ልቦለድ
እንደ ልማዴ ሶፋ ላይ ቁጭ እንዳልሁ ቴሌቪዥን ላይ አፍጥጫለሁ:: ማፍጠጥ ስላችሁ ግን አንድ ጣቢያ ላይ የረጋሁ እንዳይመስላችሁ:: አንድ ጣቢያ ላይ ረግቶ መመልከትማ የሰው ልጅ ወግ ነበር:: አንድ ጣቢያ ላይ ብረጋ ኖሮማ ያው መቼም ዜናው ሁሉ በጠላትነት ተፈራርጆ የዘራሰብን መጨራረስ ከማርዳት ብዙም የራቀ ባይሆንም የኛይቱን ጉደኛ ሀገር ጦቢያን ጨምሮ የዚችን ጣጠኛ ዓለም ውሎ ባወቅሁ፤ አንዳች ቁም ነገር በጨበጥሁ፤ አልያም የደከመ አእምሮየን ዘና ባደረግሁ ነበር:: ሆኖም አንዱ ላይ ለደቂቃ እንኳን መቆየት ተስኖኝ ከጣቢያ ጣቢያ እየዘለልሁ ምኑንም ሳልጨብጠው እንዳፈጠጥሁ አለሁ::
በድርጊቴ የተናደደች የምትመስለው ልጄ ሶስና ፊት ለፊቷ ሸራዋን ዘርግታ ከምትጠበብበት የሥዕል ሥራዋ ዐይኖቿን እየነቀለች ሰርቃ ስትመለከተኝ በጐን ዓያታለሁ:: እንዲህ እየደጋገመች እኔን የመመልከቷ ምስጢር ቢገባኝም ከድርጊቴ ግን ልታቀብ አልቻልሁም:: ልጄ ሶስና ካሁን አሁን አንዱ ጣቢያ ላይ ያርፋል ብላ ተስፋ ብታደርግም ተስፋዋ ከተስፋነት አልዘለለም:: እናም እየሰረቀች ስትመለከተኝ ቆይታ፤ “አባዬ!” ስትል ጮክ ብላ ጠራችኝ::
“እናቴ!” በማለት ለጥሪዋ መልስ ሰጠኋት:: ዓይኖቿን ቴሌቪዥኑ እንዲሁም እጄ ላይ እያሳረፈች፣ “ምን እያደረግህ ነው?” አለችኝ::
እኔም ምንም እንዳላደረገ ሰው፣ “ምንም!” ስል መለስሁላት::
“ሪሞቱን ይዘህ ቲቪው ላይ አፍጥጠህ እንደተቀመጥህ ከቻናል ቻናል መቀያየር ከጀመርህ እኮ ካንድ ሰዓት በላይ ሆነህ!” ምነው አንዱ ላይ መርጋት አቃተህ?! እኛን ሞባይል አትጐርጉሩ! ትምህርታችሁ ላይ አተኩሩ!.. አጥኑ!.. አንብቡ!…” ትለን የለም እንዴ?! እኛን እየመክርህ…”
“እሽ! አንዱን ጣቢያ መርጨ ልመልከት!” በማለት ዓይኔን ወደ ቴሌቪዥኑ ስመልስ የቀለም ብልቃጧን እየከነደች፣”ተነስ!… ተነስ!…” አለችኝ::
“ለምን?!…” ግራ ተጋብቼ ጠየቅኳት::
“ወደ ንባብ ከተማ እንሂድ!” አለችኝ፤ ጠይም ክብ ፊቷ በደስታ በርቶ::
“የምን የንባብ ከተማ ነው?!”
“አልሰማህም እንዴ?!”
“ምኑን?!”
“ከተማችን ከሱስ ከተማነት ወደ ንባብ ከተማነት መቀየሯን!”
“ከመቼ ጀምሮ?!”
“ ከዛሬ ጀምሮ!”
“እኔ ይሄን አላምንም!”
“እመነኝ! ተቀይራለች!”
“እኮ ይህቺ እኛ የምንኖርባት ከተማ?!”
