ሰላም!

0
173

በንግግራችን ቢያንስ በቀን አንዴ ሳንጠራው አንውልም። የመኖራችን ዋስትናም ጭምር ነው። “ሰላም ነው? ሰላም ዋላችሁ? ሰላም ጤና ይስጥልን! ሰላም ሁኑ!” ወዘተ. እያልን ብንቀጥል በቀን ውሏችን ከአፋችን የማይታጣ ሐሳብ ነው፤ ሰላም። ሰላም ለሰው ልጅ ብቻም አይደለም ለፍጥረታት ሁሉ ሕልውና መሰረት ነው። የሰላም ተፈጥሮው ዓለም አቀፋዊ ነው። ምንጩም ውስጣዊ ነው። ከውጪ ተቀድቶ በልገሳ ወይም በደግነት የሚሰጥ አይደለም። የሰው ልጆች ተፈጥሮ በራሱ ሰላም ነው። ኑሮ ይሉት ስንክሳር ግን ይህንን ቅዱስ መንፈስ በአሉታዊ ሐሳቦች ይሞላዋል።

የሰላምን ዋጋ የተረዳው ድምጻዊ ልዑል ሲሳይ “እውነት ሰላም ትሙት?!” ብሎ ይጠይቀናል። ሰላም ሁለመናችን፣ የሰላም ድንበር እና አጥሯም፣ፍቅርም እሷው በመሆኗ፣ ትዳርም ቢታሰብ ያለሰላም ከንቱ ስለሆነ ነው ልዑል “ ሰላም ትሙት?!” ብሎ የሚጠይቀን።

ሰላም የጋራ ሕልውናችን መሰረት ነው። በጋራ እጣ ፋንታ ያስተሳሰረን ሰዎች መጠለያችን፤ የአደጋ ጊዜ ማምለጫችን መርከባችን ነው፤ ሰላም። በአንደኛው ጫፍ መታወክ ከገጠመው ሌላኛው ጫፍ ጤንነቱ ይታወካል። ራሴን አመመኝ የሚል ሰው ሙሉ ሰውነቱ መታወኩ አይቀርም። የጋራ መኖሪያ ደሴታችንን ሰላምን አፍርሰን ወደ ጥልቁ የግጭት ሐይቅ መግባታችን ለልዑል ገርሞታል።

መነጣጠል ያልነበረብን የአንዲት ሃገር ሕዝብ ተጋጭተን አንዱ በሌላው ሞት ሊደሰት አይችልም። ግራ እጁን በቀኝ እጁ ቆርጦ ማነው የሚደሰተው? አንዱ ሲከፋው ሁሉም ይከፋዋል፤ አንዱ ሲደሰት ሁሉም ደስ ይለዋል። ተው እረፉ የጋራ ደሴታችንን እናክብር፤ በመኖሪያችን መፍረስ እንደምን ቆመን እንሳቅ ይለናል፤ ልዑል። ሰላም ይህን ያህል ዋጋ እያለው ዓለም ወደ ግጭት የመግባቱ ነገር ገርሞት ነው ልዑል ሲሳይ እየደጋገመ  “እውነት ሰላም ትሙት?!” በማለት የሚጠይቀን::

“የክብር ሰንደቅ የነጻነት ሐውልት

እስትንፋስ ሳለች የፍቅር አንበደት

እውነት ሰላም ትሙት?!” ሰላምን ገድለናት  እንዴት ግጭትን  እንመርጣለን በማለት ደጋግሞ ይጠይቃል::

ሳሚ ባርያውም “ሰላም” የሚል ርዕስ በሰጠው  ሙዚቃው የሰፈር መንደሩን ሰላም ምኞት ከጥቅሙ ጋር ይናገራል፤ የነገ ሕይወታችን  ስኬት እና እድገት በሰላም ላይ የተመሰረተ ነው ሲል::

“ሰላም ይሁን ሀገሩ ሰላም ይሁን መንደሩ

ሰላም ይሁን ሀገሩ ቀየ እና ሰፈሩ

ዋናው ነገር ሰላም  ዋናው ነገር ጤና

እናያለን ብዙ እናያለን ገና”

ሰው ከሰላም ጋር ረጂም ምኞት እና ተስፋ አለው። የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ሰላም ብቻ መሆኑን ነው በግጥሙ የምንመለከተው:: ሃገር ሰላም ሲሆን የሰው ልጅ ሕልውናው አያሰጋውም:: ሞት በደጁ አያንዣብብም:: ከቤት ወጥቶ በደህና የመመለሱ ጉዳይ አያሳስበውም:: የሰው ልጅ ሰላም ሲሆን ሞትን እንዴት እንደሚፈራት፣ እንዴት እንደሚሳቀቅ መገመቱ አይከብድም:: ለነገ የመኖር ተስፋ አለውና ረጅም እድሜን ከፈጣሪው ይለምናል:: የልጅ ልጅ አይቶ አቅፎ ስሞ፤ የዘር ሐረጉን አስቀጥሎ በኩራት ያልፋል:: ይህንን የሰው ልጅ ሞኞት ነው ሳሚ ባርያው የሚነግረን:: በሳቅ በደስታ የሚኖርበት ተጨማሪ ዘመንን ከማቱሳላ እሰከመመኘት ሚያደርስ ምድራዊ ኑሮን ይመኛል::

“ከማቱሳላ እድሜ ስጠኝ መርቅና

ጊዜ ካደለኝ ገና አያለሁ ገና ገና”

ሲል ለመኖር የበለጠ ይጓጓል:: ይህንን ያስመኘው ደግሞ ሰላም መኖሩ ነው:: ሰላም ይሁን እያለም ይለምናል:: ዛሬ ሰዎች በምድር 60 ዓመታትን በሚኖሩበት አማካይ እድሜ ላይ ሰላም ሲኖር እንደ ማቱሳላ ትቢያ ለብሶ ከዘጠኝ መቶ በላይ ዓመታትን መኖርን ያስመኛል:: ሳሚ ሰላም ይሁን የሚለውም ለዚህ ነው::

በማሕሙድ አህመድ ሙዚቃ ውስጥ ያለው የሰላም ሐሳብ ድንበር አልባዋን ሰላም ለሰዎች እና ፍጥረታት ሁሉ የሚመኝ ነው:: በዓለም ዙሪያ ሁሉ የሰው ልጅ ሰላም እንዲሆን ይመኛል::አየሩ እና ነፋሱ ሁሉ ሰላም ሰላም ይንፈስ ይላል:: የጦርነት አረር ሲጠፋ  አየሩ ከብክለት ነጽቶ፣ የዱር እንስሳት እና  አዕዋፍ በጎጇቸው ውስጥ  ባሉበት የሰላም ፋና እንዲበራላቸው፣

“በዓለም በዓለም

ይስፈንልን ሰላም”

ብሎ ያዜማል:: ጦርነት የሰው ልጅ እዳ ብቻ አይደለምና ነው ማህሙድ ለዱር እንስሳቱ ሁሉ ሰላም የሚመኘው:: አፍላ ጦርነት ባለበት ይቅርና ከዓመታት በፊት ጦርነት በተካሄደበት  ሜዳ እንኳን አየሩ፣ አፈሩ፣ እጽዋቱ  ሁሉ ተጎሳቁለው ይታያሉ:: የማህሙድ ምኞትም ወደ ሰው ልጆች ሰላማዊ ኑሮ ተሻግሮ  ከግጭት ይልቅ ለሰላም እጅ ለእጅ መያያዝን ይጠቁማል:: ሰላም የትውልድ ጸጋ ነው::

“ሕጻናት እንዲያድጉ በንጹህ አዕምሮ

ነጻ ህሊናቸው ጎልብቶ እና ዳብሮ፤

ወጣት ሽማግሌ የሰው ዘሮች ሁሉ

ሰላም ለዓለማችን ይላሉ በሙሉ፤

ዘንባባ ዘንጥፈን እርግቦችን ለቀን

ዘር ቀለም ሳንለይ ጥላቻን አርቀን፤

ለሰው ልጆች ደስታ ለሰው ልጆች ፍቅር

ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ለሰላም እንዘምር”

አርባኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሮናልድ ሬገን “ሰላም የግጭት አለመኖር አይደለም:: ግጭትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት  እንጂ”  ሲሉ አስቀምጠውታል:: ስለ ሰላም ብዙ ብዙ ተብሎለታል:: ሰላም ውስጣዊ  መንፈስ ነው:: ማህሙድ አህመድ እኛ ሁላችንም  ለሰላም እንዘምር፤ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለሰላም እንዘምር በማለት የሚቀሰቅሰው ሰላም ባህሪዋ የብዙኀን በመሆኑ ነው:: ሰላም ትሕትና ይፈልጋል:: በጥላቻ ከሚታጣው ይልቅ በሰላም የሚገኘውን ጥቅም በማሰብ አንገትን ሰበር አድርጎ ከእኔ ይቅር ማለትን ይፈልጋል::

ድምጻዊ ጸጋየ እሸቱም በሙዚቃው የሰላምን ፋይዳ ከፍ አድርጎ አስተጋብቷል::  በጊዜያዊ ግጭት ተኳርፈው ፍቅረኛው የራቀችው አፍቃሪ  በናፍቆት የመታመሙን ስሜት በሙዚቃ ከነጸጸቱ የተረከበት:: አስከፍቷታል፤ ሰድቧትም  ሊሆን ይችላል:: ትንሽ ከፊቱ ራቅ ስትል ግን  ዋጋዋን አይቷል፤ የእሷ መራቅ በሕይወቱ ውስጥ ምን እንዳጎደለበት አውቋል፤ ተጸጽቷልም:: “ልይሽ ሆዴ አልቻለም” ብሎም ሲጠራት ትታዘበኛለች፣ ሰው ምን ይለኛል አላለም:: ከምን ይሉኝ እና ምን ትለኝ በጸዳ የልብ ሰላም በመሻት ፍቅሩን ይጠራታል፤ ሰላም ሰላም እንባባል ይላል::

“ልጠይቅሽ እስኪ እንባባል ሰላም ሰላም

ሰላም ሰላም አካል ያማልዳል

ሰላም ሚወድ ሰላምን ይወልዳል

መቀራርብ ለሁሉም ይሆናል

ሰላም ሰላም ናፍቋል የኔው አካል

በማለት የተለየችውን ፍቅረኛውን    ምንም እንኳን የሐሰት ወሬ ተናፍሶ ቢጣሉም እሱ ጥፋቱን አምኖ በመሙዚቃው ሰላምን ፍለጋ ይቅርታን ይጠይቃል::  “የበደለም አምኖ ይካስ ወይ ከእኔ ወይ ከአንቺው” እያለ ለእርቅ ዝግጁ መሆኑን ይነግራታል:: እሷም ወደ እሱ ለመመለስ ልቧ ይራራል:: ቤታቸው ከግጭት ወደ ፍቅር ይሻገራል::

“ደገፍገፍ እናርገው እኛ ዋልታችን ይቃና

ደግመን እናድሰው ባክሽ ፍቅርን እንደገና”

አርስቶትል እንደሚለው ጦርነቱን የማሸነፍ ጉዳይ አይደለም፤ ሰላምን ማስፈን እንጂ። ባለበት የሚቀጥል ነገር የለምና ፤የግጭት ወቅት ገንዘብ፣ ሕይወት፣ ዕድሜ እና ስነልቦናን ሰውቶ  ያልፋል።  ችግሩ በተለይ በሀገራችን እንደሚታዩ የርስ በርስ ግጭቶች ዓይነት ሲሆንማ  “እጄን በእጄ ቆረጥሁት” በሚያስብል  ጸጸት ደንዳናው ጉልበታችን ሟሽሾ ለድርድር ሰላምን ፍለጋ ወንበር ስበን፤ ሽማግሌ መርጠን፤ ሐሳቦቻችንን ለይተን መቀመጣችን አይቀርም። ለዚህ ነው ሰላም የሰው ልጅ ተፈጥሮው ነው  የሚባለው።

ከሰላም ውጪ በግጭት ውስጥ ማርፈድ፣ መዋል ቢቻልም እንኳን ማደር ከባድ ነው። ሰው እየገበሩ፣ ሐብት እያወደሙ፣ ተስፋ እያጡ፣ እየተሳቀቁ መኖር ለሰው ልጅ መራር ነገር ነው። የግጭት ግራዋው ሲመረው የሰው ልጅ እንትፍ ብሎ መትፋቱ አይቀርም። ቶማስ ፔን “ሰላምን እመርጣለሁ። ግጭት ቢኖር በእኔ ዕድሜ ይምጣ፤ ልጆቼ በሰላም ይኖራሉና” የሚለው ግጭት አንድ ትውልድ ላይ መቆም ያለበት በመሆኑ ነው። በተመሳሳይ አልበርት አንስታይን “ሰላምን በጉልበትህ አትጠብቀውም በመግባባት እንጂ” ሲል ይገልጻል። ምክክር የግጭት ማብረጃ መሳሪያነቱን ያሳያል።

ሐተታ ሰላሜን በዚህ አበቃሁ::

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here