የግብዓት አቅርቦቱ

0
194

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በ2016/2017 የምርት ዘመን ከአምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማረስ ከ169 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት አቅዶ እየሰራ ይገኛል።

ይህን ዕቅድ ለማሳካት ደግሞ ማሳን ደጋግሞ ማረስ፣ ማዘጋጀት እና በቂ የግብዓት አቅርቦት ለአርሶ አደሩ ማቅረብ አስፈላጊ ነው። በበጀት ዓመቱ ከባለፉት ሁለት ዓመታት የተሻለ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እንዳለ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው ናቸው።

ለክልሉ  በምርት ዘመኑ ስምንት ሚሊዮን 57 ሺህ 900 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ  ለማቅረብ ታቅዶ ግዥ ተፈጽሟል። ከተገዛው ውስጥ አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደብ የደረሰ ሲሆን ከአራት ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ወይም 60 በመቶው የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዩኒየኖች ገብቷል። እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን  ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት መቻሉን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ለበኩር ጋዜጣ ተናግረዋል።

ሌላው ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ያለው ምርጥ ዘር ነው ያሉት አቶ አጀበ በምርት ዘመኑ ለመኸር ዘር የሚያገለግል 188 ሺህ ምርጥ ዘር ለማሰራጨት በዕቅድ ተይዟል።

እስካሁንም ከ76 ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ እና መጠነኛ የስንዴ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ገልፀዋል።

እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገለፃ የአፈር ማዳበሪያ በአቅርቦት እና በስርጭት ከባለፈው ዓመት የተሻለ ቢሆንም አልፎ አልፎ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት አመራሩ ከባለሙያው ጋር በቅንጅት እንዲሰራ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ እና አንዳቤት፣ በሰሜን ጎንደር ዞን በየዳ፣ ጃናሞራ እና ጠለምት እንዲሁም ሰሜን ሸዋ ዞን መሀል ሜዳ እና በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተመላክቷል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here