- በአማራ ክልል ባለው ግጭት ከ2 ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል
- በሰሜን ጎጃም ዞን ትምህርት ያልተቋረጠው ባህርዳር ከተማ በሚገኘው ፊታውራሪ ሐብተማርያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ብቻ ነው
- 2 ሺህ 935 የትምህርት ተቋማት በሰሜኑ ጦርነት የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸዋል
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ግን መፍትሄ የራቃቸው ግጭቶች እና ጦርነቶች፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ እየተከሰተ ያለው ድርቅ ዓለም ወደ ዕድገት የምታደርገውን ጉዞ እየገቱ የመጡ ይመስላሉ:: የዕድገት መሰላል፣ የሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጫ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ማስተሳሰሪያ ገመድ እንደሆነ የሚነገርለት ትምህርት በእነዚህ ጉዳዮች ክፉኛ ስለመጎዳቱ ቁጥራዊ አኃዞች ያሳያሉ::
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የዓለም ሀገራት ላይ እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶች እና ጦርነቶች ብቻ 468 ሚሊዮን ሕጻናት ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን መቀመጫውን ኦስሎ ያደረገው የሰላም ጥናት ተቋም በቅርቡ ሪፖርት አድርጓል:: እንደ ጥናቱ ከስድስት ሕጻናት አንዱ በግጭት ቀጠና ውስጥ ይኖራል:: መፍትሄ የተነፈጋቸው በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች ሕጻናት ደኅንነታቸው በተረጋገጠባቸው ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እንዳያስቀጥሉ ስጋትን በመደቀን ትምህርታቸውን የሚያ ቋርጡ ህፃናት እንዲጨምር ስለማድረጉም እየተገለጸ ነው:: ሕጻናት በግጭት ወቅት ማምለጥ ስለማይችሉ ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለአስገድዶ መደፈር እና ሌሎች አደጋዎች መጋለጣቸው የተለያዩ ሀገራት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት ጥረት አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ እያደረገው መሆኑን ጥናቱ ጨምሮ ገልጿል::
ዴሞክራሲን በመለማመድ እና መሪዎቻቸው ስልጣንን እኔ ከሞትኩ… በማለት ሙጥኝ ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ችግሩ እጅጉን የሰፋ ነው:: የአፍሪካ ሕብረት 37ኛውን የሕብረቱን ጉባኤ ባካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው ከሆነ በአፍሪካ ፈጣን ምላሽ ባልተሰጣቸው ግጭቶች እና ጦርነቶች እንዲሁም በሌሎች ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት የመማር ዕድላቸውን ተነፍገዋል::
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከስድስት ወራት በፊት ይፋ ባደረገው ሪፖርት በኢትዮጵያ ባጋጠመው ግጭት እና የተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥ ሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሕጻናት ከትምህርት ውጪ ናቸው::
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የትምህርት ሚኒስቴርን የ2016 በጀት ዓመት እና የአንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን በወርሀ ጥቅምት በገመገመበት ወቅት እንዳስታወቁት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የቀጠሉ ግጭቶች በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት ከነበረባቸው ተማሪዎች መካከል 26 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆኑት በጦርነት፣ በድርቅ፣ በጎርፍ እና መሰል አደጋዎች መምጣት አልቻሉም ብለው ነበር::
ትኩረቱን ትምህርት ላይ አድርጎ የሚሠራው ግሎባል ሲቲዝን በበኩሉ በኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የሰሜኑ ጦርነት በትምህርት መስኩ ላይ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ መሆኑን ቁጥራዊ አኃዞችን እየመዘዘ ያስረዳል:: እስከ 2013 ዓ.ም መጨረሻ ከሰባት ሺህ በላይ ትምህርት ተቋማት ለጉዳት ተዳርገዋል:: ጉዳት ያልደረሰባቸው ትምህርት ተቋማትም ለወታደራዊ ካምፕነት ውለዋል፤ ይህም በርካታ ተማሪዎች እና መምህራን ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል::
በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋም እና ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ሚያዚያ 04 ቀን 2016 ዓ.ም እንዳስታወቀው ከሆነ ደግሞ ጦርነቱ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እስከ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ጉዳትን አስከትሏል:: በዚህም ሁለት ሺህ 935 የትምህርት ተቋማት ከቀላል እስከ ከባድ ውድመት ደርሶባቸዋል::
የሰላምና ደኅንነት ችግሮችን ጨምሮ ሌሎች ችግሮች የትምህርት ጥራት ፈተና ሆኖም ብቅ ብሏል:: ዓለም አቀፉ የሕጻናት መርጃ ድርጅት (unicef) ኢትዮጵያ የዕውቀት መሠረት በሚያዝባቸው የትምህርት ቤት ደረጃዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች ብትመዘግብም ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ግን እጅግ አናሳ መሆኑን አስታውቋል:: ይህም በሀገሪቱ ያጋጠሙ የጸጥታ እና ሌሎች የትምህርት ችግሮችን በዘላቂነት ከመፍታት ጎን ለጎን የትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ የሚያረጋግጥ ነው:: ጉዳዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ድርጅቱ ያስታወቀው፣ 90 በመቶ ዕድሜያቸው 10 ዓመት የሆናቸው ተማሪዎች ማንበብ እና መረዳት አለመቻላቸውን በመጠቆም ነው::
በተደጋጋሚ እያጋጠመ ያለው የሰላም መናጋት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና ማሳደሩም አይዘነጋም:: በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት አመራር መምህር እና ባለሙያው ሸጋው ሞላ ግጭቶች እና ጦርነቶች የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን በእጅጉ እየገደቡ ስለመሆናቸው መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም ለበኲር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በስልክ አስረድተው ነበር:: በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሀገሪቱ ካስፈተነቻቸው ተማሪዎች ውስጥ 96 ነጥብ 7 በመቶ ወደ ዩኒቨርሲቲ አለመግባታቸውን እና 1ሺህ 600 ትምህርት ቤቶችም ያስፈተኗቸውን ሁሉንም አለማሳለፋቸውን በመጠቆም ነው፡ እንደ ሀገር በተሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከተፈተኑት ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ ከግማሽ በላይ ማሳለፍ የተቻለው በ2012/13 ዓ.ም ሲሆን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያስገባውን ነጥብ ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥርም 55 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ እንደነበር ይታወሳል::
የሰሜኑ ጦርነት ምንም እንኳ በሰላም ስምምነት ተቋጭቶ ለተወሰነ ጊዜ እፎይ የሚያስብል ሰላም የተገኘ ቢሆንም የጸጥታ ስጋቱ ግን አሁንም አማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀጥሏል:: ይህም የጸጥታ ችግር ባለፉት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ ላይ የተስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ከማደናቀፍ ባለፈ አሁንም በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ እና የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ቁጥር በእጅጉ እንዲቀንስ አድርጓል:: ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ከሰሞኑ እንዳስታወቀው በ2016 ዓ.ም ከ700 ሺህ በላይ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ይወስዳሉ:: ይህ ቁጥራዊ አኃዝ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ145 ሺህ በላይ ዝቅ ያለ ነው::
የአማራ ክልልም በትምህርት ዓመቱ 105 ሺህ 282 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ያስፈትናል:: ዘንድሮ የሚሰጠው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በሁለት ዙር እንደሚሰጥ ከትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያሳያል:: በተፈታኝ ተማሪዎች ልክ የማለፍ ምጣኔውን ለመጨመርም ከፍተኛ የሆነ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራም ይገኛል ተብሏል::
በአማራ ክልል አሥር ወራትን ባስቆጠረው ግጭት አሁንም ድረስ ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንደሆኑ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል:: የሰላም ችግሩ ምን ያህል መማር ማስተማሩን እንደፈተነው በአብነት እንመልከተው:: የምስራቅ ጎጃም ዞን 996 አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ:: በእነዚህ ትምህርት ተቋማት በዓመቱ መዝግቦ ለማስተማር ታቅዶ የነበረው የተማሪ ቁጥር 539 ሺህ 996 ነው::
