ድምጻዊ ነዋይ ደበበ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ በድምጽ፣ በዜማ እና በግጥም ወጥ ሥራዎቹ ከ1970ዎቹ ምርጥ ድምጻዊያን ቀድሞ የሚጠቀስ ነው:: ከዚያ በፊት ሁሉንም የግጥም እና ዜማ ሥራዎች በራሱ ሰርቶ በዝነኛነቱ ጎልቶ የወጣ ድምጻዊ ማግኘት ከባድ ነው:: በ1990ዎቹ ደግሞ ቴዎድሮስ ካሳሁን በዚህ አቅሙ ጎልቶ ይጠቀሳል::
ወደ ነዋይ ደበበ ስንመለስ ከልጅነቱ ጀምሮ ትልቅ የዘፈን ልምምድ እና አቅም የነበረው ዘፋኝ ነው:: ዛሬ የደረሰበት የዝነኛነት ቦታ ላይ እንደሚገኝ ከራሱ በቀር ማንም ሰው የገመተ አይመስልም:: ታዋቂ ዘፋኝ የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው:: ግጥም ይጽፋል፤ ዜማ ይደርሳል እንዲሁም ያንጎራጉራል:: በወጣትነት እድሜው የሙዚቃ ካሴት ለመስራት በርካታ ሙዚቃ ቤቶችን ረግጧል:: ሰዎችን አነጋግሯል:: “ከአብዮት ዘፈን በስተቀር መዝፈን አትችልም፤ ድምጽህ ቀጭን ነው ለካሴት አይሆንም” በማለት እምቢ አሉት:: ከአሊ ታንጎ (አብደላ ኬፋ) ጋር የተገናኘበት አጋጣሚ ነው ነዋይ ደበበን ለአንጋፋ እና ተወዳጅ ኪነጥበበኛነት ያበቃው:: ከራሱ አልፎ ለብዙዎች ግጥም እና ዜማ ሥራዎችን ለሌሎች በመስጠት የኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ጉልህ አሻራውን አስቀምጧል::
የ ድሪም አት፣ ፒን ኢት፣ ሊቭ ኢት መጽሐፍ ደራሲት ቴሪ ሳቬል “ትላልቅ እቅዶቻችሁን ትናንሽ አዕምሮ ላላቸው ሰዎች አትናገሩ” ትላለች:: በዚህም ንዑስ አዕምሮ ያላቸው ሰዎች ሕልማችሁን ለማጥፋት ትልቅ ጉልበት አላቸው፤ በአንጻሩ ደግሞ ትላልቅ አዕምሮ ያላቸው ሰዎች ያላችሁን ትንሽ ሕልም ወደ ትልቅ ከፍታ እንድታደርሱት ያግዟችኋል በማለት ጽፋለች::
የሕልሞቻችን መሳካት በዙሪያዎቻችን ባሉ እና ሐሳቦቻችንን በሚጋሩ ሰዎች ይወሰናል:: አብረውን ጊዜ የሚያሳልፉ፤የነገ እቅዳችንን የምንነግራቸው፤ አትችለውም ይቅርብህ የሚሉን፤ የሚከብድህ ይመስለኛል የሚሉ፤ እስኪ ለማንኛውም ሞክረው እና አንተ ይህንን ማሳካት ትችላለህ ብለው ሐሳብ የሚሰጡን የቅርብም የሩቅም ሰዎች በሕልማችን ላይ ተጽዕኖ አላቸው:: ነዋይ ደበበ ካሴት ማውጣት አትችልም፤ ድምጽህ ቀጭን ነው ሲባል አርፎ ቢቀመጥ ኖሮ ዛሬ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ስሙን አንሰማውም ነበር:: “ና እስኪ ድምጽህን እንሞክረው ፣ ድምጽህን እናሻሽለው” የሚል ሰው ስለገጠመው አሁን ስለ ነዋይ ደበበ እንድናወራ አድርጎናል::
“ስኬታማ መሆን የምትፈልግ ከሆነ እቅድህን ለማንም አትናገር” በማለት ቫርቲካ ካሺያፕ ቢቢኤን ታይምስ ላይ ባሰፈረችው ሐሳብ፤ ሁልጊዜም በሕይወት ሁለት ዓይነት ሰዎች መኖራቸውን ትዘረዝራለች:: አንደኛው ወገን የሕይወት ግብ ያላቸው እና ላገኙት ሰው ሁሉ የሚናገሩ ናቸው:: ሁለተኛው ደግሞ የሕይወት ግብ ይኖራቸውና ሥራቸውን በስውር የሚከውኑ ናቸው:: ቫርቲካ ማንም ሰው የሕይወት ዓላማውን ከመናገር ይልቅ በጸጥታ አሳክቶ ውጤቱን ማሳየት አለበት በማለት ትመክራለች:: ስራዬን ዓለም ሁሉ ካላወቀልኝ ማለቱ ጠቀሜታው ምንድን ነው በማለትም ትጠይቃለች:: ሰዎች በራሳቸው መደገፍ ነው መቆም ያለባቸው:: ሁሉም ሰው መልካም ምኞትን የሚገልጽልን ላይሆን ይችላል:: እንደዚህ ዓይነት ተግባር ለመስራት አስቤያለሁ ስትላቸው ሰዎች ደስ ላይላቸው ይችላል:: አንድም ሰዎች በውስጣቸው ካለው ቅናት በመነሳት ወይም እንድትበልጣቸው ካለመፈለግ ነው:: “የእናንተ ጠንካራ መሆን የእነሱን ስንፍና እና ድንቁርና ስለሚያሳያቸው ደካማ ሰዎች አይደሰቱም” ትላለች ቫርቲካ:: እንዲያውም የጀመራችሁት ጉዳይ የማይረባ መሆኑን በመናገር መበለጣቸውን ለማካካስ የስም ማጥፋት እና ማጣጣል ዘመቻ ሊከፍቱባችሁ የሚችሉ ሰዎች አሉ:: የጀመራችሁት እቅድ እንዳልተሳካላችሁ፤ ሙከራችሁ ፍሬ እንደማያፈራ ይነግሯችሁ እና የራሳችሁን አቅም እንድትጠራጠሩ፤ እነሱ የሚሉትን አምናችሁ ተስፋ እንድትቆርጡ ያደርጓችኋል::
እቅዳችሁ እንዲሳካ የምትፈልጉ ከሆነ እነዚህን ሦስት ሰዎች መራቅ አለባችሁ ስትል ቫርቲካ ትናገራለች:: የመጀመሪያዎቹ የግላቸው ሕልም እና የሕይወት ዓላማ የሌላቸው፤ሁለተኛዎቹ አብዝተው የሚጠራጠሩ እና ሦስተኛዎቹ ተስፋ የቆረጡ እና ከምቾት ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ናቸው:: ሕልማችሁን እና እቅዳችሁን ለሰዎች በማብራራት ጊዜና አቅማችሁን አትጨርሱ ስትል ትመክራለች::
ሰዎች ለዓላማችን የሚኖራቸው ምላሽ እነሱ ካላቸው እውቀት እና የሕይወት መረዳት የሚነሳ ነው:: ደካማ አዕምሮ ያላቸው ሰዎች በድካማቸው ልክ ነው ሐሳብ የሚሰጧችሁ:: ዓለምን የለወጡ ሰዎች ምን ያህል ወቀሳ እና ማጣጣል እንደደረሰባቸው መገመት አይከብድም:: 999 ጊዜ አምፖልን ለማብራት የሞከረው ቶማስ ኤዲሰን ምን ያህል በሰዎች ውግዘት እና ሽሙጥ እንደደረሰበት አስቡት:: አምፖልን አበራለሁ ብሎ ሦስት ጊዜ የተሳሳተን ሰው እንዴት ነው የምንፈርድበት እና የምንተቸው? የሚሰራው፣የሚሳሳተው እሱ ሆኖ ሳለ ተመልካች ባላወቀው ነገር ሐሳብ ከመስጠት አይመለስም:: አይችልም፣ እብድ ነው፣ ቅዠት ነው፣አሁንስ አሰለቸን፣ አርፎ ቢቀመጥ፣ ወሬ ብቻ፣ አንድም ቀን አይሳካለት፣ እምጵ ማለት ( ከንፈር መምጠጥ)፣ ፍረጃ እና ተስፋ ማስቆረጥ እቅዳችንን ባወቁ ሰዎች ከሚደርሱብን መካከል ይጠቀሳሉ:: እኛ ለመስራት እውቀት የለንም፤ ስንፈርድ እና እንደዚህ ወይም እንደዚያ ቢያደርግ፣ ቢተወው አርፎ ቢቀመጥ በማለት ማጣጣልን እንመርጣለን::
