ለውይይት ጊዜው ረፍዶ አያውቅም

0
144

የአማራ ክልል በግጭት ውስጥ ከገባ ዐሥራ አንድ ወራትን ተሻግሯል። ግጭቱን ተከትሎ ታዲያ ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መተዳደር ከጀመረ ከዐሥር ወራት በላይ ተቆጥረዋል። ግጭቱም ዘርፈ ብዙ ችግሮችን አስከትሏል። የሕዝቡን እንቅስቃሴ ገድቧል። በዚህም ከባድ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳትን አስከትሏል።

ግጭቱ ክፉኛ ከጎዳቸው መካከል ደግሞ ትምህርት ተጠቃሽ ነው። የምዕራብ ጎጃም ዞን ከሰሞኑ እንዳስታወቀው በትምህርት ዘመኑ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ይማራሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ይሁን እንጂ በትምህርት ገበታ የተገኙት እና ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት ሠላሳ ሺህ ያህል ናቸው።

ከዚህ ጋር በተገናኘ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማሕበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪው ጌትነት ታደለ (ፕ/ር) ለአሚኮ ሙያዊ ሐሳብ ሰጥተዋል። “የሀገሪቱን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚቻለው  የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት ሲቻል ነው” ብለዋል። ከዚህ እውነታ ባሻገር በተለይ በአማራ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ አለመምጣታቸው መነገሩ ታዲያ እንደ ክልልም እንደ ሀገርም ጉዳቱ የከፋ መሆኑን ነው የሚያስረዳው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግጭቱ በውይይት እንዲቋጭ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆዩም የተፈለገውን ውጤት ማስገኘት አልቻለም። የተጨበጠ ውጤት ባያስገኝም መንግሥት ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እያለ ከሚጠራው ኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ተከታታይ ውይይት ማድረጉ ይታወሳል። መሰል ፖለቲካዊ ውይይቶች ማድረግ በአማራ ክልል ለተከሰተው ግጭት ቀዳሚ የመፍትሔ አማራጭ ሊሆን እንደሚገባ ሀገራት፣ ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ሌሎችም በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ ሁሉ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ግጭቱን ለማስቆም በተለያዩ ጊዜያት ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል። ከሰሞኑ ባደረጉት የሰላም ጥሪም “ሁላችንም ለሰላም እጃችንን እንድንዘረጋ ጥሪየን አቀርባለሁ። መንግሥት ምን ጊዜም ቢሆን ሰላምን አጥብቆ ይሻል፣ ለዚህም ሲባል በግጭት ውስጥ ያሉትን አካላት ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ይቀበላል” ብለዋል።

በክልሉ ለተከሰተው ግጭት በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። በዋናነት ደግሞ የተጠራቀሙ የሕዝብ ብሶቶች፣ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘት እንደሆነ በ2015 ዓ.ም መጨረሻ በነበረው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ተሳታፊ የምክር ቤት አባላት መናገራቸው ይታወሳል። በመሆኑም ተግባራዊ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

በተመሳሳይ ባለፉት በርካታ ዐሥርት ዓመታት በተዘሩት የተዛቡ ትርክቶች ምክንያት አማራው በሌሎች ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታይ አድርጎታል። ችግሩን ለማረም ታዲያ ሕገ መንግሥቱን ከማሻሻል ጀምሮ በርካታ የእርምት ርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በቅርቡ ሐሳብ የሰጡት ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ “የተዛቡ ትርክቶችን ፈጥኖ ማረም፣ አዳዲስ የተዛቡ ትርክቶች እንዳይፈጠሩም መጠንቀቅ ያስፈልጋል”ብለዋል።

በግጭት ውስጥ የነበሩ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ውይይት፣ ቁርጠኛ ፖለቲካዊ ውሳኔ፣ በይቅርታ ወንድማማችነትን እና ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር ዋናዋናዎቹ  ሀገራቱ ከችግራቸው የተሻገሩባቸው ስልቶች ናቸው። ለአብነትም ደቡብ አፍሪካ ሩዋንዳ፣ ሴራሊዮን፣ አሜሪካ፣ … ተጠቃሾች ናቸው። መሰል ተሞክሮዎችን ተግባራዊ በማድረግ እንደ ሀገር ከገባንበት የአንድነት እጦት ቅርቃር ሊያስወጣን  እና እንደ ክልል ደግሞ የተከሰተውን ግጭት ለማስቀረት እንደሚችል ነው የሚነገረው።

ከሰሞኑ ውይይት ያደረጉት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎችም ያስተጋቡት ይህን ሐሳብ ነው። “ወንድም ከወንድሙ ጋር መገዳደል ይበቃናል፣ ልማት ለማምጣት መገዳደልን ማቆም፣ ፍቅርን ማጎልበት አለብን” ብለዋል።

በተመሳሳይ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ “የአማራን ሕዝብ መብት እና ጥቅም ማስከበርም የጋራ አጀንዳችን ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here