ይሁን እንጂ ከ2015 ዓ.ም ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር አሁንም ድረስ መፍትሄ ባለማግኘቱ ወደ መማር ማስተማር ሥራ የገቡት 32 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው። ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት ከ13 ሺህ የበለጡ እንዳልሆኑ የምስራቅ ጎጃም ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያሰፈረው መረጃ ያሳያል::
ትምህርት መምሪያው የ2016 ዓ.ም የተማሪ ምዝገባ ከመጀመሩ ቀድሞ በ791 ትህርት ቤቶች 41 ሺህ 944 ተማሪዎችን በስድስተኛ ክፍል ተቀብሎ በማስተማር ለክልላዊ ፈተና ለማብቃት ማቀዱም ይታወሳል:: እውነታው ግን በ12 ትምህርት ቤቶች ያውም በሁለት ዙር 506 ተማሪዎች ብቻ ይፈተናሉ::
593 ትምህርት ቤቶች ደግሞ 38 ሺህ 203 የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች እንደሚያስፈትኑ በዓመቱ መጀመሪያ ታቅዶ ነበር:: አሁናዊ እውነታው ግን አሥር ትምህርት ቤቶች 431 ተማሪዎችን ብቻ ያስፈትናሉ::
ባለፉት ሁለት ዓመታት በጣም ዝቅተኛ ውጤት የተስተዋለበት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የክልሉ ዋና አጀንዳ ሆኖ ለማሻሻል በልዩ ትኩረት ሲሠራበት ቆይቷል:: ይሁን እንጂ የጸጥታ ችግሩ የተፈታኝ ተማሪዎችን ቁጥር እና የማለፍ ምጣኔውን ለማሻሻል ሲደረግ የነበረው ጥረት ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል:: ለዚህ አብነቶችን እንመልከት:: የምስራቅ ጎጃም ዞን በ2016 ዓ.ም በ65 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 19 ሺህ 657 ተማሪዎችን ለማስፈተን ዕቅድ ነበረው:: በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ የተረጋገጠው አምስት ትምህርት ቤቶች፣ 577 ተማሪዎች ብቻ ሆነው በሁለት ዙር ፈተና ተብሏል::
የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ እና ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ ከማድረግ በተጨማሪ 407 ትምህርት ቤቶች እንዲወድሙ በማድረግ ከ290 ሚሊዮን በላይ ሀብት እና ንብረት መውደሙ ተመላክቷል::
የጸጥታ ችግሩ በሰሜን ጎጃም ዞን የሚገኙ 503 ትምህርት ቤቶች ከትምህርት ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል:: ይህም 400 ሺህ 987 ተማሪዎች እና ከአሥር ሺህ በላይ መምህራን እና ሠራተኞች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ ማድረጉን የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል:: በዓመቱ በ115 ትምህርት ቤቶች 38 ሺህ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ገብተው የነበረ ቢሆንም በተደጋጋሚ በተፈጠሩ ግጭቶች ባሕር ዳር ከተማ ከሚገኘው ፊታውራሪ ሐብተ ማርያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውጪ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ሥራ ማቆማቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ነጋልኝ ተገኘ ተናግረዋል::
የተፈጠረው የሰላም ችግር በባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር በሚገኙ የትምህርት ተቋማት እና ተማሪዎች ላይ ተጽእኖ ማሳደሩም ተመላክቷል:: በከተማ አሥተዳደሩ ከሚገኙ ከመቶ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሁለት የሁለተኛ ደረጃ እና 22 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ውጪ መሆናቸውን ያስታወቁት የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ኀይለማርያም እሸቴ ናቸው::
በአጠቃላይ የሰላም መታጣቱ በትምህርት ተቋማት ላይ እያደረሰ ያለው አጠቃላይ ጉዳት እና ውድመት ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል:: የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በፈረንጆቹ ሰኔ 29 ቀን 2023 ከትምህርት ሚኒስቴር አገኘሁት ብሎ እንደዘገበው በኢትዮጵያ ካሉት 50 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ71 በመቶ በላይ የሁለተኛ ደረጃ እና ከ86 ከመቶ በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹነት የሌላቸው እና በጥራታቸውም ከደረጃ በታች መሆናቸው ነው:: በመሆኑም የትምህርት ተደራሽነትን ከጥራት ጋር ማረጋገጥ፣ ተደጋጋሚ ግጭቶችን በሰላማዊ ስምምነት መቋጨት ይገባል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም