ኮሌጅ የበጠሱ ስፖርተኞች

0
124

ስፖርተኞች ሜዳ ላይ በሚያሳዩት ድንቅ እንቅስቃሴ ከብዙ ሚሊዮን ተመልካች አድናቆት እና ሙገሳ ይቸራቸዋል። ይሁን እንጂ ስፖርተኞች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በመቀላቀል ትምህርታቸውን ይከታተላሉ ብሎ ብዙዎች እንደማያስቡ ዘ ኢንድፔንደን አስነብቧል።

ስፖርተኛነት ለዘላለም የሚቆይ ሥራ ባለመሆኑ ስፖርተኞች ጡረታ ከወጡ በኋላ፣ ጉዳት ሲገጥማቸው እና በተለያዩ ምክንያቶች ከስፖርቱ ሲገለሉ ወደ ሌላ ሥራ የሚሰማሩበትን አማራጭ ዘርፍ ይፈልጋሉ። ይህንን ቀድመው የተረዱ አንድ አንድ ስፖርተኞችም በዕውቀት ራሳቸውን ለማብቃት በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመግባት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ስፖርትን እና ትምህርትን ማመጣጠን ቀላል አለመሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ። ብርቱዎች ግን ትምህርት የእድገት እና የስኬት ዋነኛ መሳሪያ መሆኑን ተረድተው አድርገው አሳይተዋል፤ አሁንም እያሳዩ ይገኛሉ።

በ2024ቱ የጀርመን የአውሮፓ ዋንጫ ድንቅ አቋማቸውን እያሳዩ ከሚገኙ ታዳጊ የእግር ኳስ ኮከቦች መካከል ስፔናዊው የፊት መስመር ተሰላፊ ላሚን ያማል አንዱ ነው። ባለተሰጥኦው ታዳጊ በትንሽ ዕድሜው (በ16 ዓመት ከ338 ቀናት) በአውሮፓ ዋንጫ በመሰለፍ አዲስ ክብረወሰን ሰብሯል፡፡ ይህ ተጫዋች ከሰሞኑን የእንግሊዝ እና የስፔን ጋዜጦች መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱ አይዘነጋም።

ላሚን ያማል የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ነው፡፡ በጀርመን ብሔራዊ ቡድኑ ባረፈበት ሆቴል ከኳሱ ጎን ለጎን የቀለም ትምህርቱን በበይነ መረብ በመከታተል ላይ ይገኛል። ከልምምድ መልስ በቀጥታ ወደ መኝታ ክፍሉ በማምራት ትምህርቱን ያጠናል፤ የቤት ሥራዎቹንም በአግባቡ ይሠራል፣ ለፈተናም ይዘጋጃል። እንደ ኳሱ ሁሉ በትምህርቱም ጎበዝ ተማሪ መሆኑን መምህራኑ ይመሰክሩለታል።

የዚህን ድንቅ ባለተሰጥኦ የእግር ኳስ ኮከብ ብርታት የተመለከቱ የመገናኛ አውታሮች በመኝታ ክፍሉ ሲያጠና እና የቤት ሥራ ሲሠራ ምስሉን አሰራጭተውታል። ይህም የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። በዚህ የበኲር ዕትማችን በስፖርቱ ዓለም ስኬታማ የሆኑ እና የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በመቀላቀል ራሳቸውን በዕውቀት ያበለፀጉ ስፖርተኞችን እንዳስሳለን።

አሜሪካዊው የቀድሞው የቅርጫት ኳስ ኮከብ ማይክል ጆርዳን በቅርጫት ኳስ ስፖርት ታሪክ እጅግ ስማቸው ከናኘ ስፖርተኞች ውስጥ ቀዳሚው ነው። ማይክል ጆርዳን በቅርጫት ኳስ ህይወቱ ለሁለት ክለቦች ብቻ ተጫውቶ ማለፉ አይዘነጋም። በተጫወተባቸው ቺካጎ ቡልስ እና ዋሽንግተን ዊዛርድስ በርካታ የግል እና የቡድን ክብሮችን ተጎናጽፏል።