“አዎ! የምንኖርባት ከተማ! ይልቅ ተነስ!… ተነስ!… ተነስ!…”
“ተለወጠች የተባለችውን አዲሷን ከተማችንን ለማየት ጓጉቼ ከተቀመጥሁበት ተስፈንጥሬ ተነሳሁና ቁም ሳጥኔን ከፍቼ የወትሮየ ባልሆነ ፍጥነት የክት ልብሴን ለባብሼ ረዥሙ መስታዎት ፊት ቆምሁ:: የለበስሁት ጠቆር ያለ ሰማያዊ ሙሉ ሱፍ እንዲሁም ነጭ ሸሚዝ፣ ያሰርሁት ጥቁር ከራባት፣ የተጫማሁት ሹል ቴክስ ጥቁር ጫማ ተደማምረው ሙሽራ አስመስለውኛል::
ሶሲም ክፍሏ ገብታ ለባብሳ፣ ረዥም ፀጉሯን ግራ ቀኝ በትከሻዋ ነስንሳ ከመቼውም ጊዜ በላይ አምራና ተውባ መጣች:: ጣቶቿን አፏ ላይ አሳርፋ፣”ዋው!..አባዬ!… እንዴት ነው ያማረብህ!… ማሚ ብታይህ ከቤት አታስወጣህም!…” አለችኝ::
“አንቺም እኮ ልዕልት ሆነሻል!… ረዥም ፀጉርሸ፣ ቢጫ ቲሸርትሽ፣ ሰማያዊ ጅንስ ሱሪሽ፣ ባለተረከዝ ጫማሸ!… ተባብረው የቆንጆዎች ቆንጆ፣የልዕልቶች ልዕልት አድርገውሻል” አልኳት በስስት እየተመለከትኋት::
“ይሄ ካስቀያሚነት ወጥታ በድንገት እጅግ የሚያምር ገጽታን ለተላበሰችው ውቧ የንባብ ከተማችን የሚገባ አለባበስ ነው:: ከተማችን ባንድ ዕለት ከጫት፣ ከቁማር፣ከጃንቦ… ከተማነት ወደ ንባብ ከተማነት ስትቀየርልን፣ ስታምርልን፣ እኛ ከደከረትን ገጽታዋን ማበላሸት ነው የሚሆንብን:: እናም እንዲህ ቢያምርብን ቢያንሰን እንጂ አይበዛብንም!” ስትል ያለባበሳችንን ምክንያታዊነት ልታስረዳኝ ሞከረች::
“ሶሲ የተናገርሽው እውነት ነው:: ማማር…” ንግግሬን ሳልጨርስ ባለቤቴ ሳምራዊት፣ “አባት እና ልጅ ምንድነው የምትዶልቱት?!” እያለች ገባች:: ከልብ በመነጨ የደስታ ስሜት ሁለታችንንም ላፍታ ከላይ እስከ ታች ስትመለከተን ቆየችና፣ “ሆሆይ!… ደግሞ እንዴት ነው ያማረባችሁ?! ወዴት ለመሄድ ነው እንዲህ ሽክ ያላችሁ?!…” እየተገረመች ጠየቀችን::
“በድንገት ያማረች የተዋበችውን የንባብ ከተማችንን ልንጐበኝ!… አንቺም ቶሎ ለባብሽና አብረን እንጐብኛት!” ሶሲ በደስታ እየተፍለቀለቀች መለሰችላት::
“የንባብ ከተማ ነው ያልኸኝ?! አሁን እኮ ጐረቤት ቆይቼ ወደ ቤት ስመጣ ካንድም ሁለት ሦስት ሰዎች አንዳንድ መጽሐፍ ይዘው አየሁ:: እንግዳ ነገር ስለሆነብኝ እንደሞኝ ቆሜ ሳስተውላቸው ቆይቼ ወደ ግራ ታጥፈው ካይኔ ሲሰወሩብኝ ወደ ቤት ገባሁ:: ምንድነው ነገሩ?!” ባየችው ያልተጠበቀ ለውጥ በመገረም ጠየቀችን::
“አይ እማዬ!… አልሰማሽም እንዴ ከተማችን እኮ ከመጠጥ፣ ከቁማር፣ ከጫት… ከተማነት ወደ ንባብ ከተማነት ተቀየረች:: “
“እኛም እንደሰለጠነው ዓለም አንባቢ ልንሆን?!”