ኤዲሰን ግን 999 ጊዜ አምፖል የማይሠራባቸውን መንገዶች ተረዳሁ እንጂ አልተሳሳትሁም በማለት ሙከራውን ቀጥሎ ጨለማውን ዓለም ብርሀን አበራበት:: ማሰብ ቀላል ነገር አይደለም:: ሐሳብን ስለምንፈራ ወደ ፍርደ ገምድልነት እናጋድላለን:: ብዙዎች ሕልሞቻቸውን መናገር ለማይገባቸው ሰዎች በመናገራቸው ምክንያት ካሰቡት አልደረሱም:: በሰዎች ነቀፌታ እና ትችት የተነቃቃው ወኔያቸው እንደበረዶ ቀዝቅዞባቸው ህልማቸው ተኮላሽቷል:: እናንተ ያሰባችሁትን ሌሎች አያስቡትም:: እናንተ የታያችሁ ለሌሎች አይታይም:: ህይወት ግለሰባዊ ኃላፊነት በመሆኑ ከራሳችሁ በቀር ማንም የእናንተን ሕልም ለማሳካት ጊዜም ሆነ ፍላጎት የለውም::ሕልምን ወይም ስራን ለሌሎች ማሳወቅ ደስ የሚያሰኝ ነገር ይኖረው ይሆናል:: አዕምሯችን በሰዎች ዘንድ የሚያስገኘው የመደነቅ እና የመወደድ ስሜት ለጊዜው ያስደስተናል:: ቀጥሎ በሚመጣው ትችት እና ወቀሳ ሳይደናበሩ፣ ብዙ ሳይኮሩ መቀጠል ግን ጥንካሬን ይጠይቃል::
ሰዎች ዓላማቸውን በብዙ ምክንያቶች ለብዙኀኑ ይፋ ሊያደርጉ ይችላሉ::ሌሎችን ለማነቃቃት፣ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ፣ የተሸናፊነት ስሜትን ለመደበቅ በማሰብ እና በሌሎችም ምክንያቶች የወደፊት ዕቅዳቸውን ይፋ ማድረጋቸው አይቀርም:: በአደባባይ አሳካዋለሁ በማለት የተነገረ እና የታቀደ የህይወት ግብ በከዋኙ በኩል ሰዎች ምን ይሉኛል፣ ሳያሳካው ቀረ እባላለሁ የሚል ስሜትን ይፈጥራል:: በዚህም ምክንያት የህይወት ዓላማን ለሰዎች ማሳመኛነት ሲባል ለማሳካት ከአቅም በላይ መሯሯጥ ይጀምርና ሰው ምን ይለኛል የሚል ፍርሃት ላይ ይጥላል:: እቅዳችንን ስናጋራ ጥሩ የደስታ ስሜት ይሰማን እና ሰውነታችን ዶፓሚን ሆርሞን ያመነጫል:: በማውራት ብቻ በሐሳብ እንረካለን::በዚህም አዕምሯችን ጉዳዩን አሳክተን እንደጨረስን ሊያታልለን እና ትኩረት ልናጣ እንችላለን:: በአደባባይ ስናወራ የሰሙን ሰዎች የተናገርነው አለመሳካቱን ባወቁ ቅጽበት እንደ ጉረኛ እና ውሸታም ይቆጥሩናል:: ይህም የጀመርነውን መንገድ ሳንጨርስ በጉዟችን መሐል ተዘናግተን እንድንቆም ያደርገናል:: ሰዎች ሲያደንቁን ትኩረት እና እውቅና እናገኛለን:: በዚያው ልክ ደግሞ ሰዎች ጉዟችንን አይተው ትኩረት ካልሰጡን ተስፋ ማጣት እና መሰልቸት ውስጥ እንገባለን:: ዳንኤል ሚድሰን ሚድስ ኦን ሶርት ድረ ገጽ ላይ ባሰፈረው ሐተታ የሕይወት ግብን ለሰዎች መናገር ከህዝቦች ባህል እና አኗኗር ጋር የሚያያዝ መሆኑን ይገልጻል:: በአሜሪካ ካፒታሊስት ባህል ግብን ማሳካት በህይወት የስኬታማ ሰዎች መገለጫ ሆኖ ስለሚወሰድ አደባባይ ላይ ጉዞን መናገር ይበረታታል:: በዚህም ማህበረሰብ ውስጥ አንድን ግብ አሳክቶ መታየት፣ ከአንድ ወደ ሌላ ስራ ማደግ የሚያስመሰግን ተግባር ነው:: በአንጻሩ በሩስያ እና ደቡብ ኮሪያ የግል ዓላማን በአደባባይ መናገር የራስ ወዳድነት፣ ሰውን የመናቅ ምልክት ተደርጎ ይታያል:: ራስ ላይ ማተኮር ለህብረተሰብ ምንም ግድ እንደሌለን ሊያስቆጥርብን ይችላል በማለት ዳንኤል ይናገራል::
ስራ ፈጣሪው ዴሪክ ሲቨርስ ዓለም አቀፍ የስኬታማ ሰዎች መድረክ በሆነው ቴድ ኤክስ ላይ እ.ኤ.አ በ 2010 ቀርቦ “የህይወት ግባችሁን ለማንም ይፋ አታድርጉ፣ እቅዳችሁን ለሰዎች ስታጋሩ ለማሳካት መክፈል የሚገባችሁን ጥንካሬ እንድታጡ ያደርጋችኋል” በማለት ተናግሮ ነበር:: በንግግሩም እቅዳችሁን ለሰዎች በተናገራችሁት መጠን የተሳካ እየመሰላችሁ በማውራት ብቻ ትረኩና ሳታሳኩት ትቀራላችሁ በማለት አብራርቷል:: መስራት እንደማውራት ቀላል አይደለም፣ ስኬት ብዙ ውጣ ውረድ ያለበት በመሆኑ በማውራት እንረካና ተግባሩ ላይ ቆመን እንቀራለን ይላል ዴሪክ ሲቨርስ:: ከድርጊቱ ወሬው ቀድሞ መምጣቱ ከእውነታ ጋር ተቃርኖን ያመጣል:: ወደ ስፖርት ማዘውተሪያ ሳይሄዱ ስለ መሄድ እንደ መናገር የሚታይ ተግባር ይሆናል:: ሰውነታችን ፣ጤናችን በሐሳብ ተለውጦ የደስታ ሆርሞን ዶፓሚን መንጭቶ በርካታ ውስጥ ሆነን ከቀናት በኋላ የመስራት ተነሳሽነትን እናጣለን እንደማለት ነው:: ሜክ ቤተር ድረ ገጽ የጀመርኸውን ተግባር፣ የገቢ መጠንህን፣ የፍቅር ግንኙነትህን፣ የበጎ አድራጎት ተግባራትን፣ የቀድሞ ስህተቶችህን፣ ፖለቲካዊ ወይም ሃይማኖታዊ አቋሞችን ለሰዎች ማሳወቅ ተገቢ አይደለም በማለት ይመክራል:: እቅድን ማጋራት ይህን ሁሉ ችግር የሚያስከትል ከሆነ እንደ እባብ ድምጽን ሳያሰሙ በስውር ማደግ እና ሳይገመቱ ውጤቱን ይዞ ድንገት ከች ማለት ብዙዎች አሳቢያን የሚናገሩት ጉዳይ ነው::
በአጠቃላይ እቅድህን ለሰዎች በምታጋራበት ጊዜ ትችት፣ ጥርጣሬ፣ ፍረጃ፣ ቅናት፣ ፉክክር ያድርባቸዋል:: ለዚህም በሐሳብ እና በድርጊታቸው ትኩረትህን ይበትኑታል፤ እንድትሳሳት ይገፋፉሀል:: አንዳንዶቹ አውቀው ሌሎቹ ደግሞ ሳያውቁ እቅድህ እንዲከሽፍ ያደርጋሉ:: ይህንን ተከትሎ ስለ እቅዶችህ ሰዎችን በማስረዳት ጊዜ ታባክናለህ::እቅዶችህን በመናገርህ የሰው ትኩረት አንተ ጋ ይመጣና ተጠያቂነት ይሰማሃል:: እነዚያን ግቦችህን ለማሳካት ከውጪ ግፊት ይመጣብሃል::እንደዚህ ብታደርግ፣ ያንን ለምን አደረግህ እያሉ ጣልቃ ይገቡብሃል:: የሰዎች ትኩረት እና መከታተል ነጻነት ያሳጣሃል:: በዚህም ምክንያት የውሸት ስኬት ስሜት እያዳበርህ፤ የውጪ ጫናዎችን ለመቋቋም ጊዜ እና አቅምህን ታባክናለህ::
ለሰዎች እቅድን መናገር ጉዳዩ ምንድን ነው እና ሰዎች እነማን ናቸው የሚለውን ይዞ ይመጣል:: ምንም እንኳን እቅድህን ለሰዎች አትናገር ቢባልም፤ ከሰው ማህበራዊነት ተፈጥሮ አንጻር ተግባራዊ ለማድረግ የሚቻል አይደለም:: ስለዚህ ጉዳዩን በምን መጠን ለማን መናገር ያስፈልጋል ወደ ሚለው ይወስደናል::
እቅዶችን ለምታምናቸው፣ ስኬትህን ለሚደግፉ፣ በገንዘብ ወይም በሐሳብ ለሚያግዙህ፣ ቀና አመለካከት ላላቸው ሰዎች፣ በዘርፉ የሕይወት ልምድ ላላቸው ሰዎች መናገር ይመከራል:: እነዚህ ሰዎች ምክር ይሰጡሃል፤ አዲስ እውቀት እንድታገኝ፤ የሚተባበሩህ ሰዎች ከጎንህ እንዲሰለፉ ያግዝሃል::
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም