“ራስን ያልለወጠ ትምህርት ሀገር አይቀይርም”

0
173

የባሕር ዳር የኒቨርሲቲ የባህል ቋንቋ እና ኮሙዩኒኬሽን ኮንፈረንስ ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ (ፔዳ) ተካሂዷል::

ማህበረሰባዊ ለውጥ ለማምጣት ቋንቋ፣ ባህል፣ ትምህርት እና መገናኛ ብዙሃን የሚያደርጉት አስተዋጽኦ  ምንድን ነው ? በሚለው ዙሪያ የተለያየ ጥናታዊ ጽሑፍ ሲቀርብ የኮንፈረንሱ መሪ ቃልም “ማህበረሰባዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዙ ነገሮች ላይ አዕምሮን ማካተት” የሚል  ነበር::

የአውደ ጥናቱን ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉት የዕለቱ የክብር እንግዳ  ገጣሚ፣ ደራሲና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  መምህር እና ተመራማሪ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ  ስለ ማህበረሰባዊ እድገት ሲወራ መጀመሪያ ወደ አዕምሮ የሚመጣው ትምህርት እንደሆነ አንስተው ትምህርት መጀመሪያ የሚማረውን ግለሰብ፣ ቀጥሎ ማህበረሰብ፣ ከፍ ሲል ደግሞ ዓለምን ለመቀየር የሚያስችል መሣሪያ  እንደሆነ ገልጸዋል:: ይህም ሲባል ታዲያ ይላሉ  በድሉ ዋቅጅራ /ዶ/ር/ የተማረው ተምሮ መሆን የሚፈልገውን ነገር ከመሆኑ ውጭ ማህበረሰቡ ደግሞ ከሚማረው ሰው የሚጠብቃቸው ነገሮች ይኖራሉ:: እነዚህም  መጀመሪያ ሥራ እንዲይዝ  ቀጥሎ ደግሞ አካባቢውን እና ሀገራዊ ችግሩን እንዲፈታለት ነው የሚጠብቀው::

አሁን ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ የትምህርት ሥርዓታችን  በተግባር የታገዘ እና በክህሎት የተደገፈ ሳይሆን ንድፈ ሀሳብ ላይ  ያተኮረ በመሆኑ ተማሪዎች ክፍል ከመቁጠር በዘለለ ተምረው ሥራ የላቸውም፤ እየተማሩም ቀጥሎ ምን እንደሚሆኑ አያውቁም::

በዚህ ሂደት ነው  የትምህርት ሥርዓቱ የተማሪውን፣ የወላጅ እና የማህበረሰቡን ቀጥሎ ምን ሊያደርግ ይችላል የሚለውን ጥበቃ ያላሟላ ነው ለማለት የሚቻለው:: የትምህርት ስርዓታችን ማንነትን ማሳወቅ ብቻ ሳይሆን ለሚጠበቀው ህይወትም ማዘጋጀት እንዲቻል አድርጐ ሊሠራ እንደሚገባ ይገልፃሉ::

ጥራት ያለው መሠረታዊ ትምህርትን ማስፋፋትና በአጠቃላይ የህብረተሰቡን የማንበብና የመፃፍ ክህሎት ለማሻሻል ልዩ ጥረት መደረግ አለበት በሚል ትምህርት ላይ እየተሰራ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ቢያስታውቅም ዩኔስኮ በ2002 ዓ.ም በሁለተኛና ሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ የዝቅተኛ ክፍል ደረጃ የንባብ ደሰሳ ጥናት ተካሂዶ ነበር::  የተገኘውን ውጤት ስንመለከት ጥናቱ በመጀመሪያ ደረጃ አንደኛ ሳይክል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በቀጣይ ክፍሎች በአግባቡ ለመማር የሚያስችሉዋቸውን መሠረታዊ ክህሎቶች ያላዳበሩ መሆናቸውን አሳይቷል:: ለምሣሌ ሁለተኛ ክፍል ከሚማሩት ተማሪዎች 34 በመቶ ለደረጃው ከተዘጋጀው ምንባብ ውስጥ አንድም ቃል ማንበብ ሳይችሉ ቀርተዋል፤ ከተማሪዎቹ 48 በመቶው ከተዘጋጀው አንብቦ የመረዳት ፈተና አንዱንም መመለስ አልቻሉም፣ በተጨማሪ ከተማሪዎቹ መካከል በደቂቃ 60 ቃላትን አቀላጥፈው ማንበብ (ተማሪዎች በደቂቃ 60 ቃላት እንዲያነቡ ይጠበቅ ነበር) የቻሉት 5 በመቶ ብቻ ናቸው::

