ለዘላቂ ሰላም ንግግር እና ድርድር ወሳኝ ነው!

0
149

ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደ የሰላም ጉባኤ ላይ አማራ ክልልን ከገባበት ቀውስ ለማውጣት ንግግር እና ድርድር  የመፍትሄ መንገድ ሆኖ ቀርቧል። ይህ ይበል የሚያሰኝ ሂደት ነው። በመንግሥት በኩል የተለሳለሱ መግለጫዎች መኖራቸውም ተገቢ ነው። ከመወጋገዝ፣ ጥላቻን ከማናር፣  ነገርን ከማክረር ተቆጥቦ ወንድሜ፣ ዘመዴ፣ ወገኔ ተባብሎ ከጫፍ ወደ መሃል መምጣት ጠቀሜታው የሁሉም ነው።

የፖለቲካ ጥያቄን በነፍጥ ለማሳካት መጣር ጉዳቱ የሁሉም ነው፤ ጦርነት  ልማትን የሚበላ የስልጣኔ ጠላት ነውና።  ሀገራት ከከፍታ ወደ ዝቅታ፣ ከዲጂታል ዘመን ወደ ድንጋይ ዘመን፣ ከሰውነት ወደ አውሬያዊ ባህሪነት የተቀየሩት በጦርነት ነው። ጦርነት ያጨካክናል፤ ሰውነትን ያስክዳል፤ ትስስርን ይበጣጥሳል። በመሆኑም የጠብ መንጃ አፈ ሙዞች ተዘግተው ብሩህ ሐሳቦች በፍትሐዊነት ዳኝነት ሊሰጡ ይገባል። የተለያዩ ሀገራት ተመሳሳይ ችግር ገጥሟቸው ከዘመናት ችግራቸው የወጡበትና ወደ ሰላም የመጡበት እንዲሁም የፈቱበት መንገድ ድርድርና ንግግር  ነው፡፡ በድርድር አሸናፊና ተሸናፊ ሳይኖር ሁሉን አሸናፊ ባደረገ ሂደት ፍትሕን ማረጋገጥ ይቻላል።

አሁንም እየተነሳ ያለው የንግግር እና የድርድር ሂደት እውን እንዲሆን፣ ወደ ድርድር የሚገፉ በጎ እርምጃዎችን በመደገፍ ለአንድ ወገን ብቻ ሳይተው መተባበር ያስፈልጋል፣ አመቻች  ኮሚቴው በይፋ ሥራውን እንዲያከናውንና  ድርድሩ እውን እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። ንግግር እና ድርድር  የሰላም አጃቢዎች ናቸው። በንግግር እና ድርድር ሰላምን ማስፈን ይገባል። በድርድር ወንድም ከወንድሙ ጋር በይቅርታ ይተቃቀፋል። ይህም የአብሮነት፣ የልማት፣ የዕድገት እና ሥልጣኔ በርም ይከፈታል።

በነገራችን ላይ የሽግግር ፍትሕም ሆነ ሀገራዊ ምክክሩ ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው በእውነተኛ ውይይት የተኩስ ድምፆች ቁመው ሁሉም ተደራዳሪ ወገኖች በቀናነትና በመፍትሔ አፍላቂነት ሲሳተፍበት ብቻ ነው። ተኩስ ሳይቆም የሚደረግ ምክክርም ሆነ የሽግግር ፍትሕ አይሰላም። የሽግግር ፍትሑም ሆነ የሀገራዊ ምክክሩ ዓላማም  ለትናንት፣ ለዛሬ እና ለነገ የሚበጅ ሀገራዊ ሰላምን ማምጣት እና የጎለበተ ሀገረ መንግሥት ማቆምን ኢላማ ያደረገ ነው።

“ድርድሩ ይግፋ፣ ድርድሩ አይገፋ፣

ጥላቻ ይጥፋ፣ አብሮነት ይስፋ፣

ይህ ነው ለሕዝባችን ተስፋ።”

ለሕዝባችን ሰላም ሲባል ከእብሪት፣ ከሴራ፣  ከተሳሳተ ትንታኔ፣ ከአጉል ተስፋ በመውጣት ነባራዊ ሁኔታውን አጥንቶ  ለንግግር፣ ለድርድር፣ ለተቋማዊ መሻሻል መዘጋጀት ከሁሉም ወገን የሚጠበቅ ሰብዓዊ፣ ሞራላዊ እና ማህበረሰባዊ ኃላፊነት ነው።

ድርድሩ እንዲሳካ ሁሉም ወገን ጥረት እና ልፋቱን ሊያስቀጥልም ይገባል- ድርድሩን በፍጥነት መተግበር የፖለቲካ ሥራ ብቻ ሳይሆን የነፍስ አድን ሥራም ነውና፡፡

 

በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here