ጆርዳን ከስፖርት ህይወቱ ባሻገር በትምህርት ዓለምም ስኬታማ እንደሆነ ታሪኩ ያስረዳል። አሜሪካዊው የቀድሞ ስፖርተኛ በ1986 እ.አ.አ በካልቸራል ጂኦግራፊ ከኖርዝ ካሮሊና ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ተቀብሏል። ማይክል ጆርዳን በተለያዩ መድረኮች ማጣቀሻ ሀሳቦችን በማንሳት የአየር ብክለትን አጥብቆ ሲያወግዝ በተደጋጋሚ ይደመጣል።

በዚህ ዘመን ካሉ ምርጥ የቅርጫት ኳስ ስፖርተኞች መካከል ደግሞ ስቴፈን ከሪ አንዱ ነው። የ36 ዓመቱ የቅርጫት ኳስ ባለተሰጥኦ እ.አ.አ ከ2009 ጀምሮ በአንድ ክለብ ታምኖ ለጎልደን ስቴት ዋሪየርስ እየተጫወተ ይገኛል። ከሪ በትውልዱ ካሉ ድንቅ ስፖርተኞች መካከል አንዱ ስለመሆኑም ብዙዎች ይስማሙበታል። የአንደር አርመር የጫማ ብራንድ ባለቤት የሆነው ከሪ በ2022 እ.አ.አ ነበር፣ ከዴቭድሰን ኮሌጅ በሶሺዮሎጂ የትምህርት ዘርፍ የተመረቀው።

ይህ ስም እንደ ፔሌ፣ ሮናልዶ እና ሮማሪዮ በብራዚል ምድር ዝነኛ እና ገናና ነው- ዶክተር ሶቅራጠስ። ብራዚላዊው የቀድሞው አማካይ ጥሩ ክህሎት እና ችሎታ የነበረው ሲሆን በታላላቅ የብራዚል ክለቦች ተጫውቶም አሳልፏል። ከፍላሚንጎ፣ ሳንቶስ እና ኮረንቲያስ ጋርም የተለያዩ ዋንጫዎችን አሳክቷል። ሶቅራጠስ ከእግር ኳስ ስፖርት ጎን ለጎን በህክምና ትምህርት የዶክትሬት ዲግሪውን ተቀብሏል።

ከእግር ኳስ ሜዳ ላይ ካለው ችሎታው በተጨማሪ በጥልቀት በማስብ የሚታወቀው የቀድሞው ተጫዋች በ1989 በአውሮፓውያን የጊዜ ቀመር አቆጣጠር ነበር በህክምና ትምህርት የዶክትሬት ዲግሪውን የተመረቀው። እ.አ.አ በ2004 ከእግር ኳሱ ከተገለለ በኋላ በተማረበት የህክምና ትምህርት ዘርፍ አገልግሏል።

ዶክተር ሶቅራጠስ በተለያዩ የሙያ ዘርፎችም ያገለገለ ሲሆን በሳል የፖለቲካ ተንታኝ እንደነበረም የግል ማህደሩ ያስነብባል። በተጨማሪም በተለያዩ ጋዜጦች እና መጽሔቶች አምደኛ በመሆን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትንታኔዎችን አስነብቧል። በሀገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ የቴሌቭዥን ጣቢያዎችም በስፖረት ተንታኝነት ማገልገሉን የተጫዋቾች ማህበር ድረገጽ መረጃ ያሳያል። ሁለገቡ ዶክተር ሶቅራጠስ በ2011 እ.አ.አ ነበር ባደረበት ህመም ምክንያት በ57 ዓመቱ ህይወቱ ያለፈው።

የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትዱ ግብ ጠባቂ ኢድዊን ቫን ደር ሳር በዓለማችን ከታዩ ምርጥ ግብ ጠባቂዎች አንዱ ስለመሆኑ አያጠያይቅም። ቫን ደር ሳር በእግር ኳስ ህይወቱ ስኬታማ ጊዜያትን በአያክስ አምስተርዳም እና ማንቸስተር ዩናይትድ ቤት አሳልፏል። በአጠቃላይ በእግር ኳስ ህይወቱም 26 ዋንጫዎችን አሳክቷል።

በ2011 እ.አ.አ ከእንግሊዙ ክለብ ጋር ከተለያየ በኋላ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ እንዲሆን በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም ለመማር ባለው ከፍተኛ ጉጉት ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉን በአንድ ወቅት በቃለ ምልልሱ ተናግሯል። የሁለት ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ኔዘርላንዳዊ፤ በስፖርት እና ብራንድ ማኔጅመንት የሁለተኛ ዲግሪውን ተቀብሏል። ቫንደር ሳር አሁን ላይ ባደገበት አያክስ አምስተርዳም ክለብ፣ በሥራ አስፈፃሚነት እያገለገለ ይገኛል።

አቤል ማኖመይ በጋና ፕሪሚየር ሊግ እየተጫወተ ይገኛል። ጋናዊው አጥቂ ለትምህርት ባለው ጥልቅ ፍቅር እና ፍላጎት ይታወቃል። በጋና እግር ኳስ ታሪክ  የሁለተኛ ዲግሪ የያዘ ብቸኛው እግር ኳስ ተጫዋች ሆኖ ስሙ ሰፍሯል። የ32 ዓመቱ አጥቂ በጤና፣ አካላዊ ትምህርት፣ መዝናኛ እና ስፖርት የመጀመሪያ ዲግሪውን ተመርቋል። የሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ በጤና አካላዊ ትምህርት፣ መዝናኛ እና የስፖርት ፍልስፍና የትምህርት መስክ ከዊንባ ዩንቨርሲቲ አጠናቋል። አቤል ሌሎች ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጫዋቾች ወደ ዩንቨርሲቲዎች እንዲገቡ እና ከእግር ኳስ ህይወታቸው ጎን ለጎን ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ምክንያት ሆኗል።

የቀድሞው የእግር ኳስ ተጫዋች አንድሬ አርሻቪን ብዙዎች በፕሪሚየር ሊጉ ክለብ አርሴናል ያስታውሱታል። ሩሲያዊው የቀድሞው የጨዋታ አቀጣጣይ በእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ  ጥሩ የፋሽን ተከታይ እንደነበረ ብዙዎች ይመሰክሩለታል። ይህ  ስሜቱ አድጎ እና ጎልብቶ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የፋሽን ዲዛይን እንዲያጠና ምክንያት ሆኖታል።

አርሻቪን ለፋሽን ያለው የማይደበዝዝ ስሜት ከመጀመሪያ ዲግሪም አልፎ የሁለተኛ ዲግሪ እንዲማር አስችሎታል። የ43 ዓመቱ የቀድሞው የአርሴናል እና የፒተርስበርግ ተጫዋች አሁን ላይ በሀገሩ ሩሲያ ታዋቂ ከሆኑ የፋሽን ዲዛይነሮች መካከል አንዱ ሆኗል።

አሰልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ በዚህ የክረምቱ የዝውውር ወቅት የባቫሪያኑ ክለብ ባየርን ሙኒክ አለቃ ሆኖ መሾሙ አይዘነጋም። የ38 ዓመቱ አሰልጣኝ ከ2008  እስከ 2019 እ.አ.አ በማንቸስተር ሲቲ ድንቅ ጊዜን ማሳለፉ አይዘነጋም። የቀድሞው የመሀል ተከላካይ እ.አ.አ በ2017 ነበር የሁለተኛ ዲግሪውን በንግድ ሥራ አስተዳደር በአሊያንስ ማንቸስተር ቢዝነስ ትምህርት ቤት ያጠናቀቀው። አዲሱ የባየርሙኒክ አሰልጣኝ የሠራው የመመረቂያ ፕሮጀክቱም ድንቅ እንደነበር የዘ ኢንድፔንደንት መረጃ ያትታል።

በአሮጊቶቹ ቤት 18 ዓመታትን አሳልፏል፤ በአንጸባራቂው የእግር ኳስ ህይወቱ ከቱሪኑ ክለብ ጋር የሴሪኤ፣ የኮፓ ኢጣሊያ እና ሌሎችንም በርካታ የግል ክብሮችን አሳክቷል፤ በትውልዱ ካሉ ምርጥ ተከላካዮች መካከል አንዱ መሆኑንም ይነገራል- ጣሊያናዊው ተከላካይ ጆርጂኖ ቺሊኒ።

የ39 ዓመቱ የቀድሞው የእግር ኳስ ተጫዋች በእግር ኳስ የእድሜ ማምሻው ወደ አሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከር አቅንቶ ለሎሳንጀለስ ክለብ ለአንድ ዓመት ያህል መጫወቱ አይዘነጋም። ቺሊኒ በ2010 እ.አ.አ ከዩነቨርሲቲ ኦፍ ቱሪን በኢኮኖሚክስ እና ኮሜርስ የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል። በ2017 እ.አ.አ ደግሞ በንግድ ሥራ አስተዳደር(Masters of business administration) የሁለተኛ ድግሪውን ይዟል።

እንግሊዛዊቷ የቀድሞዋ ብስክሌተኛ ቪክቶሪያ ፔንድልተን ከቀድሞ ምርጥ ሴት ብስክሌተኞች መካከል አንዷ ናት። ቪክቶሪያ እ.አ.አ ከ2005 እስከ 2012 የሴቶችን የዓለም ብስክሌት በበላይነት ተቆጣጥራው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።  ቪክቶሪያ እ.አ.አ በ2008 የቤጂንግ እና በ2012 የለንደን ኦሎምፒክን አሸንፋለች። የቀድሞ ብስክሌተኛዋ ለትምህርት ከፍተኛ ፍላጎት የነበራት ሲሆን በ2002 እ.አ.አ በኖርተምበሪያ ዩንቨርሲቲ በስፖርት እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቃለች።

ዌልሳዊው የራግቢ ስፖርት ተጫዋች ጂሚ ሮበርትስ በሀገሩ ዌልስ ለበርካታ የራግቢ ቡድኖች ተጫውቷል። አሁን ላይ እየተጫወተም ይገኛል። የ37 ዓመቱ የራግቢ ስፖርተኛ በ2013 እ.አ.አ በካርዲፍ ሲቲ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ዶክትሬት ዲግሪውን ተቀብሏል።

ስፔናዊው የቀኝ ተመላላሽ ሄክቶር ቤለሪን በማርኬቲንግ፣ ዩሀን ማታ በስፖርት ሳይንስ እና ፋይናንስ፣ አንድሬስ ኢኔስታ በባዮሎጂ እና ስፖርት ሳይንስ እንዲሁም ሮሚዮ ሉካኩ በቱሪዝም እና ህዝብ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ለአብነት የሚጠቀሱ ስፖርተኞች ናቸው።

በአውሮፓ እና በሌሎች አህጉሮች የሚገኙ ስፖርተኞች ሳምንታዊ ደሞዛቸው ከመንግስት እና የግል ተቋማት ሠራተኛ ዓመታዊ ደሞዝ እንደሚበልጥ አያጠያይቅም። ቢሆንም ግን ከዝና እና ገንዝብ ባለፈ ብዙ ስፖርተኞች እራሳቸውን ማስተማር እና በዕውቀት ማነጽ ያስደስታቸዋል። እኛ ሀገርስ?  መልሱን ለእናንተ ለአንባቢያን በመተው፣ የሀገራችን ስፖርተኞች ከላይ ከጠቀስናቸውን ስፖርተኞች ልምድ እንዲያዳብሩ መበረታት ይኖርባቸዋል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here