የተረሱት ጥቁር አፍሪካውያን በሕንድ

0
162

በደም ግባታቸው ዓለም ያደነቃቸው መኖሪያ በሆነችው ሕንድ ጠያይም ሕንዳውያን መኖራቸው ያስገርም ይሆናል። ቁጥራቸው ቢያንስም የሕንድ ድምቀት ናቸው። የቆዳ ቀለማቸው ጥቁርነት ከብዙኃኑ ቢለይም ለሕንድ መሰልጠን ግንባር ቀደም የሚያስብል ታሪክ አላቸው። ከአፍሪካ የዘር ሃረጋቸው የሚመዘዘው እነዚህ ጠያይም አፍሪካዊ ሕንዳውያን ሕይወታቸውን በሕንድ ምድር መስርተው መኖር ከጀመሩ ከስምንት ክፍለ ዘመናት በላይ የሆናቸው፣ በፓኪስታን እና በሰሜን ምእራብ ሕንድ የከተማ ስልጣኔን ያስጀመሩት የተረሱ ግን ትልቅ ባለውለታ የሆኑ ማህበረሰቦች ናቸው።

ሳይዲዎቹ ይባላሉ። እናም እነዚህ የተረሱት ከረጅም ዘመን በፊት በሕንድ እየኖሩ ግን ተረስተው ያሉት ጠያይም ሕንዳውያን እነማን እንደሆኑ፣ የአኗኗር ዘይቤያቸውን፣ ባህላቸውን እና መሰል መረጃዎችን ልናጋራችሁ የዚህ ሳምንት የሽርሽር አምዳችን ርዕሰ  ጉዳይ አድርገናቸዋል፣ አብራችሁን ቆዩ።

በሕንድ የሚኖሩት ሳይዲዎቹ መነሻቸው ከምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ነው። የዘር ሀረጋቸው ከባንቱ ሕዝብ ይመዘዛል። ከሰባተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ፣ በመጀመሪያ በአረብ ነጋዴዎች አማካይነት በኋላም ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በፖርቹጋሎች እና በእንግሊዞች አማካይነት ወደ ሕንድ ምድር እንደተጓጓዙ ይታሰባል።

ብዙዎቹ ሳይዲዎች በባሪያ መልክ፣ ነገር ግን የተወሰኑቱ በሰራተኝነት፣ በአናፂነት፣ በአንጥረኝነት እና በግንበኝነት ወደ ሕንድ የተወሰዱ እንደሆነ ይታመናል። ምናልባትም አንዳንዶቹ ራሳቸውን የቻሉ ነጋዴዎች ወይም በአረብ ሰራዊት ውስጥ ወታደር በመሆን መጥተው የቀሩ አፍሪካውያን ናቸውም ይባላል። ጥቂት የሆኑ ሲዲዎችም በ14ኛው እና በ16ኛው ክፍለ ዘመናት ባለው ጊዜ ውስጥ በአንዳንድ የሕንድ አካባቢዎች ላይ የነገሥታትነት፣ የወታደራዊ አዝማችነት፣ እግረኛ ወታደርነት እና የአስተዳዳሪነት ደረጃ ይዘው እንደነበር ይነገራል።

ሕዝቡ በዋናነት፣ ጋዎ፣ ጉጅራት፣ ካርናታካ፣ ማሃራሽትራ እና ታሌንጋና በተባሉ የሕንድ አምስት ክልሎች ውስጥ ይኖራሉ። ነገር ግን ዘጠና በመቶ የሚሆኑት በጉጅራት ወይም ካርናታካ ውስጥ ነው የሚገኙት።

ለአፍታ አይኖቻችንን ወደ ሕንድ እናንሳ ወደ ህንድ እንመልከት፡፡ ወደ ህንድ የሚመጡት አፍሪካውያን እንደ ነጋዴ፤ ወታደር፤ ሰራተኛ እና ባለሙያ ሆነው ከገቡ በኋላ በሕንድ ተላምደው ይኖራሉ፡፡ እንደ ነጋዴዎች ሆነው ሙስሊም መር በሆኑ የመካከለኛው ዘመን ሕንድ ዴካን በተባለች ደቡባዊት ክፍል አፍሪካውያን ከቤተመንግሥት ሰራተኝነት እስከ ወታደራዊ መኮንንነት ሰፊ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት እስከ 300ሺህ ሚገመቱ አፍሪካውያን ሕንዳውያን በሕንድ ይኖራሉ፡፡ በእነርሱም ውስጥ ማክራን በተባለ የፓኪስታን ክልል፤ ጉጅራት በተሠኘ ሕንድ ክልል፤ በአንድራ ፓሬድሽ እና በካርናታካ በደልሂ፤ ኮልካታ እና ቦምቤይ በሚባሉ ሕንድ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ አፍሪካውያን ሕንዳውያንን ያካትታል ፡፡ ለረጅም ዘመን ያህል ሀበሽ በሚል ስም ይታወቁ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በስፋት የተለመደ መጠሪያቸው ሳይዴ ሻይዴ ሚል የሚል እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡ የስሙ አመጣጥ ላይ ብዙ አይነት ማብራሪያዎች ቢኖሩም ይበልጥ የቀረበው ትርጉም ከአረበኛ የተወሰደ መሆኑ ነው፡፡ ትርጉሙም ጌታየ እንደማለት ነው ይላል ኢንሳክሎፔዲያ ብርታኒካ፡፡

አፍሪካዊ ሕንዳውያን ሀገረ ሕንድን በተለያየ መልኩ አበልጽገዋል፡፡ አስደናቂ ሆኑ ሕንጻዎች፤ በአፍሪካ ሕንዳውን የተገነቡ ናቸው፡፡ ሣዴ ሰይድ የተባለው በሕንድ አህመዳባድ ከተማ ውስጥ ያለው መስጅድ ይጠቀሳል፡፡

በታሪክ እንደሚታወቀው እንግሊዝ የባሪያ ንግድን በሕግ የከለከለችው ከ1800ዎቹ አጋማሽ ቀደም ብሎ ነበር። በባርነት እንዳይታደኑ በመፍራት የሕንድ ምእራባዊ ጠረፍን ይዞ ባሉ የወደብ ከተሞች ይኖሩ የነበሩት ብዙ ሳይዴዎች፣ በካራናታካ ክልል ውስጥ ወደ ሚገኘው የኡታራ ካናዳ አውራጃ ጫካው እምብርት ድረስ ዘልቀው ተሰድደው ሄደዋል። በአንዱ ጎን የአረቢያ ባህርን ቁልቁል መመልከት በሚቻልበት እና በሌላኛው በኩል ተራራማውን ምእራባዊ ጋትስን ማየት የሚያስችለው የሙሪዲሽዋር ጠረፋማ ከተማ አንዱ ጥቅጥቅ ወዳለው የኡታራ ካናዳ አውራጃ ጫካ መግቢያ በር ነው።

በዚህ ስፍራ የሚኖሩ ሳይዲዎች በዋናነት ኮንካኒ የተባለውን የአካባቢ ዘዬ የሚናገሩ ቢሆንም የክልሉ የስራ ቋንቋ የሆነውን ካናዳ የቋንቋን አቀላጥፈው ይናገራሉ። በአለባበሳቸው ባህላዊውን የሕንድ ልብሶች የሚያዘወትሩ በሚያስገርም ሁኔታ ከሌሎች የአካባቢው ማህበረሰቦች ጋር በቀላሉ እና በተፈጥሯዊ ሁኔታ የተላመዱ ናቸው። አብዛኛዎቹ ቤተሰቦች በትናንሽ መንደሮች፣ የበተገለሉ ቡድኖች ውስጥ  ወይም በተናጠል አባወራዎች ደረጃ ይኖራሉ። ብዙሃኑ ሳይዴዎች በእርሻ ስራ ተሰማርተው ይሰራሉ። ሩዝ፣ አርካ እና ሌሎች ለገበያ ተፈላጊ ምርቶችን ያመርታሉ።

በካርናታካ የሚኖሩ ሳይዴዎች የሂንዱ፣ የክርስትና ወይም የእስልምና ሃይማኖቶችን ይከተላሉ። ሀይማኖት በሳይዴዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ነገር ግን በሕዝብ መካከል በፍፁም የክፍፍል መሳሪያ አድርገው አይጠቀሙበትም። ሲዲዎቹ ከሀይማኖት ውጭ ሁላቸውም የአንድ ዘር ትውልድ እንደሆኑ ያምናሉ፣  እናም ብዙዎቹ ሳይዴዎች እርስ በእርስ የተዛመዱ ናቸው። በመሆኑም፣ እርስ በእርስ ይከባበራሉ። ጠንካራ የማኅበረሰባዊ ስሜት አላቸው። እንዲሁም የጋራ ማንነትን አዳብረዋል።

ሲዲዎች ወይም አፍሮ ሕንዳውያን የአንድ ጎሳ ማሕበረሰብ ሲሆኑ በካርናታካ፣ ጉጅራት ጠረፋማ አካባቢና እና በተወሰኑ የአንድህራ ፕራዴሽ በተባሉት የሕንድ ክልሎች ይገኛሉ። በሲዲዎች ዘረ መል ላይ በተደረገ ሳይንሳዊ ምርምር መሰረት ሲዲዎች ከአፍሪካ፣ ከሕንድ እና ከፖርቱጋል የዘር ሀረግ ትስስር እንዳላቸው ፍንጭ ተገኝቷል። በተጨማሪም የተደረገ ምርምር እንዳረጋገጠው ሲዲዎቹ የትውልድ ሀረግ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ ክፍል ካሉ የባንቱ ቋንቋ ተናጋሪ ዘሮች ይነሳል። ይህም  ናሽናል ላይብራሪ ኦፍ ሜዲስን በተሰኘ ድረ ገፅ ላይ ተፅፎ ይገኛል።

በሕንድ ሥልጣኔ  ውስጥ  ትልቅ  ስፍራ የተሰጣቸው  እነዚህ  አፍሪካዊ  ሕንዳውያን ዛሬ ተገቢው ስፍራ አልተሰጣቸውም፡፡  ተረስተው፤  በቆዳ ቀለማቸው  ጥቁርነት ተንቀው አብዛኛዎቹ ከሰዎች ርቀው በጫካ ሊኖሩ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here