ጥቅምት 1955 ዓ.ም ምድራችን አንድ አስደንጋጭ ክስተት አስተናግዳለች። አሜሪካና የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት በኒኩሊየር ገደል አፋፍ ላይ ቆመው የተፋጠጡበት፣ መላው ዓለም በጭንቀት የታመሰባቸው የጨላለሙ ሁለት ሳምንታት፣ ለአያሌ ህይወት በድንገት የመጥፋት ከፍተኛ ስጋት የደቀኑ የዓመታት ያህል የረዘሙ አስራ ሦሥት ቀናት የተመዘገቡበት የታሪክ አጋጣሚ ነው። የተፈራው ጦርነት ቢከሰት ኖሮ ሁለቱም የኒዩክሌር ሚሳኤሎቻቸውን ምላጭ ቢስቡት ኖሮ በደቂቃዎች ውስጥ መቶ ሚሊዮን የሚገመቱ አሜሪካውያንን፣ ከመቶ ሚሊዮኖች በላይ ሩሲያውያንን እንዲሁም የብዙ ሚሊዮን አውሮፓውያንን ህይወት ሊቀጥፍ የሚችል አደጋ በደጅ ቆሞ ነበር። የሚከተለው ጥፋት በታሪክ ውስጥ የተመዘገቡበትን ሁሉ ያስንቅ ነበር። ብቻ የሰው ልጅ አይቶት የማያውቀው ስቆቃ ሊደርስ በቋፍ ነበር፤ የኩባው ሚሳየል ፍጥጫ። የቀዝቃዛው ጦርነት ጫፍ የደረሰ ውጥረት።
ባልስቲክ ሚሳየሎች በሶቭየት መርከቦች ወለል ስር ተደብቀው በሚስጢር ወደ ኩባ ተጓጉዙዋል:: ተጨማሪ መካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ባልስቲክ ሚሣየሎች፣ ሚሳየል ትሬይለርስ እንዲሁም የኑክሌር አረሮች ማከማቻ ባንከሮች ኩባ ደርሰው ወደ መገጣጠሚያ ስፍራቸው ተንቀሣቅሰዋል:: ይህ ሁሉ ሲሆን አሜሪካ ሳታውቅ፣ ኩባ በመስከረም መጨረሻ ላይ ለመካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ባልስቲክ ሚሣየሎች የሚሆኑ የኑክሌር አረሮችን ተረክባለች:: ከዚህም ጋር አያሌ ለኮስታል ዲፌንስ ክሩዝ ሚሣየሎች የሚሆኑ የኑክሊር አረሮችን ለመካከለኛ ጀት ቦምብ ጣይ ጀቶች የሚሆኑ 16 ኑክሊር ቦምቦችን ብሎም “ለአጭር ርቀት ታክቲካል ሮኬቶች የሚሆኑ 12 ኒውክሌር አረሮችን አግኝታለች::
ሚሳየሎቹ በኩባ ምድር እንዲተከሉ የመጨረሻው ውሳኔ የሚወሰነው በሶቭየት ኘሬዚደንታዊ ፅ/ቤት ከፍተኛ ካቢኔ አባላት ሲሆን የዘመቻው ዝርዝር አፈፃፀሞች ከአጠቃላዩ ውሣኔ እስከ ሚሣየሎች በኩባ ምድር ተተክለው ለተኩስ ዝግጁ እስከሚሆኑበት ድረስ ያለው ሒደት ለሁነኛ የሶቭት ድርጅቶች በኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። እያንዳንዱ ድርጅት የራሱን ምስጢር ይጠብቃል፤ አንዱ የሌላውን መረጃ ስለሚያገኝ የዘመቻውን ሙሉ እይታ ማግኘት አይቻልም::
ሚሣየሎችን እና አስፈላጊ ቁሶችን ማጓጓዝ፣ ማራገፍ እንዲሁም ወደ ተከላ ማዕከሉ የማጓጓዣ ሂደቱን በማይነቃ መልኩ የማከናወን ሥራው ስኬታማ ነበር:: ሚሣየሎቹን ለማጓጓዝ የሲቭል የመጓጓዣ እና የጭነት መርከቦች፣ የሆስፒታል እንዲሁም መሰል ወታደራዊ ያልሆኑ መርከቦች ጥቅም ላይ ውለዋል::
የመጀመሪያዎቹን የሰቭዮት ሚሣየሎች የተሸከሙ መርከቦች ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ኩባ ደርሰዋል:: ወታደሮቹ ስፖኒሽ ቋንቋ እንዲናገሩ የሠለጠኑ ነበሩ:: ኩባ እንደ ደረሱ የቀዩን ጦር የደንብ ልብስ አውልቀው የሲቪል ልብስ ወይም የኩባን መከላከያ የደንብ ልብስ እንዲለብሱ ተደርጓል:: ጭነቱን ወደብ ላይ የማራገፍ ስራው በከፍተኛ ጥበቃ ታጅቦ በአብዛኛው በጨለማ ይከናወን ነበር:: የተራገፈውን ጭነት ወደ መትከያ ስፍራው የሚያጓጉዙ ኮምቦዮች ከመንግሥት ተቃዋሚዎች ወይም ከሲ .አይ .ኤ ሠላዮች አይታ ውጭ ሆነው በአስተማማኝ እንዲያልፉ ለማድረግ የኩባ ፖሊስ የውሸት የትራፊክ አደጋ ይፈጥርና መንገዶችን ይዘጋጋ ነበር::
በተከላው ስፍራ ያሉ ሠራተኞች ከአሜሪካ የሰለላ አውሮፕላኖች እይታ ለመሠወር በኘላስቲክ ዳስ ውስጥ የሚሰሩበት ሁኔታ ተመቻችቶም ነበር:: በዚህ መልኩ በከፍተኛ ምስጢራዊ ሁኔታ እና በጥንቃቄ ለወራት ስኬታማ በሚባል ደረጃ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ተግባር መፈፀም የተቻለበት ሂደት ነበር::
ሆኖም የሚሣየል መትከያው ስፍራ ሙሉ በሙሉ ከእይታ ነፃ አልነበረም:: በኩባ እየተከናወነ ያለውን እንቅስቃሴ መጠርጠር የጀመሩት አሜካኖች ጥቅሞት 3 ቀን 1955 ዓ.ም አንድ U-2 የተሰኘ የቅኝት አውሮኘላን በኩባ ሰማይ ላይ ሚሣየሎች እየተተከሉ ወዳለበት ስፍራ በከፍታ በመብረር ፎቶ ግራፎችን እንዲያነሣ አደረጉ። ፎቶ ግራፎቹን ደጋግመሙ መረመሯቸው:: ታዲያ ፎቶ ግራፎቹ ያወጡት ጉድ አሜሪካኖችን ያስደነገጠ ነበር:: ሶቭየቶች በኩባ ጠረፍ፣ ከአሜሪካ 90 ማይል ርቀት ላይ ኑክሌር ተሸካሚ መካከኛ እና አጭር ርቀት ተወንጫፊ ሚሣየሎችን በመትከል ሥራ ላይ መጠመዳቸውን አጋለጠ::
ጥቅምት 4 ቀን 1955 ዓ.ም የመዘዘኛው U–2 አውሮኘላን ፎቶ ግራፎች ጉድ ለኘሬዚዳንት ኬኔዲ እና አማካሪዎች ይፋ ሆነ:: የኩባ ሚሣየል ቀውሱም ከዚህ ይጀምራል:: ኘሬዚዳንቱ የሰበሠቧቸው የካቢኔ አባሎቻቸው እና የሲቪል እንዲሁም ወታደራዊ ከፍተኛ አማካሪዎች የተካተቱበት ኤክስ ኮም የተባለ ኮሚቴ በዚህ መረጃ ከፍተኛ ቁጣ ተፈጠረባቸው:: በመሆኑም ይህን ሶቭየቶች በኩባ ላይ እያደረጉት ያለውን የኒኩሊየር ሚሣዬሎች ግንባታ በአሜሪካ እና አጋሮቿ ላይ የተቃጣ ጥቃት አድርገው የሚወስዱት በመሆኑም ፈጣን የአፀፋ እርምጃ ይወሰድ ዘንድ ጫና አደረጉ:: የኤክስ ኮም አባላቱ ለሰቭየቶች የማያዳግም ማስጠንቀቂያ እንደሰጥ እና ኩባን የማፈራረስ እርምጃ እንዲወሰድ በኬኔዲ ላይ ግፊት አበዙ:: ኬኔዲ ግራ ተጋብተዋል:: በታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የያዘ ውሳኔ በእርሳቸው ጫንቃ ላይ መውደቁ ተሰምቷቶዋል::
ኬኔዲ የሚመኩበት የቅርብ አማካሪያቸው እና የንግግር ጽሑፍ የሚያዘጋጅ ቁልፍ ሰው ሶረንሰን ከቀናት በፊት በጉዳዩ ላይ ሲንሸራሸሩ የነበሩ ሀሳቦችን ጨምቆ ለኬኔዲ አቀረበላቸው:: አንደኛው ሀሳብ ፖለቲካዊ ማስጠንቀቂያ መስጠት እና ሚሣየሎቹ ከስፍራው ካልተወገደ መጠነኛ የአየር ድብደባ ማድረግ እና ቀጥሎ ሚሣየሎች እንዲወገድ መጠየቅ:: በሦስተኛነት ሁሉን አቀፍ የባህር እንቅስቃሴ ማድረግ እና በኩባ ላይ ጦርነትን ማወጅን ያስከተለ ፖለቲካዊ እርምጃ ማድረግ በመጨረሻም ኩባን ከካስትሮ እጅ ለማውጣት በኩባ ላይ የተሟላ ደረጃ ወረራ መፈፀም እና የመሣሰሉት ሀሳቦች መንፀባረቃቸውን አሣወቀ:: ከእነዚህ ውስጥ ኩባን በአየር በመደብደብ ከዓለም ካርታ ማጥፋት የሚለው ሀሳብ በኮሚቴው ዘንድ ጎልቶ ወጣ:: ኬኔዳ በዚህ ሀሳብ መጀመሪያ ላይ ተስማምተው ነበር::
ኬኔዲ በተከታዮቹ ቀናት ካደረጓቸው ውይይቶች በኋላ ሀሳብ ቀየሩ፣ ከአየር ድብደባው ይልቅ “የባህር መስመሮቹን መዝጋት” የሚል እቅድን ለመተግበር ወሰኑ::
ኘሬዝዳንት ኬኔዲ ጥቅምት አምስት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው የሶቭየት ሚሣየሎች በኩባ ምድር መተከላቸውን እና አሜሪካ ይህን ተግባር እንደ ጥቃት ሰለምትቆጥረው ማንኛውንም ወታደራዊ አጻፋ እንደምትወስድ ለህዝቡ ይፋ አደረጉ:: ኩባን የመውረር ወታደራዊ ዝግጅቱ በምድር እና በአየር በተጠናከረ ሁኔታ ተጧጧፈ::
ሶቭየት ህብረት በበኩሏ የጦርነት ዝግጅቷን ቀጠለች:: የኒዩኩሊየር ጦርነት አይቀሬነቱን ከኬኔዲ ንግግር የተረዱት ክሩስቼቭ ሚሣኤሎቹ ተተክለው ዝግጁ እንዲሆኑ ባለሙያዎቻቸውን አዘዙ:: ተጨማሪ ሚሣየል የጫኑ መርከቦች ወደ ኩባ ተሰማሩ:: በሁሉም ወገን ለጦርነት የነበረው ፍላጎት እያየለ ሲሄድ ተው የሚል እንኳ አልነበረም::
አሜሪካኖች ጠላታቸውን አሣንሰው በማየት ባላቸው የጦር መሣሪያ ብልጫ ነገሩን በኃይል እንደሚቋጩት በማሠብ የጦርነት ግፊታቸው ከፍተኛ ነበር:: ነገር ግን ኬኔዲ ወታደራዊ አማካሪዎቻቸውን እና ዲኘሎማቾቻቸውን የኒዩኩሊየር ጦርነት እንዲቀሰቀሥ ከሚያደርግ እንቅስቃሴ መታቀብ እና ነገሩን በስክነት ማየት እንደሚገባ ይመክሯቸው ነበር::
ምክንያቱ ደግሞ ሶቭየቶች በምንም አይነት አፁፋ ምላሽ ለመስጠት አይን የማያሹ መሆኑ ወደ መጨረሻ እየጠራ መምጣቱ ነበር:: ኩባ ላይ የተጠመዱ የኒኩሊየር ሚሳየሎች ትላልቅ የአሜሪካ ከተሞችን ማውደም እንደሚችሉ እና የበርካታ ሚሊዮን ዜጎችን ህይወት በደቂቃዎች ውስጥ እንደሚቀጥፉ ባለሙያዎች ግልጽ እያደረጉላቸው መጡ:: በተለይ ደግሞ ኩባ ውስጥ በምስጢር ተጓጓዘው የደረሱ ለውጊያ ዝግጁ የሆኑ ከ 40 ሺህ በላይ የቀዩ ጦር ወታሮች ኩባ ውስጥ መኖራቸውን እና እነዚህ ወታሮች ደግሞ ሚሣየሎችን የመተኮስ በቂ ስልጠና ያገኙ መሆናቸው ነገሩን ቆም ብሎ ከማሠብ የተሻለ ሌላ አማራጭ አለመኖሩን ግልፅ እያደረገው መጥቷል::
በዚህ መካከል ጥቅምት 11 ቀን 1955 ኬኔዲ ተጨማሪ ሚሣኤሎች ወደ ኩባ እንዳይገቡ ለመከላከል የባህር ላይ እግድ አዘዙ:: ከኩባ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የአሜሪካ መርከቦች በሙሉ ተደርድው መንገድ ዘጉ:: መርከቦች ሁሉ ለዚህ ጥቅም ዋሉ:: አልፎም የአርጀንቲና እና ሌሎች አገራት መርከቦችም እንዲሳተፉ ተደረገ:: ይህ ጦርነት እንደማወጅ ማለት ነበር:: የታጠቁ ሀይሎችም ወታደራዊ ግዳጅ ለመፈፀም ተዘጋጅተዋል:: እንዲሁም ወረራ ለማድረግ በተጠንቀቅ የቆመ ከ40 ሺህ የሚበልጥ ወታደር እና 579 ከምድር እንዲሁም ከመርከቦች ላይ የሚነሱ የውጊያ አውሮፕላኖች በኩባ አቅራቢያ ለመነሳት እያሟሟቁ ነበር። ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳየሎችም ተቀባብለው ትእዛዝ ብቻ ይጠብቁ ነበር።
ከፍተኛ ፍጥጫ ተፈጠረ:: ክሩስቼቭ ይሄን ሲሰሙ ጉዳዩ በጣም አሳሰባቸው:: ለማንኛውም ሰራዊታቸው ጥቃት ከተፈፀመበት ሚሳይሎችን እንዲጠቀም ትእዛዝ አሳልፈዋል። ለዚህም ሚሳየሎቹ ዝግጁ እንዲሆኑ ታዝዟል።
በኩባ ያሉት ሚሳየሎቻቸው እንደ ካስትሮ መንግሥት ሁሉ፣ ለጥቃት መጋለጣቸው ያሳሰባቸው ክሩስቼቭ የአየር መከላከያው ሚናውን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲወጣ መክረዋል። ክሩስቼቭ በትዕግስት በጉዳዩ ላይ መምከር፣ ነገር ግን በአሜሪካኖች ግፊት ሚሣኤሎችን ማውጣት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ፖሊሴያቸውን ዋጋ የሚያስከፍል እና የካስትሮን መልካም ፍቃደኝነት የሚጠይቅ ነበር። ክሩስቼቭ እግዱን መጣስ ባይፈልጉም ለሀገራቸው ክብር እና ለያዙት የፖለቲካ አቋም መጠበቅ ሲሉ የተወሰኑ መርከቦቻቸው አሜሪካኖችን ፊት ለፊት ለመጋፈጥ እንዲጠጉ መመሪያ ሰጥተዋል:: ሊተኮስባቸው እንደሚችል ያውቃሉ:: ግን የሶቭየትን ተገዳዳሪነት ማሣየት ግድ ሆኖ ተሰማቸው። ሆኖም ተጨማሪ ግጭት ለመቀነስ ተጨማሪ መርከቦች ወደ ኩባ እንዳይሄዱ፣ ጉዞ የጀመሩትም ወደ ሞስኮ እንዲመለሱ አዝዘዋል:: ይህ ለአሜሪካኖች የተወሰነ እፎይታን የሰጠ መሰለ::
በዚህ መካከል የአሜሪካ ዩ-2 አውሮፕላን በሶቭየቶች አየር መቃወሚያ ተመትቶ ወደቀ። ይህ ክስተት ውጥረቱን አናረው። እውነተኛው የኒዩክሌር ጦርነት ሊቀሰቀስ የሰዓታት ዕድሜ መቅረቱን አመላከተ። አሜሪካ አፀፋ ትሰጣለች ተብሎ በሶቭየቶች ዘንድ ተሰግቶ ነበር። ነገር ግን አሜሪካኖች ከክሩስቼቭ ጋር የጀመሩትን ድርድር ዳር ከማድረስ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ ያመኑ ይመስላል፤ ነገሩን እንዲሁ አለፉት።
ኬኔዲ ጦርነት እንዲያደርጉ ግፊት የሚያደርጉ አማካሪዎቻቸውን ያላካተተ ውይይት አደረጉ። ከክሩስቼቭ ጋር ድርድር ማድረግ ቀጣይ የሚኖረውን አደገኛ የኒዩክሌር ጦርነት ማስቀረት ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ እንደሚያመዝን ውሣኔ ላይ መድረስ ችለዋል::
ክሩስቼቭ ሚሣየሎችን ከኩባ ለማንሣት አሜሪካ ኩባን የመውረር እቅዷን እንድትተው ያስቀመጡት ቅደመ ሁኔታ ተቀባይነት አግኝቷል:: ነገር ግን አሜሪካ በቱርክ የተከለቻቸውን ሚሣኤሎች እንድታስወግድ ጠየቁ:: ነገሩ በቀጥታ ግልፅ ምላሽ ባይሰጠውም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት ሁለቱ ሀገሮች በምስጢር እንዲስማሙ አድርጓል:: ሶቭየት ኅብረት መጀመሪያ ከኩባ ሚሣኤሎቿን ማውጣቷን ተከትሎ እነርሱም ከቱርክ እንደሚያወጡ ስምምነት አድርገው ነገሩን የማብረድ ተነሳሽነት አሣዩ። ነገሩ ከጫፍ ደርሶ ባለበት ክሩስቼቭ ካቢኔያቸውን ሰብስበው ለሰው ዘር ሰላም ሲባል መሸነፍ እንዳለባቸው አሳምነው በመጨረሻ ሀገራቸው ሚሳየሎቹን ከኩባ እንደምታስወግድ ለዓለም ይፋ አደረጉ።
በመጀመሪያ በሁለቱም ወገን ስሜታዊነት የሚነዳው ውሳኔ ዓለምን ወደ ከፋው የኒኩሌር ጦርነት ጫፍ አድርሷት ነበር። በመጨረሻ ግን አንዳንድ የሰከኑ አማካሪዎች የመሪዎቹን አካሄድ አስተካክለው ለታሪክ ተወቃሽ ከሚያደርገው ውሳኔ መልሰው ዓለምን ከታላቁ ውድመት ታድገዋታል። ይህ ታሪክ በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ተደግሞ በዘመናችን አይተነዋል። አሁን ነገሩን የከፋ የሚያደርገው ከአሜሪካ እና ሩሲያ አልፎ ኑክሊየር የታጠቁ አገራት ቁጥር መብዛቱ እና ያኔ ከተፈራው የላቀ ጥፋት የሚከተል መሆኑ ነው:: የቀውስ ጊዜ አመራርን እና ውሳኔን ከኬኔዲ እንዲሁም ከክሩስቼቭ ይማሯል እያልን ጽሑፋችንን በዚሁ አበቃን።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም