የክረምት ወቅት የጤና ስጋቶች

0
232

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሰኔ 5 ቀን 2016 ዓ.ም የክረምቱን ወቅት ተከትለው ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ስጋቶችን አስታውቋል:: የኢንስቲቱዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በክልሉ በቀጣይ ስድስት ወራት ሊከሰቱ የሚችሉ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ሲያስታውቁ፣ በሽታዎቹ ሊያስከትሉት የሚችሉትን ሰብዓዊ ኪሳራ እና ምጣኔ ሐብታዊ ጉዳት ለመቀነስ ሁሉም ትኩረት እንዲሰጥ ለማንቃት ነው::

ከጦርነት፣ ከግጭት፣ ከድርቅ፣ ከሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ዓለም አቀፍ  ስደተኞች ጋር ተያይዘው በሽታዎች ሊከሰቱ እና ሊባባሱ እንደሚችሉ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል:: ወባን ጨምሮ ኩፍኝ፣ እከክ፣ ኮሌራ፣ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፈው አባ ሰንጋ (አንትራክስ)፣ አጣዳፊ የምግብ እጥረት፣ ማጅራት ገትር፣ የደም ተቅማጥ፣ የእብድ ውሻ በሽታ እና ሌሎችም ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች የቀጣይ ወቅቶች ስጋት ሆነው በኢንስቲትዩቱ ተለይተዋል::

የወባ በሽታ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የወባ በሽታ ስርጭት እና የሞት መጠን ከፍተኛ ቁጥርን የሚይዘው የአፍሪካ አህጉር እንደሆነ የአፍሪካ አቀፍ የወባ ቁጥጥር ማኅበር እና የጤና ሚኒስቴር መስከረም 4 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ መረዳት ይቻላል:: በዚህ ወቅት እንደተገለጸው በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋሉ የመጡት የፀጥታ ስጋቶች እና የአየር ንብረት ለውጦች ስርጭቱን ለመግታት ማነቆ ሆነዋል:: በተጨማሪም የወባ በሽታ በተለይ አርሶ አደሩ የግብርና ሥራዎችን በሚከናወኑበት ወቅት መከሰቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ያስከትላል:: የማኅበረሰቡ የግንዛቤ ክፍተቶችም ለችግሩ መባባስ ዋና ምክንያት ናቸው::

የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በመግለጫቸው እንዳስታወቁት ወባ አሁንም የአማራ ክልል ከፍተኛ የኅብረተሰብ ጤና ስጋት መሆኑን አስታውቀዋል:: በክልሉ ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የወባ ህሙማን የወባ ክትባት መሰጠቱን ለችግሩ ስፋት ማሳያ አድርገው አንስተዋል::

የወባ በሽታ በዚህ የክረምት ወቅትም አሳሳቢ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል አቶ በላይ ጠቁመዋል:: በሽታው በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ የሰው ሕይወትን እስከ መንጠቅ እንዳይደርስ ከወዲሁ ጠንካራ የዝግጁነት ሥራ መከናወን እንዳለበት ጠቅሰዋል።

ኢንስቲትዩቱ የችግሩን ስፋት ቀድሚ ከለየ በኋላ በሽታውን ቀድሞ ለመከላከል፣ ከተከሰተም ለማከም የሚውል ግብዓት ለማሟላት እየሠራ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። በሽታውን ለማከም የሚውሉ መድሃኒቶች በግሎባል ፈንድ በኩል በነጻ እየቀረበ መሆኑን ያስታወቁት ዳይሬክተሩ መድሃኒቶቹ ለታለመላቸው ወገኖች ብቻ እንዲውሉ ሁሉም ሕገ ወጥነትን እንዲከላከል ጠይቀዋል።

የበሽታውን ስርጭት ቀድሞ የመለየት ሥራ የሥርጭቱን ስፋት ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ዋናው መፍትሄ ሆኖ ይሠራበታልም ተብሏል። የአልጋ ላይ አጎበርን በጥንቃቄ እና በአግባቡ መጠቀምም ይገባል። እንደ ዳይሬክተሩ በ2015/16 ዓ.ም ከሦስት ሚሊዮን በላይ የአልጋ ላይ አጎበር ተሰራጭቷል። አሁንም ከበሽታው ስጋትነት አኳያ የተቀደደውን ሰፍቶ፣ የቆሸሸውን አጥቦ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዓመቱ ከፍተኛ የወባ ስርጭት በሚስተዋልባቸው 20 ወረዳዎች የቤት ውስጥ የጸረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት እንደሚከናወን ተመላክቷል። የኬሚካል ርጭት በሚከናወንበት ወቅት ሕዝቡ ተባባሪ እንዲሆን እና ኬሚካሎችም ለታለመላቸው አላማ ብቻ እንዲውሉ ሁሉም በኃላፊነት እንዲሠራ ተጠይቋል።

ማኅበረሰቡም የተለመደ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራን በልዩ ትኩረት በማከናወን የወባ በሽታ ሊያስከትል የሚችለውን ሰብዓዊ፣ ማኅብባዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ በመግታት በኩል አሻራውን እንዲያኖር ተመላክቷል። የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በዋናነት ወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ እና ውኃ ሊያቁቱ የሚችሉ ቦታዎችን ማዳፈን፣ ማፋሰስ፣ ውኃ ሊይዙ የሚችሉ የእቃ ስብርባሪዎችን ማስወገድ እና ሌሎች ሥራዎችን ያጠቃልላል።