“አዎ!…
“እኮ እንዴት?!”
“መንግሥት አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር አቅዶ ቀን ከሌሊት ሢሠራ ኖሮ መንገድ ዘግቶ መጠጥ ማንጫለጥን፣ቁማር መቆመርን፣ ጫት መቃምን… በመከልከል ዛሬ በይፋ ከማተችንን ወደ ንባብ ከተማነት ቀየራት!” አለች ሶሲ ሳምሪን እየተመለከተች::
“እንዴት ደስ ይላል!” አለች ሳምሪ በድጋሜ ከላይ እስከታች እያስተዋለችን::
“ሰው ከጧት እስከ ማታ ብርጭቆ እና ጠርሙስ ከመጨበጥ ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ መጽሐፍ.. ወደ መጨበጥ ተሸጋግሮ ማየት በርግጥም ደስ ይላል፤ ያኮራልም:: በመጠጥ፣ በቁማር፣ በጫት… ሱስ ተይዞ ኪሱ ተራቁቶ፣ ህሊናው ደንዝዞ፣ ቤቱ ያለ ጥሪት ቀርቶ… ጐጆውን ያፈራረሰ፣ ልጆቹን የበተነ፣ ይይዝ ይጨብጠውን ያጣ… ስንቱ ነው!… ዛሬ ሶሲ መጣ የምትለው ለውጥ እኮ ይሄን ሁሉ ስር የሰደደ ውስብስብ ችግር የሚያስቀር ነው:: ይሄን ለውጥ ማየት ታላቅ ደስታ ነው:: ይሄን ደስታ አብረን ማየት አለብን፤ ለባብሽና አብረን እንሂድ!” ልጃችን መጣ ያለችንን ለውጥ ፋይዳ አጉልቼ በማሳየት ሳምሪ ለውጡን አብራን እንድታይ አኔም ጠየቅኳት::
“አብሬ ብሄድ ደስ ይለኝ ነበር:: ሆኖም ሰፈር የታመመ ሰው ልንጠይቅ ከተዋበች ጋር ልንሄድ ነው:: እናንተ ሂዱ፤ እኔ ደግሞ ነገ ዓያታለሁ፤ የት ትሄድብኛለች!…” ሳምሪ አብራን መሄድ እንደማትችል በምክንያት አስረግጣ ነገረችን:: እኔ እና ሶሲም ሳምሪ አብራን ባለመሄዷ ቅር እያለን የንባብ ከተማችንን ለመጐብኘት ወጣን::
ሶሲ መጣ ያለችው ለውጥ እውነት መሆኑን በማረጋገጥ በደስታ ስሜት እንደ ሕፃን መፍለቅለቅ የጀመርሁት ገና ከሰፈራችን ሳንወጣ ነበር:: በሰፈራችን ስናልፍ ጋዜጣ፣ መጽሔት እንዲሁም መጽሐፍ የያዙ እግረኞችን፣ ሱቅ ደጃፍ፣ መኪና ውስጥ፣ መንገድ ዳር ተቀምጠው የሚያነቡ ሰዎችን ተመለከትን:: በማየው ነገር እየተገረምሁ ሳለ ሶሲ፣ “ዓየህ አይደል አባዬ! ባንድ ቀን ሰው ሁሉ ምን ያህል አንባቢ እንደሆነ!” አለችኝ፤ ሱቅ ደጃፍ ተቀምጠው ጋዜጣ እንዲሁም መጽሐፍ ወደሚያነቡ ሰዎች እየተመለከተች፤ በመገረም:: ሰዎቹን ዕያየን እየተደመምን ባለንበት ቅጽበት መጽሐፍ የያዘ ወጣት በፊታችን አልፎ ሲሄድ ተመለከትን:: በዚህ ተገርመን ሳናበቃ ሌላ ወጣት ከእኛ ትንሽ አልፍ ብላ ከቆመች መኪና ዳጐስ ያለ መጽሐፍ ይዞ ሲወርድ ዓየን::
በምናየው ለውጥ እየተደመምን እና እየተደሰትን ታክሲ ተራ ደረስን:: ተሰልፎ የታክሲ ወረፋ ከሚጠብቀው ሰው አብዛኛው የሚነበብ ነገር ይዞ ይታያል::
ከታክሲ መሳፈሪያው ግራ ቀኝ ያሉ ጃንቦ ቤቶች እንዲሁም የመጠጥ መደብሮች ለወትሮው በጠጪ ተጣበው ይታዩ እንዳልነበር ወደ መጻሕፍት መሸጫነት ተቀይረዋል:: ሰውም መጽሐፍ ለመግዛት ሰልፍ ይዟል:: እጄን አፌ ላይ ጭኜ፣ “ወቼው ጉድ!… ደስ ሲል !… “ ስል ሶሲ ኮቴን ሳብ ሳብ እያደረገች፣ “አባዬ እኔ እና አንተ ብቻ እኮ ነን መጽሐፍ ያልያዝን፤ ኧረ ያሳፍራል!… “ ስትል ከተደምሞየ አናጠበችኝ:: ጊዜ ሳናጠፋ ተሰልፈን አንዳንድ መጽሐፍ ገዛንና ካንባቢው ሕዝብ ጋር ተመሳሰልን:: ከዚያም 10፡00 ሲል ታክሲ ውስጥ ገብተን ወደ መሀል ከተማ ጉዞ ጀመርን::
ከተሳፈርንባት ታክሲ ውስጥ ካለውም ሆነ በመስኮት ከምናየው ሰው ውስጥ አመዛኙ ጋዜጣ፣ መጽሔት ወይም መጽሐፍ ይዞ ይታያል:: የሚያነበው ሰው ቁጥርም ቀላል አይደለም:: ሌላው ይቅርና ለወትሮው ምድረ ጠጪ ገበያተኛ መስሎ መንገድ ዘግቶ እየተንጫጫ መጠጥ ይጨልጥባቸው የነበሩ መንገዶች ሁሉ ወደ ማንበቢያነት በመቀየራቸው ፀጥታ ሰፍኖባቸዋል:: በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ዳር እንዲሁም አደባባዮች ላይ ጋዜጣ፡ መጽሔት እንዲሁም መጽሐፍ የሚያነቡ ሰዎች ትልልቅ ፎቶ ግራፍ ተሰቅሎ ይታያል:: ከግርጌያቸው ደግሞ፣ “ማንበብ ምሉዕ ሰው ያደርጋል! አንባቢ ትውልድ ሀገርን ወደ ሥልጣኔ እና ዕድገት ጐዳና ያሻግራል! አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር አንጣር!…” የሚሉ ልብን በሀሴት የሚያሞቁ ወርቃማ ጥቅሶች ተለጥፈዋል::
ሶሲ ጥቅሶቹን ባነበበች ቁጥር፣ “አባዬ!… ደስ አይልም?!…ዋው!…” እያለች ደስታዋን ትገልጻለች:: እኔም ዓይኖቼ ጥቅሶቹ ላይ እንደተተከሉ፣ “በጣም!… በጣም እንጂ ልጄ!… ከዚህ በላይ ምን ደስታ አለ?!…” እያልሁ በደስታ ስሜት እመልስላታለሁ::
ሶሲ እና እኔ ወደ ንባብ ከተማነት የተለወጠችውን ከተማችንን በደስታ ባሕር እየዋኘን ስንጐበኝ እግራችን ለወትሮው ሰው ማለፊያ አጥቶ እስኪቸገር ድረስ መንገድ ተዘግቶ ጃንቦ እንደ ክረምት ወንዝ ይፈስባቸው፣ ቢራ ባይነት ይጨለጥባቸው… ከነበሩ በቀኝም ሆነ በግራ መደዳውን ከተደረደሩ ቤቶች መሀል አደረሰን:: እነሱም በሌሎች የከተማችን መጠጥ ቤቶች እንደተመለከትነው ያ የድሮ አስቀያሚ መልካቸው ፍጹም ተቀይሯል:: መንገዱ ነፃ ወጥቶ አላፊ አግዳሚው ያለ ችግር፣ ያለሰቀቀን እንደልቡ ይተላለፍባቸዋል:: ጫት እና ቁማር ቤቶች ወደ ጋዜጣ፣ መጽሔት እንዲሁም መጽሐፍ መሸጫነት ተቀይረዋል፤ ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣ ወንዱ፣ ሴቱ.. እንደምርጫው የሚነበብ ነገር እየገዛ ያነባል::
ሶሲ እና እኔ ባድናቆት እንዲሁም በደስታ… እንደሰከርን ቅንጣት ድካም ሳይሰማን የንባብ ከተማችንን በእግራችን አዳረስናት::
እግራችን በደረሰበት ሁሉ የምናየው ተመሳሳይ ለውጥ ነው:: ቁማር ቤቶች፣ ጫት መሸጫ እና መቃሚያ ቤቶች… ሳይቀሩ ወደ ቤተ መጻሕፍትነት ተቀይረዋል:: መናፈሻዎች ባንባቢዎች ተሞልተዋል:: እዚህም እዚያም ሰው ድንገት በመጣው ለውጥ የተሰማውን ከልብ የመነጨ ደስታ ሲገልጽ ይደመጣል:: “ፈረንጅ አነበብሁ አይበል! ድንቄም እቴ አንባቢ!… ኧረ አንባቢስ ጦቢያዊ!… ኧረ አንባቢስ ሀበሻ!… እንዲህ ካነበበ ማነው ሀበሻን በዕድገት፣ በሥልጣኔ… የሚደርስበት?!…” እያለ በኩራት ይናገራል::
“ምስጋና እና ክብር ይሄን ለውጥ ላመጡልን ወገኖች ሁሉ ይድረሳቸው!” በማለት መልካም ምኞቱን የሚገልፀውም ብዙ ነው:: አንዳንዱ ደግሞ ለውጡ በማን እንዴት ሊመጣ እንደቻለ አጠገቡ ያለውን ሰው ይጠይቃል:: ጥያቄው የቀረበለት ሰውም፣ “መንግሥት ነዋ! ሌላ ማን ሊሆን ይችላል!…” ሲል በኩራት እና ባድናቆት ይመልሳል::
“እኮ እንዴት መንግሥት ይሄን ለውጥ ሊያመጣ ቻለ?!” ሌላው ያየውን ለማመን እየተቸገረ ይጠይቃል::
“ከተማችንን ወደ ንባብ ከተማነት የመቀየር ጉዳይ መንግሥት ሳይሠራው ለዓመታት ሲንከባለል የኖረ የቤት ሥራ ነው:: ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ የሆነው መንግሥታችን እስከ ዛሬ ይሄን የቤት ሥራውን ቀድሞ መሥራት ነበረበት:: ሕዝብ በየጊዜው፣ “ ቁማር ቤቶች፣ ጫት ቤቶች፣መጠጥ ቤቶች… ተስፋፉ! ከተማችን የሱስ ከተማ እየሆነች ነው! ልጆቻችን በሱስ ተጠመዱ! ይህቺ ሀገር በንባብ የጐለመሰ፣ ከሱስ ነፃ የሆነ ተረካቢ ትውልድ አጣች!.. ኧረ መላ ዘይዱ!…” እያለ ስጋቱን ሲገልጽ፣ ሲወተውት፣ ሲማጸን ኖሯል:: ይህን ለውጥ ሲሻ የኖረ ሕዝብ መንግሥት ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ሲነሳ የተጠየቀውን ድጋፍ እንዲሁም ትብብር የማያደርግበት ምን ምክንያት ይኖራል? ሕዝብ ከተባበረ እና ከደገፈ ደግሞ ምን የማይሳካ ነገር አለ?!…” እያለ በማብራሪያ የተደገፈ መልስ ይሰጣል::
