የኮንጐ ተፋሰስ ደን

0
128

የኮንጐ ደን እና ተፋሰሱ “የአፍሪካ ሳምባ፤ የዓለም የልብ ትርታ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል:: በማእከላዊ አፍሪካ የሚገኘው የኮንጐ ደን ከአማዞን ቀጥሎ በዓለማችን በስፋቱ ሁለተኛው  የሞቃታማው ቀጣና ደን ነው::

የኮንጐ ተፋሰስ ደን በዋናነት ስድስት አገራትን (ካሜሩን፣ ማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐ፣ የኮንጐ ሪፐብሊክ፣ ኢኪቶሪያል ጊኒ እና ጋቦን) አካሎ ይዟል:: አጠቃላይ ስፋቱም አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዬን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ተለክቷል:: ይህም ከአማዞን ደን ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል::

የኮንጐ ተፋሰስ ደን ለቀጣናው ብዝሃ ህይወት አስፈላጊ የሆኑ በርካታ ወንዞች አሉት:: ከእነዚህ መካከል በአፍሪካ ከዓባይ ቀጥሎ በትልቅነቱ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የኮንጐ ወንዝ ዋነኛው ነው::

በኮንጐ ተፋሰስ ከኮንጐ ወንዝ በተጨማሪ በማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐ የሚፈሰው ኡባንጊ ወንዝ በመጠኑ ቀዳሚ ነው:: በተጨማሪም በካሜሩን፣ በማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና በኮንጐ ሪፐብሊክ አቆራርጦ የሚፈሰው ከሳንጋ ወንዝ ባሻገር ለቀጣናው እፅዋት እና እንስሳት ዝርያዎች የተመረጠ ያደረጉት በርካታ ወንዞች እና ገባሮች መኖራቸውም ተረጋግጧል::

የኮንጐ ደን በድንቅ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ፣ በጥቅጥቅ ደኑ፣ በሰፋፊ የሳር ምድሮቹ እና በፏፏቴዎች መገኛነቱ ተጠቃሽ ነው:: በደኑ እስከ 7ዐ ሜትር ሽቅብ የተመዘዙ ዛፎች ችምችም ብለው ወይም በጥግግት ተጠቅጥቀው ይገኙበታል::

የደኑ የመጨረሻ ቅርንጫፍ መገኛ ወይም የላይኛው ገጽ የበርካታ አእዋፍ እና ዝንጆሮዎች “መናኸሪያ” ነው::

የኮንጐ ደን በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐ  እና የጋቦኑ ሉፋላካሪ ፏፏቴ አስደማሚ የቀጣናው  ጌጦች ናቸው:: ፏፏቴዎቹ ለውኃ ውስጥ እንስሳት መኖሪያ መሰረት መሆናቸውንም ልብ ይሏል::

የኮንጐ ተፋሰስ አስር ሺህ የዕፅዋት ዝርያዎች ይገኙበታል:: ከነዚሁ መካከል በየትኛውም አገር የማይገኙቱ በርካታ መሆናቸውን ድረ ገፆች አስነብበዋል::

እንስሳትን በተመለከተም አራት መቶ የአጥቢ ዝርያዎች፣ አንድ ሺህ የአእዋፍ ዝርያዎች እንዲሁም ሦስት መቶ ተሳቢ እና በውኃ ውስጥ የሚኖሩ  እንስሳት መገኘታቸውን ነው የድረ ገጾቹ  ጽሁፎች ያስነበቡት::

ህገ ወጥ የደን ጭፍጨፋ፣ ለማእድን ፍለጋ የሚደረግ ምንጣሮ እና ቁፋሮ በደኑ ላይ ያንዣበቡ ስጋቶች ሆነው ተመዝግበዋል:: ለዘገባችን ወርልድ ሬይን ፎረስት፣ ዘቢሮ ኢንቨስትጌት ድረ ገፆችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here