ኮሌራ

የኮሌራ ወረርሽኝ አሁንም ከወባ በሽታ ቀጥሎ የክልሉ ሕዝብ የጤና ስጋት ሆኖ መቀጠሉን ኢንስቲትዩት አስታውቋል:: በ2016 ዓ.ም ኮሌራ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች መከሰቱ ይታወሳል:: ባለፈው ዓመት በምዕራብ ጎንደር ዞን በርሚል ጊየርጊስ ተቀሰቀሰ የተባለው ወረርሽኙ በርካቶችን ለሞት ማዳረጉ የሚታወስ ነው:: ወረርሽኝ በዚህ ዓመት ሚያዚያ ወር በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳድር ባቲ ወረዳ መከሰቱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል:: ችግሩ ሊያደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ጉዳት በከፍተኛ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እና ርብርብ መቀነስ ቢቻልም አሁንም ስጋትነቱ ስለመቀጠሉ ግን ጠቁመዋል:: በባሕር ዳር ከተማ ዙሪያ በሚገኙ አንዳሳ እና የአቡነ ሀራ አካባቢዎች ወረርሽኙ አሁንም ስለመኖሩ አስታውቀዋል:: በመሆኑም የሰሜን ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል::

በከተሞች የሚኖረው መተፋፈግ፣ ድርቅ የተከሰተባቸው አካባቢዎች፣ የተፈናቃይ መዳረሻዎች፣ ጸበል ቦታዎች አሁንም ለወረርሽኙ መከሰት እንደ ምቹ ሁኔታ ተመላክቷል:: በመሆኑም መጸዳጃ ቤት መጠቀም፣ የግል ንጽህናን መጠበቅ፣ ምግብን አብስሎ በትኩሱ መመገብ፣ ንጽህናው የተጠበቀ እና በኬሚካል የታከመ ውኃ መጠቀም ይገባል።

ለመሆኑ ኮሌራ ምንድን ነው? ኮሌራ ቫይብሪዮ ኮሌራ በተባለ ባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰት አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከትን በማስከተል በአጭር ጊዜ ለሞት የሚዳር በሽታ ነው።

ዋና መተላለፊያ መንገዱም የተበከለ ምግብ እና ውኃ በመጠቀም እንደሆ መረጃዎች ያሳያሉ:: የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ውስንነት ባለባቸው አካባቢዎች ወረርሽኙ በከፍተኛ ደረጃ ሲቀሰቀስ ይስተዋላል::

የኮሌራ ወርሽኝ በዋናነት ተቅማጥ እና ትውከትን በማስከተል በአጭር ጊዜ ለሞት የሚዳርግ አደገኛ በሽታ ነው። በመሆኑም ምልክቶችን ቀድሞ በማወቅ እና ፈጣን ሕክምና ማግኘት እንደሚገባ የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ:: የሩዝ ውኃ” የመሰለ ተቅማጥ፣ በተደጋጋሚ ማስመለስ፣ የሰውነት ፈሳሽ መቀነስ፣ ፈጣን የልብ ምት፣ ዝቅተኛ የደም ግፊት ዋና ዋና ምልክቶች ናቸው::

ተፈናቃይ ወገኖች እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች

በአማራ ክልል በተለያዩ የጸጥታ እና ሌሎች ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች ይገኛሉ:: ኢንስቲትዩቱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ላይ በልዩ ትኩረት ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፣ በተለይ በመጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ ወገኖች ላይ በሽታዎች ተከስተው የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ፣ ለሌላውም የማኅበረሰብ ክፍል ስጋት እንዳይፈጥር የጤና ክብካቤውን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል:: የዕለት ደራሽ ምግብ እና የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ባልተቆራረጠ ሁኔታ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል:: በድንኳን ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች መኖራቸውን ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፣ በመሆኑም እነዚህ ወገኖች ለዝናብ እና ለጎርፍ ተጋላጭ የማይሆኑበትን ደኅንነቱ የተጠበቀ  ካምፕ መሥራት እንደሚገባ፣ ለዚህም በዋናነት የሚመለከተው አካል ትኩረት አድርጎ ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል::

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስደተኞችን እያስተናገደች ትገኛለች:: በተለይ በሱዳን የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ በርካታ የሱዳን ስደተኞች ወደ አማራ ክልል እየገቡ መሆኑ ይታወሳል:: ከእነዚህም ዓለም አቀፍ ስደተኞች ጋር የተለያዩ በሽታዎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ለአማራ ክልል ሕዝብ ስጋት እንዳይሆኑ ከፌደራል ጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን  ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል::

በዓመቱ የክረምት ወቅት ሊከሰቱ ይችላሉ ተብለው ለተለዩ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች የሚያስፈልጉ የግብዓት አቅርቦት፣ የገንዘብ ድጋፍ እና ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አቶ በላይ ጠቁመዋል:: በአጠቃላይ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እንደሚከሰቱ እና እንደሚባባሱ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣  በመሆኑም የጤና ግብዓቶች ያለምንም ችግር ለተጎጂ ወገኖች እንዲደርሱ በግጭት ውስጥ የሚገኙ ሁሉም አካላት ትብብር እና ድጋፍ እንዲያደርጉ ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here