ይህን ታላቅ ለውጥ ዕያየን እና እያደነቅን፣ የሰውን ደስታም እየተጋራን ከከተማዋ ትላልቅ አደባባዮች ወደ አንዱ ተቃረብን:: በአደባባዩ መሀል ግዙፍ ቴሌቪዥን ተሰቅሏል:: ለወትሮው ቴሌቪዥኑ ሲለፈልፍ ውሎ ሲለፈልፍ ቢያመሽ ዞር ብሎ የማያየው ሰው ሁሉ ዛሬ ከቦ አንጋጦ ይመለከተዋል:: እኛም ሰው የሚያየውን ለማየት የርምጃችንን ፍጥነት ጨምረን ወደ አደባባዩ ተጠጋንና ቴሌቪዥኑን መመልከት ጀመርን፡ የከተማችን ከንቲባ አቶ ላቃቸው ሙሀመድ በከተማችን ስለመጣው ለውጥ በቀጥታ ስርጭት መግለጫ በመስጠት ላይ ናቸው:: ሰው ሁሉ አፉን እና ዓይኑን ባድናቆት ከፍቶ ያዳምጣል፤ “በከተማችን ጫት ቤቶች፣ ቁማር ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች አለቅጥ ተስፋፍተው ከተማችን የሱስ ከተማ ሆና ቁጥሩ ቀላል የማይባል ወጣት ከጧት እስከ ማታ ጊዜውን እንዲሁም ገንዘቡን በጫት እና ቁማር እያጠፋ፣ የጃንቦ ብርጭቆ እንዲሁም የቢራ ጠርሙስ ጨብጦ እየዋለ ሀገራችን ተረካቢ ትውልድ የማጣት አደጋ ተደቅኖባት ኖራለች:: ወጣቱን መክሮ እና ተቆጥቶ ወደ መልካም ቦታ የመመለስ ኃላፊነት ያለበት ብዙ ጐልማሳ እንዲሁም አዛውንት ሳይቀር በመጠጥ ሱስ ተጠምዶ መጠጥ ሲጨልጥ ውሎ ያመሻል::
“ይህን ችግር ስር ሳይሰድ የመቅረፍ ጉዳይ ቀደም ብለን ልንሠራው የሚገባ የቤት ሥራችን ነበር:: ሀገር ትደግ፣ ትበልጽግ፣ ትሠልጥን… ከተባለ ከጫት፣ ከቁማር፣ ከመጠጥ… ሱስ ነፃ የሆነ እና ራሱን በንባብ ያበቃ ትውልድ ማፍራት ግድ ይላል:: ለዚህ ደግሞ ከተማችን ከሱስ ከተማነት ወደ ንባብ ከተማነት መለወጥ አለባት:: ይህ ደግሞ የሕዝባችን የረዥም ጊዜ ጥያቄ ሆኖ ዘልቋል:: መንግሥታችንም ይህን የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ አቅዶ ሌት ከቀን ሢሠራ ኖሯል:: እነሆ ዛሬ በጥረታችን ከተማችንን ከሱስ ነፃ አውጥተን ወደ ንባብ ከተማነት አሸጋግረናታል:: እንኳን ደስ አለን! እንኳን ደስ አላችሁ!” ሲሉ አንጋጦ ንግግራቸውን ሲያዳምጥ የነበረው ሕዝብ በደስታ ጩኸት እና ጭብጨባ አካባቢውን አደባለቀው:: እኔ እና ሶሲም ደስታችንን መቆጣጠር ተስኖን ባለ በሌለ ኃይላችን እየጮህን እና እጃችን እስኪቃጠል እያጨበጨብን፣ እየዘለልን… ደስታችንን ስንገልጽ ከእንቅልፌ ብንን አልሁ፤ ድቅድቅ ጨለማም ተቀበለኝ:: የራስጌየን መብራት አበራሁ፤ ሳምሪ ከጎኔ እንደተኛች እንደመንቀሳቀስ አለችና እንቅልፏን ቀጠለች:: ዓይኖቼ ተወርውረው ፊት ለፊቴ ከተሰቀለው የግድግዳ ሰዓት ላይ አረፉ፤ ከሌሊቱ 9፡10 ይላል::
(አባትሁን ዘገየ)
በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም