብለዋል ሥራ አስኪያጁ።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተንታ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ረጅም ጊዜ ከቆዩት እና በሀገራችን ቀዳሚ ከሆኑት ከበቆጂ፣ ቦሬ፣ ሀገረ ሰላም እና ደብረ ብርሃን የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላት ባልተናነሰ የተሻለ አቅም ላይ ይገኛል። ማዕከሉ ይበልጥ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራትም በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ከአሚኮ የበኲር ስፖርት ዝግጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት የማሠልጠኛ ማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሀመድ አለባቸው ተናግረዋል።
ወሎ ዩኒቨርስቲ ለአትሌቲክስ ማዕከሉ እያደረገ ያለው ድጋፍ ለሌሎች ተቋማትም አርያ በመሆኑ የሚበረታታ ነው። ይህ ደግሞ አትሌቶች እና አሰልጣኞች ሥራቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያድርጉ ያስችላል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም