በሶቪዬት ሰራሽ የታንክ ሞተር የጐለበተ፣ አምስት ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝን፣ በክብደቱ ክብረ ወሰን የያዘ የሚሽከረከር ሞተር ሳይክል መሰራቱን ኦዳቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል::
የዓለማችን ከባዱ ሞተር ሳይክል ታሪኩ የሚጀመረው ከ2003 እ.አ.አ ነው:: ሁለቱ ቲሎ እና ዊልፍሬድ የተባሉ ወንድማማቾች በጀርመን የሞተር ሳይክል መሸጫ ነበራቸው:: ወንድማማቾቹ የሶቬዬት ቀዩ ጦር ምሽግ የነበረበት ስፍራ ሲፈራርስ ይመለከታሉ:: በጊዜው ተመተው የቆሙት ታንኮችን በመገጣጠም የተለየ ነገር መሥራት እንደሚችሉ አስበው እና ተስማምተው አሮጌ ታንክ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ:: ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶም አሮጌ ታንክ ማግኘት ቻሉ::
“T-55” የተሰኘውን አሮጌ ታንክ ወደ ቤት የወሰዱት ወንድማማቾች የሚሠራ ሞተር ያለው ታንክ አፈላልገው የተለያዩ ክፍሎቹን ቆራርጠው በመገጣጠም ከአንድ ዓመት በኋላ “ፓንዘር ባይክን” መሥራት ቻሉ::
አስገራሚው በሁለቱ ጀርመናዊ ወንድማማቾች የተሰራው ፓንዘር ታንክ አብዛኛው ክፍሎቹ ከሶቬየት ታንክ የተነቃቀሉ ነበሩ:: “38 ሺህ ሲሲ T 55” ሞተር የተገጠመለት ሞተር ሳይክሉ የፊት መብራቶቹ የድንበር ጠባቂዎች ባውዛ ሲሆኑ ከጐን ያለው የተሽከርካሪ ክፍል ከጦር ተሽክርካሪ የተነቀለ ነው::
የሀሳቡ አመንጪ ወንድማማቾች ለከባዱ ሞተር ሳይክል ኃይል ሰጪ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦዎችን ከጦር ኃይሎች ሆስፒታል ለህሙማን ደም መስጫ መሣሪያ ነው የተጠቀሙት::
ወንድማማቾቹ ከባዱን ሞተር ብስኪሌት ለመሥራት 5000 ሰዓታት ፈጅቶባቸዋል:: የተለያዩ የተቆራረጡ ክፍሎችን ለመበየድ ደግሞ 120 ኪሎ ግራም ሽቦ ተጠቅመዋል::
ከባዱ ሞተር ብስክሌት በ2007 እ.አ.አ ከባድ የሚሽከረከር ሞተር ብስክሌት ክብረ ወሰንን ይዞ ተመዘግቧል::
ሞተር ብስክሌቱንም ለማሽከርከር ሁለት ሰው ያሻል፤ ክብደቱ ክብረወሰን እንደያዘም 20 ዓመታት ሊደፍን መቃረቡን ልብ ይሏል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም