የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር አሥራት አጸደ ወይን ጋር ቆይታ አድርጓል:: የዩኒቨርሲቲውን የምርምር ደረጃ እና የማኅበረሰብ ግልጋሎት በተመለከተ የሰጡት ሀሳብ እንደሚከተለው ቀርቧል::
መልካም ንባብ!
ሴንተር ፎር ዎርልድ ዩኒቨርሲቲ ራንኪንግ የተሰኘ ዓለም ዓቀፍ ድርጅት ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ የሰጠው ደረጃ አለ። እስኪ ስለሱ ይንገሩን…
ሴንተር ፎር ዎርልድ ዩኒቨርሲቲ ራንኪንግ የተሰኘው ድርጅት ከፍተኛ ትምህርት ላይ መንግሥታትን የሚያማክር፣ ዩኒቨርሲቲዎችን ደግሞ በመማር ማስተማር እና በምርምር ውጤታቸው የተሻለ እንዲሆኑ የሚያግዝ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ለዩኒቨርሲቲዎች ባላቸው ተልዕኮ ደረጃ መስጠትም ሌላው ነው። እንደ አውሮፓዊያን የዘመን ቀመር ከ2012 ጀምሮ የዩኒቨርሲቲዎችን ደረጃ ሲያወጣ ቆይቷል:: መጀመሪያ አካባቢ ምርጥ 100 የዓለም የኒቨርሰቲዎችን ደረጃ ያወጣ ነበር:: ባለፉት አምስት ዓመታት ግን በደረጃው የሚሳተፉ ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ከፍ ቢል የሚል ጥያቄ በመነሳቱ የዓለማችን ምርጥ 2000 ዩኒቨርሲቶዎች የሚል ደረጃ ይዞ ሲመድብ ቆይቷል::
ከዚህ አኳያ ዩኒቨርሲቲያችን በያዝነው ዓመት ብቻ ሳይሆን ምርጥ 2000 ዩኒቨርሲቲዎች የሚለውን ደረጃ መስጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ማለትም ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ በተከታታይ የሁለተኛ ደረጃን በሀገር ውስጥ ይዞ ቆይቷል፤ በዓለም ላይ ደግሞ ከ2000 ከፍ ዝቀ ሲል ቆይቶ አምና 1487ኛ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ 1701ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል:: በዚህ ዓመት የተወዳደሩት 20 ሺህ 966 ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው:: ምርጥ 2000 ውስጥ መግባታችን ትልቅ ስኬት ነው::
ሴንተር ፎር ዎርልድ ዩኒቨርሲቲ ራንኪንግ እንደ መስፈርት የሚጠቀመው በዋናነት የትምህርት ጥራትን ነው:: ከዚያ ቀጥሎ ከዩኒቨርሲቲው ተመርቀው የወጡ ተማሪዎች ምን አይነት የስኬት ቦታዎች፤ የኃላፊነት ቦታዎች በሀገር፣ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ ይገኛሉ የሚለውንም ያያል። በተጨማሪ ተቀጣሪነት፤ የመምህራን ብቃት እና ምርምር፣ ዓለም አቀፍ ስልጠና እና ምርምር፣ ጽሑፎችን የማሳተም ብዛት፣ የሚፈጥሩት ተጽዕኖ፣ ለማኅበረሰብ ያላቸው ግልጋሎት፤ ለሌሎች ጥናት ማጣቀሻ መሆናቸው በአጠቃላይ በግብዓት፣ በሂደት እና በውጤት የጥራት መለኪያዎች ታሳቢ አድርጎ ነው:: ከዚህ አንጻር ስኬት ማግኘት መቻላችን ትልቅ አቅም ነው፤ የደረጃ ምደባውም ራሳችንን ከሌላው አኳያ የት ላይ ነው ያለነው? የሚለውን እንድንመለከት አድርጐናል፤ ምን ይጎለናል? ምን መሥራት አለብን? የሚለውንም አመላክቶናል::
በሌሎች አወዳዳሪ ድርጅቶችም ተመሳሳይ ደረጃ ነው የተሰጠን:: ይህም የኛን ቋሚ ጥንካሬ የሚያሳይ ነው:: ሰራተኛው በደንብ እንዲሠራ፣ የመንግሥት አካላት እምነት እንዲጥሉ እና እንዲያግዙን የሚያነሳሳ ነው። የመረጃ አያያዝ ክፍተት ስለገጠመ ነው እንጂ ከዚህ በላይ ደረጃ እንይዝ ነበር። በዚህ አጋጣሚ የመረጃ አያያዝን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ትምህርት ወስደንበታል::
ዩኒቨርሲቲያችሁ በ2030 ከአፍሪካ 10 ምርጥ የምርምር ተቋማት አንዱ የመሆን ርዕይ አስቀምጧል። በመሆኑም ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማውጣት ረገድ ምን ደረጃ ላይ ነን ትላላችሁ?
ዩኒቨርሲቲያችን በዋናነት የሚታወቀው የማኅበረሰቡን ችግር በመፍታት ነው:: ከታሪክ ስንነሳ ችግር የወለደው ነው፤ በ1940ዎቹ መጀመሪያ በደንቢያ ወረዳ የወባ ወረርሽኝ ተከስቶ በርካታ ወገኖቻችንን ጎድቶ በማለፉ በወቅቱ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በዚህ አካባቢ ለማኅበረሰቡ መሠረታዊ የጤና ትምህርቶችን የሚሰጥ ተቋም እንዲመሠረት አድርገዋል፤ ከአሜሪካ መንግሥት፣ ዩኒሴፍ እና ሌሎች ጋር በመሆን:: ታሪኩ ራሱ የሚነግረን ትናንትም ሆነ ዛሬ የማኅበረሰቡን ችግር ትኩረት አድርጎ እየሠራ የሚገኝ መሆኑን ነው:: የምርምር ሂደቶች በማኅበረሰብ ተሳትፎ ጭምር የሚቀረጹ ናቸው:: በተጨማሪ የባለ ድርሻ አካላትን እና የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትን ተሳትፎ ባገናዘበ መልኩ ነው:: ይህን መሠረት አድርገን ሠርተናል፤ ተጽዕኖ ፈጥረናል::
ከአለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር ከወሰዳቸው የለውጥ እርምጃዎች መካከል ዩኒቨርሲቲዎች ባላቸው ሀብት አካባቢያዊ አቅም የመለየት ሥራ አንዱ ነው። በዚህ መሠረት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከስምንቱ የምርምር ማዕከላት አንዱ ሆኖ ተመርጧል፤ በተለይ በድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራዎች እየሠራ ነው የሚገኘው:: መመረቂያ ጽሑፎች እና በመምህራን የሚሰሩ ጥናቶች የማኅበረሰቡን ችግር እንዲፈቱ ታሳቢ ተደርጓል::
የዚህን ዓመት ብቻ ብንወስድ የጎንድር ከተማ አሥተዳዳር ከንቲባውን ጨምሮ እና የተለያዩ መምሪያዎችን እንዲሁም ባለ ድርሻ አካላትን በማሳተፍ ልዩ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት አጀንዳዎችን ለይተናል:: በዚህም 14 የሚሆኑ የምርምር፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት ስድስት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር አምስት ሥራዎች እየተሠሩ ነው:: ለምሳሌ በምርምር የጤና ተቋማት ላይ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት በምርምር ለመለየት እየተሠራ ነው:: በትምህርት አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ያውን ውጤታማነት እየፈተሽን ነው:: በአጠቃላይ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የሚታዩ ችግሮችን ከእነ መፍትሔዎቹ እያመላከትን እንገኛለን::
ምርምር ላይ እንደ አንድ ትልቅ ስኬት የምናየው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታተሙ አምስት የምርምር ውጤቶች አራቱ በትምህርት ሚኒስቴር እውቅና ማግኘታቸው ነው:: ምርምሮቹ የሚደረጉት በመንግሥት በጀት ባቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ውድድሮች በማሸነፍ በሚገኝ ገንዘብ ጭምር ነው:: በዚህ ገንዘብ በአንድ በኩል የማኅበረሰብን ችግር የሚፈታ ምርምር ይካሄዳል፤ የምርምር ውጤቱም የሥራ እድል ይፈጥራል። ሌላው ደግሞ የውጭ ምንዛሬ ማምጣት በመቻሉ ሚናው ትልቅ ነው::
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር አቅሙን እንዴት እያሳደገ መጥቷል?
የምርምር አቅሙን ስንመለከት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ክፍተቶችን እየሞላ የመጣ ነው:: የመምህራንን አቅም በማሳደግ ረገድ ሰፊ ሥራ ሠርቷል:: በየዓመቱ በትንሹ ከ200 በላይ መምህራንን በማስተርስ እና ፒኤች ዲግሪ ደረጃ በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገር ያስተምራል:: ባለፉት በርካታ ዓመታት ለአቅም ግንባታ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ በመሠራቱ ዩኒቨርሲቲያችን አሁን ካለበት ደረጃ ደርሷል::
በተጨማሪ ብዙ ተሞክሮ ያላቸውን ከዩኒቨርሲቲያችን ያሉም ሆነ ከሌላ አካባቢ በሚመጡ ግለሰቦች ለወጣት ተመራማሪዎች አጫጭር ስልጠናዎችን እናሰጣለን:: ይህም ወጣቱ ተመራማሪ ለምርምሮች ትልቅ ትኩረት እንዲሰጥ እና በጥራት አንዲፈጽም ያስቻለ ነው:: ይህን በማድረጋችን ነው የምርምር አቅማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው:: ከዛ ባሻገር ዩኒቨርሲቲያችን ለዎርክ ሾፖች (ሠርቶ ማሳያዎች) እንዲሁም ለቤተ ሙከራዎች ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ነው የሚሠራው:: ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል ትልልቅ ፕሮጀክቶቻችን ከቤተ ሙከራ እና ከዎርክ ሾፕ ጋር የተያያዙ ናቸው:: ይህ የምርምር ባህላችን እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል::
አሁን አሁን የዩኒቨርሲቲያችን መምህራን በመንግሥት ወጪ ምርምር ከማካሄድ ይልቅ በአብዛኛው የውጭ ሀገራት ፈንድ ላይ ትኩረት አድርጎገው በመሥራት ላይ ናቸው:: የመማር ማስተማር ሂደቱ ወደ ምርምር ተኮር እየተቀየረ ነው:: ከቅድመ ምረቃ ወደ ድህረ ምረቃም እየተሸጋገረ ነው:: ይህም ደግሞ የምርምር ባህሉን እያሳደገ እንደመጣ ያሳያል:: ፒኤች ዲግሪ ያላቸው መምህራን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው:: ወደ ፕሮፌሰርነት እያደገ የሚመጣው ቁጥርም እየጨመረ ነው:: በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ትልቅ የለውጥ ሂደት ላይ ነው ያለው:: ከሀገር ውስጥ ተወዳዳሪነት ወደ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለመሸጋገር ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል::
በማኅበረሰብ አገልግሎት ረገድ ሕይወትን በዘላቂነት ለመቀየር ምን ተሠራ?
የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎቻችንን ከተማ ተኮር አድርገናቸዋል:: ይህንንም ስንቀርጽ ከአሥተዳደሩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርገን ነው የመረጥናቸው:: በማኅበረሰብ አገልግሎት ወደ ስድስት ፕሮጀክቶች ተመርጠው እየተሠሩ ነው::
የበጀት ዓመቱ መገባደጃ ላይ ስለሆነ የምንገኘው አብዛኞቹ ሥራዎች እየተጠናቀቁ ነው:: ከሚሠሩት መካከል የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል አንደኛው በልጆች አስተዳደግ፣ አያያዝ እና እንክብካቤ ላይ የሚሠራ ነው:: አሁን ልጆች ላይ ካልሠራን የነገዋ ኢትዮጵያ ጤናማ መሆን አትችልም። ስለዚህ በመልካም የልጆች አስተዳደግ ላይ እየሠራን እንገኛለን:: በተለይ ለመምህራን እና እናቶች ስልጠና ሰጥተናል:: የማኅበረሰብ ንጽህና አጠባበቅ ላይ እና የሚከሰቱ የጤና እክሎችን በተመለከተ የአቅም ግንባታ ስልጠና፣ የመድሃኒት አያያዝ እና አወጋገድን በተመለከተ ስልጠና ሰጥተናል:: የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ በዩኒቨርሲቲያችን አማካኝነት ብቻ ከ5 ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ እድል አግኝተዋል:: ስደትን በተመለከተ የተለያዩ የግንዛቤ ፈጠራዎችን ሠርተናል:: የከተማ ግብርናን በተመለከተ ሥልጠና ሰጥተን ወደ ተግባር አስገብተናል::
በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለሀገር ብቁ የሆኑ ተማሪዎችን የማፍራት ሥራ እየሠራን ነው:: በተለይ በአይሲቲ፣ ሮቦቲክስ እና የተለያዩ ሳይንስ ዘርፎች ወጣት የሐገር ተረካቢዎችን እያፈራን ነው። አቅም ለሌላቸው ዜጎች የህግ ማማከር እና የጥብቅና ድጋፍ እንሰጣለን::
ይቀጥላል
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም