“ፓራለምፒክስ በሀገራችን ምንም ያልተሠራበት ነው”

0
149

ከ10 ዓመታት በላይ የፓራለምፒክን አሰልጥነዋል፤ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች ፍላጎት እና ችሎታን መሠረት አድርጎ  በማሰልጠን ለፓራለምክ ሲያበቁ ቆይተዋል:: በልዩ ፍላጎት መምህርነት ከ30 ዓመታት በላይ አስተምረዋል::

ያሰለጠኗቸው አትሌቶች በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገር በተደረጉ ውድድሮች አሸናፊ ሆነዋል፤ ሀገራቸውንም አስጠርተዋል:: ለአብነት ከአራት ዓመታት በፊት በተካሄደው የቶኪዮ ፓራለምፒክ የመጀመሪያውን ወርቅ ያመጣችው አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ተጠቃሽ ናት:: ስልጠናውንም በበጎ ፈቃድ ያለምንም ክፍያ ነው የሚሰጡት፤ ለዚህ አገልግሎታቸው በ2014 ዓ.ም በደብረ ብርሃን ከተማ የበጎ ሰው ሽልማትን አግኝተዋል፤ አሰልጣኝ ንጋቱ ሃብተማሪያም

 

ስለ ራስዎ ትንሽ ይንገሩን?

የተወለድኩት በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃ እና ወደራ ወረዳ ሰላ ድንጋይ ከተማ አካባቢ ነው:: ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በሰላ ድንጋይ ነው የተማርኩት፤ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ሳልፍ ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ አቀናሁ:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ወደ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገባሁ:: ከአንድ ዓመት ስልጠና በኋላ በመምህርነት ተቀጠርኩ:: በሂደት ወደ ፓራ ኦሎምፒክስ አሰልጣኝነት ገባሁ:: አሁንም በማስተማር ላይ ነው ያለሁት::

 

እርስዎ የሚያሰለጥኑት ፓራ አሎምፒክስ ምንድን ነው?

ፓራለምፒክስ ሲባል ብዙ ዘርፍ አለው:: ሩጫ፣ ውርወራ እና ዝላይ ስፖርቶችን ይሸፍናል:: እኔ ማሰለጥነው የፓራለምፒክስ አትሌቲክስ ነው:: 100 ሜትር እስከ ማራቶን ድረስ የሩጫ ስልጠናዎች አሉ:: እኔ የማሰለጥነው እስከ 1500 ሜትር ነው:: የእጅ፣ የእግር እና የአይን ጉዳት ያለባቸው በሦስቱም የአትሌቲክ ዘርፎች አሰለጥናለሁ::

የፓራ ኦሎምኪስ ስልጠና የጀመርኩት በ2004 ዓ.ም ነው:: ስጀምረውም 38 የአካል ጉዳተኞችን  በመሰብሰብ እና በመመልመል ነው:: የልዩ ፍላጎት መምህር መሆኔ እገዛ የሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ጋር አገናኝቶኛል:: ይህም አካል ጉዳተኞች በምን ቢታገዙ ውጤታማ ይሆናሉ የሚለውን እንዳውቅ አድርጎኛል::

የአንደኛ ደረጃ የፓራለምፒክስ የአሰልጣኞች ስልጠና በመሰልጠኔም ወደ ዘርፉ እንድገባ በር ከፍቷል:: ስጀምረውም ጥቅም አገኝበታለሁ ብየ ሳይሆን በማገልገል የሚገኘውን የአእምሮ እርካታ በማሰብ ነው:: ልጆቹ ውጤታማ ሆነው ሳያቸው ደግሞ የበለጠ ክፍያው ያ ነው:: ነገ ሟች ነኝ ዛሬ ሀገር እና ወገንን የሚጠቅም ነገር ሰርቶ ማለፍ ትልቅ ስጦታ ነው:: ቤተሰቤን ማስተዳድርበት የመምህርነቱ ሙያ አለ:: ከዛ ውጪ በነጻ ነው የማሰልጠን አገልግሎት የምሰጠው:: ፈጣሪየም ይህንን ጽናት ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ:: ቤተሰቦቼ በተለይ ባለቤቴ አታጨናንቀኝም፤ ማገልገል ትልቅ ጸጋ ነው… በማለት ትደግፈኛለች

 

ስልጠናውን በምን መንገድ ነው የሚሰጡት?

አካል ጉዳተኛን ለማሰልጠን ምቹ አካባቢ እና ሁኔታ ያስፈልጋል:: ሩቅ ቦታ ከከተማ እየወጣን ነው የምናሰለጥነው:: በፊት የቦታ ችግር እምብዛም አልነበረም:: አሁን ግን በመኖሪያ ቤት ግንባታ ምክንያት መሬቱ በመወረሩ የመለማመጃ ስፍራ ማግኘት አዳጋች ሆኗል:: ወጣ ገባ ገደላማ በቁጥቋጦ እና በአለት የተሞላ ከሆነ በቀላሉ ይወድቃሉ፤ ጉዳት ይደርስባቸዋል::

አይደለም መለማመጃ ሜዳው ይቅርና የመሮጫ ትራኮች ሳይቀር ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አይደሉም፤ ይህ እንደ ሀገር ያለ ችግር ነው:: በተለይ በከፊል እና ሙሉ ለሙሉ አይነ ስውራን ያለ ስጋት ሊሮጡበት የሚችል ትራክ የለም:: የእጅ እና እግር ጉዳት ያለባቸውም በተመሳሳይ እነሱን ታሳቢ ያደረጉ መለማመጃዎች እና መወዳደሪያዎች የሉም::

ዝም ብሎ ከመቀመጥ ያለውን ሀብት እና አንጻራዊ ምቹ ሁኔታ ይዞ መሥራት ካልተቻለ ደግሞ ትንሽም ቢሆን ውጤት ማምጣት አይቻልም:: ስልጠናው በጣም ከባድ ነው፤ በተለይ ሙሉ በሙሉ አይነ ስውር የሆኑ ስፖርተኞችን ለማሰልጠን የሚመራቸው ያስፈልጋል:: ፈቃደኛ የሆነ የሚመራቸው ሰው ማግኘት ከባድ ነው:: ለግዜው አይናማ አትሌቶች በልመና እንዲመሯቸው እያደረግን ነው:: ነገር ግን የሚመሩት አትሌቶች ራሳቸው ልምምድ ማድረግ አለባቸው:: አሊያ አቋማቸው እና ውጤታቸው ይቀንሳ፤ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እየገባን የጅምናዚየም እና ሌሎች የአካል ብቃት ልምምዶችን እናደርጋለን::

የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ድጋፍ ያደርግ ነበር:: ለምሳሌ ውድድር ሲሆን ለተወሰኑ አትሌቶች ላብ መተኪያ  ይሰጥ ነበር:: አሁን ላይ የላብ መተኪያ ቀርቶ ትጥቅ የመሳሰሉ ለአንድ ፕሮጀክት ሰልጣኝ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች እንዲሟሉ ከማደረግ አንጻር  ድጋፍ ቆሟል ማለት ይቻላል:: ከሪፖርት እና ክትትል ካልሆነ በስጠቀር ድጋፍ የለም::

ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ በተደደጋሚ አቅርበናል፤ ግን ምላሽ የለም:: እንዲሁም በፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን ሰፋ ብሎ በክለብ ደረጃ ለሀገር እና ለወገን የሚጠቅሙ ልጆች ታቅፈው እንዲሠራ ብዙ ጊዜ ጠይቀናል:: ነገር ግን የሚያግዘን ስለሌለ እኛው ባለችን አቅም ለመንቀሳቀስ ተገደናል:: ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ዋና አጋዣችን ነው:: የስልጠና ማዕከላችን እንዲሁም ድጋፍ ሰጪያችን ነው:: ሰባት ልጆችን ይዞልን ምግብ፣ መኝታ  የኪስ ገንዘብ እየሰጠ ተጠቃሚ አድርጓቸዋል፤ ለጉዳት አልባ አትሌቶች የሚያደርጉትን ሁሉ ያደርጉላቸዋል::

 

ፓራለምፒክስ በሀገራችን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ፓራለምፒክስ በሀገራችን ምንም ያልተሠራበት ነው ማለት ይቻላል:: ትዕግስት በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያውን ወርቅ አምጥታለች:: ከዘርፉ አንጻር እና ከሀገራችን ሁኔታ ሲታይ ብዙ መሠራት የሚቻልበት ቢሆንም የሚጠበቀውን ያክል አይደለም:: በሀገራችን ብዙ አካል ጉዳተኞች አሉ:: ፍላጎቱ፣ ችሎታው እና ጥረቱ ካላቸው አሰልጥኖ ብቁ በማድረግ ከወረዳ ጀምሮ ሀገር እንዲያስጠሩ ማድረግ ይቻላል:: ይህን በሰፊው ለማድረግ ግን በደንብ ወደ ውስጥ ሰርጾ የገባ ሥራ አልተሠራም:: በአመለካከት ደረጃ ቀድሞ ከነበረው የሚሻል ነገር አለ:: እንደ ኅብረተሰብ፣ እንደ ተቋም እና ሀገር ሲታይ ታች ወርዶ አካል ጉዳተኛውን አግኝቶ በማብቃት ለሀገር ጠቃሚ በማድረግ ረገድ ብዙ ሥራ ይቀራል::

 

ያመጣችሁት ውጤት ምን ይመስላል?

የትግስት ውጤት የእኔ ብቻ ጥረት አይደለም፤ የበፊት አሰልጣኞቿ የእነሱ ሁሉ ጥረት የተካተተበት ነው:: እሷም ከፍተኛ ዋጋ ከፍላ ነው እዚህ የደረሰችው:: በመሆኑም አንድ ነገር ላይ ውጤታማ ለመሆን ትልቅ ደረጃ ለመድረስ መስዋትነትን መክፈል አስፈላጊ ነው::

በሀገር ውስጥ ውድድሮች ሰሜን ሸዋ ዞን በተደጋጋሚ አንደኛ ወጥቷል:: ከፍ ሲል ደግሞ ክልሉ በፓራለምፒክስ ውጤት ሲያመጣ ትልቅ አቅም የሆኑት ከዚህ የሚወጡ ናቸው:: እስከ 18 ድረስ አትሌቶች አስመርጠን በክልል ውድድሮች ተሳታፊ ሆነናል:: ከዚህ ባሻገር በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፈዋል:: ትልቁ በሀገር ደረጃም የመጀመሪያው ውጤት በትዕግስት የመጣው የመጀመሪያው ወርቅ ነው::

 

ወደፊት ስፖርቱን ለማሳደግ ምን መሠራት አለበት?

ዋናው ሥራ የሚሠራው ታች ነው፤ ልክ ለአትሌቲክስ እና ለእግር ኳስ የሚወጣውን አይነት ጉልበት እና ገንዘብ ለፓራለምክሱም መውጣት አለበት:: የኅብረተሰቡ አመለካከት ከድሮው ተቀይሯል:: በፊት አይነ ስውር ስታስሮጠው ቢያይህ እንደ እብድ ሁሉ ሊቆጥርህ ይችላል፤ አሊያም ለምን ታሰቃየዋለህ ይልሃል:: ይህ አመለካከት አሁን ተቀየሯል:: መስተካከል ያለበት የሚሰጠው ኢንቨስትምንት እና ድጋፍ ከሌሎች ስፖርቶች እኩል  የተሻለ ትኩረት ሊሰጠው ያስፈልጋል::

 

በመጨረሻ ስለመምህርነት ይንገሩን?

መምህርነት  ፈታኝ ነው፤ ሰው የሚቀረጽበት ነው፤ ስነ ምግባር በተለይ ዋናው ነው፤ ሰውን ማነጽ ማለት የባህሪ ለውጥ እንዲያመጣ የሚያስችል ነው:: ተማሪውንም እንደ አቅሙ እና ባሕሪው መያዝን የሚጠይቅ ነው:: በእኔ ዘርፍ ደግሞ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ናቸው:: ለእነሱ ደግሞ የተለየ አቀራረብ እና ድጋፍ ያስፈልጋል:: ቀላል የሚመስሉትን ነገሮች እንኳ ለማስረዳት የሚያስቸግርበት ሁኔታ ሊገጥም ይችላል:: ለምሳሌ ሲወለድ ጀምሮ አይነ ስውር የሆነ ሰውን ቀለም ሌሎች የሚታዩ ነገሮችን ለማስተማር ወይም ለማስረዳት ከባድ ነው:: ጥረት ያስፈልጋል:: ብዙዎቹ ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰው ስትመለከት ግን ድካምህ ጠፍቶ እርካታ ይሰጥሃል::

 

እንግዳችን ስለነበሩ እናመሰግናለን!

አመሰግናለሁ!

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here