ዶ/ር በድሉ በ2014 ዓ.ም የአሜሪካ መንግሰት በኢትዮጵያ ትምህርት ላይ ያደረገውን ጥናት ሲጠቅሱም አራተኛ ክፍል ደርሰው ማንበብ እና መጻፍ የሚችሉ 23 ከመቶ ብቻ እንደሆኑ ሲያሳውቅ መገንዘብ የሚቻለው የትምህርት ሥርዓቱ ራስን በማወቅ በኩል ሊሠራበት እንደሚገባው የሚያሳይ እንደሆነ ነው የጠቆሙት::

የሥርዓተ-ትምህርቱ ተግባር ተኮር አለመሆን ሥራ ፈጣሪ የሆኑ ዜጎችን ከማፍራት፣ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎችን ከማበረታታት አንጻር እንዲሁም ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ አካትቶ ተግባራዊ በማድረግ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያ ሰፊ ክፍተቶች እንዲያሳይ ያደርገዋል።

ዶ/ር በድሉ  እንደሚሉት በተለይ በአሁኑ ወቅት ልጆቻችን ከማስተማር ውጭ ባሉበት ባህል፣ ከመገናኛ ብዙሀን፣ ከማስታወቂያ፣ ዜና እና ማህበራዊ ሚዲያ ከሚያዩት እና ከሚገነዘቡት ነገር ጋር ሁሉ ታግለን እንዴት ወደምንፈልገው መንገድ እንወስዳቸዋለን የሚለው ነገር አጽንኦት ተሰጥቶ ሊታሰብበት እንደሚገባ ነው የገለፁት::

ድሮና ዘንድሮ ሲነፃፀር ትውልድን ከመገንባት አንጻር የተሠራውን ሥራ ሲገመገም አሁን ላይ ያለው ትውልድ ባህሉን፣ወጉንና አገራዊ የማህበረሰብ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ በሚያየውና በሚሰማው በማይጠቅመን ዘመንኛ ዲጅታል ግንኙነት ስለቀየረው ትውልዱን የማዳን ሥራ መሰራት ይገባል።

ተግባቦትም ከባህልና ከቋንቋ ጋር መጣጣም እንዳለበትና አሁን ላይ በተጨባጭ ያለው የትምርት ስርዓት መቀየር ላይ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል::

ትውልድን ለሀገር ፍቅር እንዲኖረው  ትምህርት ለውጥ ሊመጣ የሚያስችለው ራስን ማሳወቅ እና እንዲለውጥ ማድረግ  ሲቻል ነው። ከታች ክፍል ጀምሮ ያለው የትምህርት ሥርዓቱን መቀየር ሲቻል ነው ለምሳሌ አንድ ተማሪ  ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ምን መሆን እንደሚፈልግ እና የሚጠበቅበትን ካወቀ፣ ከተማረ፣ ካስተዋለ ለውጥ ሊመጣ ይችላል::

አሁን እንዳለው ሁለተኛ ደረጃ ዩንቨርሲቲ ጨረሰ… ብቻ ከሆነ መማር እራሱ ለመጨረስ ብቻ ነው የሚሆነው::

ማንም ለራሱ በጎ ሲሰራ አገር ይለወጣል እንጂ ራሱን ያላወቀ ሥራ ያላገኘ ዜጋ ማንንም ሊለውጥ አንደማይችል መታወቅ እንደሚገባው ነው የሚያሳስቡት::

ምርምሮች ሲሰሩም በሀገርኛ ቋንቋ ሆነው በትክክል ተማሪው እና ችግር የሚፈታለት ማህበረሰብን ሊያግባባ እንደሚገባ ገልጸዋል::

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሂውማኒቲ ፋካሊቲ ዲን  ዶ/ር ዋልተንጉስ መኮንን በበኩላቸው ዩንቨርሲቲ የዕውቀት ተቋም በመሆኑ በማህበረሰቡ ችግሮቻችን ላይ ምርምር እየሠራ ችግሮች ተፈተው እንዴት ተመልሰው ወደ ማህበረሰብ ይተላለፋል የሚለውን ይሠራሉ ብለዋል::

መማር በራሱ ተነጥሎ የሚሄድ ነገር ባለመሆኑ ተማሪዎች ከትምህርት ተቋሙ ውጭ ማህበረሰቡን እየፈተኑ ያሉ ችግሮችን በማወቅ ለመፍታት የሚሄድበት መንገድ ምርምር በመሆኑ በዚህ ለችግሮች መፍትሄ ይመጣል የሚል ሃሳብ እንዳለ ነው የገለጹት::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here