በጋዛ ቋሚ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ተወሰነ

0
165

በእስራኤል እና ሐማስን እና የፍልስጤማውያን እስላማዊ ጂሃድ በተባሉ የፍልስጤም ታጣቂ  ቡድኖች መካከል መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም ላይ የተጀመረው ጦርነት፣ የሐማስን ከጋዛ ሰርጥ ተነስቶ  በእስራኤል ምድር ላይ በየብስ፣ በባህር እና በአየር ያደረገውን የተቀናጀ ጥቃት ተከትሎ እንደነበር ይታወሳል። ጥቃቱ ከ1200 በላይ የሆኑ በዋናነት የእስራኤል ዜጎች ላይ የሞት ጉዳት ያስከተለ ሲሆን ይህም እስራኤል ካወጀችበት ወዲህ ከተከሰቱት ከፍተኛ ጉዳት የተመዘገበበት ተብሎለታል።

ከ240 በላይ የእስራኤል ዜጎች በሃማስ የታገቱበት ጥቃት እስራኤልን በማግስቱ አስቸኳይ የጦርነት አዋጅ እንድታውጅ ግድ ያለ ነበር። በመሆኑም የእስራኤል መከላከያ ኃይል ከፍተኛ የሆነ የአየር ድብደባ በጋዛ ሰርጥ ላይ ጀመረ ። ከሳምንታት በኋላም የምድር እና የብረት ለበስ ሰፊ ዘመቻ ተከትሏል። እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረችበት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ከ30ሺ በላይ ጋዛውያን ሕይወት እንዳለፈ እና ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑ ሕንፃዎች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል።

እስራኤል ራስን ከጥቃት የመከላከል እና ሕልውና የማስጠበቅ ዘመቻ በምትለው ወታደራዊ ዘመቻ በንፁሃን ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ በማስከተሉ ዓለምአቀፍ ውግዘት ከገጠመው ዋል አደር ብሏል። በተለይ ሕፃናት እና ሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው አሰቃቂ ጉዳት ብዙዎችን አስቆጥቷል።

ስምንት ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት በርካታ ንፁሃን ባለቁበት፣ አያሌ ህንፃዎች እና መሰረተ ተቋማት በወደሙበት እና በብዙ ሺዎች ላይ የረሀብ አደጋ በተጋረጠበት እስራአል ሀይ ባይ ያጣች እስኪመስል ሀማስን ሙሉ ለሙሉ እስኪሸነፍ ጦርነቱን እንደሚቀጥል እየገለፀች ትገኛለች።

ለገላጋይ ያስቸገረው የእስራኤል እና ሀማስ ግጭት የእስራኤልን ጠላቶች እያበዛ ኢራንን ለጥቃት እስከመጋበዝ፣ በሊባኖስ የሂዝቦላ ታጣቂዎች ቡድንን ጦርነት እንዲያውጅ ያስገደደ አደገኛ ቀጠናዊ ውጥረት እያስከተለ መምጣቱ በርካቶችን አሳስቧል።

ይህ በእንዲህ ባለበት ነው ታዲያ የእስራኤል ቀኝ እጅ በምትባለው አሜሪካ አማካይነት በጋዛ ቋሚ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ያለመ ምክረ ሀሳብ ለፀጥታው ምክርቤት የቀረበው። የስምንት ወራቱን ጦርነት መፍትሄ እንደሚያበጅለት ተስፋ በተጣለበት የአሜሪካ የተኩስ አቁም እቅድ ላይ ከሩሲያ ብቸኛ ድምፀ ተአቅቦ ውጭ በአስራ አራቱ የምክር ቤቱ አባላት የድጋፍ ድምፅ አግኝቶ ፀድቋል።

እንደ አጃንስ ፕሬስ ዘገባ እቅዱን እስራኤል መቀበሏን የአሜሪካ መንግሥት ይፋ ማድረጉን እና ሀማስም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርባለች። ሆኖም እስራኤል ተቀብላለች ቢባልም ፕሬዚደንት ኔታንያሁ የማወላወል ስሜት በማሳየት እስራኤል አሁንም  ሀማስን  ለማስወገድ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት ገልፀዋል።

ሀማስ የመፍትሄ ሀሳቡን እንደተቀበለ እና ለተግባራዊነቱ በአደራዳሪዎች በኩል ከእስራኤል ጋር ቀጥተኛ ድርድር ለማድረግ ዝግጁነቱን መግለፁን አጃንስ ፍራንስ ዘግቧል።

ዘ ኒውዮርክ ታይም እንደዘገበው ደግሞ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ሀማስ በተኩስ አቁም እቅዱ ምላሹ ላይ አንዳንድ ተፈፃሚነት የማይኖራቸውን ለውጦች አድርጓል። ነገር ግን አሜሪካ በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ድርድር እንዲጀመር ከፍተኛ ጥረቷን እንደምትቀጥል ገልፀዋል። በቀጣይ ቀናት ከአጋሮቻቸው ካታር፣ እና ከግብፅ ጋር በመሆን በአስቸካይ መሰረታዊ መርህ ድርድሩን ለመቋጨት ግፊት ማድረጋቸውን ለመቀጠል መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

“ሀማስ ጠረጴዛ ላይ ባለው  ምክረ ሀሳብ ላይ በርካታ ለውጦችን አቅርቧል” ያሉት ብሊንከን ከአንድ ቀን በኋላ የፀጥታው ምክር ቤት ባፀደቀው ውጊያውን በሚያስቆመው እና ታጋቾችን እና እስረኞችን  በሚያስለቅቀው የተኩስ አቁም እቅድ ላይ ሀማስ ምላሽ ሰጥቷል።  “አንዳንዶቹ የሃማስ ጥያቄዎች የሚተገበሩ ከሆኑ፣ የተወሰኑት ደግሞ የማይፈፀሙ ናቸው።”

የተኩስ አቁም ምክረ ሀሳቡ በፍጥነት ውጊያው እንዲቋረጥ የሚያደርግ እና እስራኤላውያን ታጋቾችን እና ፍልስጤማውያን እስረኞችን ከተፈቱ በኋላ፣ ለረጅም ጊዜ ወይም ቋሚ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና እስራኤል ከጋዛ ለቃ እንድትወጣ ማድረግ የሚያስችል ንግግር ያስጀምራል። ካታር እና ግብፅ እንደ አሸማጋይ ሆነው እንደሚሰሩ የዘ ኒውዮርክ ታይም ዘገባ ያሳያል።

በሌላ ዘገባ እስራኤል በፀጥታው ምክር ቤት የመፍትሄ ሀሳብ ዓለማቀፍ ግፊቱ ባየለበት የተኩስ አቁም እቅዱን የመቀበል አዝማሚያ አሳይታለች እየተባለ ባለበት የኔታንያሁ ዋነኛ ተቀናቃኝ የሆኑት የጦርነት ካቢኔ ሚንስትሩ ቤኒ ጋንፅ ከስልጣናቸው መልቀቃቸውን ይፋ ማድረጋቸው ኔታኒያሁን አጣብቂኝ ውስጥ ማስገባቱን አጃንስ ፕሬስ ዘግቧል።

በዘገባው እንደተመለከተው የጦርነት ካቢኔ ሚንስትሩ እንዳታገኝ የተሟላ ድል እስራኤል እንቅፋት እንቅፋት ሆነዋል በሚል ስልጣናቸውን እንደሚለቁ እና መንግሥት እንዲበተን እንደሚያደርጉ ሲያስፈራሩ የቆዩበትን ዛቻ በቅርቡ እውን አድርገዋል። ይህ ደግሞ ኔታንያሁን አቋማቸውን በማስቀየር በጦርነቱ ለመግፋት እንዲወስኑ ሊያስገድዳቸው እንደሚችል የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።

ቤኒ ጋንፅ /Gantz/ የኔታኒያሁ ተቀናቃኝ ሲሆኑ ፍልስጥኤማውያንን ከጋዛ ሙሉ በሙሉ በማስወጣት እና እስራኤል በጋዛ የሰፈራ መርሀ ግብሯን እንድታከናውን ጦርነቱን እንዲቀጥል የሚፈልጉ ሲሆን የተኩስ አቁሙን እቅድ አይቀበሉም። ስለሆነም ኔታኒያሁ በአሜሪካ ግፊት ያሳዩትን የመስማማት አዝማሚያ በመቃወም ስልጣናቸውን መልቀቃቸው ተዘግቧል። ኔታኒያሁም የጦር ካቢኔት ሚንስትር ስልጣን እንዳይለቁ፣ ይልቁንም አንድነታቸውን አስጠብቀው ለእስራኤል ብሔራዊ ጥቅም በጋራ እንዲሰሩ ሲያግባቧቸው እንደቆዩ ታውቋል።

ሌላው አነጋጋሪ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ይዞት የወጣው ሪፖርት ነው። እስራኤል እና ሀማስ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሳይፈፅሙ እንዳልቀረ ያወጣውን ሪፖርት የዓለማቀፍ ሚዲያዎች እየተቀባበሉት ይገኛሉ።

እንዲህ ባለው አጣብቂኝ ውስጥ በጋዛ እየደረሰ ያለውን ኢሰብአዊ ውድመት እና ለስምንት ወራት የዘለቀውን ጦርነት በቋሚነት ሊያስቆም እንደሚችል ተስፋ የተደረገበት የመፍትሄ ሀሳብ ፈተናዎቹን ሁሉ አልፎ ለዚህ አኬል ዳማ ምድር እፎይታ ያጎናፅፍ ይሆን? አብረን የምናየው ይሆናል።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here