እጽዋትን መሠረት ያደረጉ የስጋ አማራጮች፤ ከእንስሳት የሚገኝ ስጋን ከመመገብ በተሻለ በልብ እና በደም ቧንቧ ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን መቀነስ እንደሚያስችል ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::
በካናዳ በልብ እና የደም ስር ላይ አተኩሮ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለንባብ በሚያበቃው ህትመት ከእንስሳት የሚገኝ ስጋን፣ እጽዋትን መሠረት ባደረጉ አማራጭ ምግብ መተካት፤ የልብና የደም ቧንቧ በሽታ ስጋትን ሊያሻሽል፣ የኮሊስትሮል መጠንን ሊቀንስ እንደሚችል ተጠቁሟል::
ተመራማሪዎቹ አክለውም እጽዋትን መሠረት ያደረጉ የስጋ አማራጮችን አትክልትና ቅጠላቅጠሎች፣ ጥራጥሬዎች ሲቀነባበሩ አሉታዊ ተጽእኖ ይፈጥራሉ የሚል ስጋት ቢያሳድርም ስጋን መመገብ ከሚያስከትለው ችግር እንደማይበልጥ ነው ያሰመሩበት::
በካናዳ አትክልትና ጥራጥሬን መሠረት ያደረገ ምግብ የመመገብ ፍላጐት እየጨመረ መምጣቱን አረጋግጠዋል- ተመራማሪዎቹ:: ለዚህ ደግሞ ለህብረተሰቡ በየጤና ተቋማትና በብዙሀን መገናኛዎች የተሰጠው ትምህርት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ነው በባለሙያዎች የተብራራው::
በካናዳ በአብዛኛዎቹ ከተሞች አትክልትና ፍራፍሬ የያዘ “በርገር” የተጠበሰ የእንስሳት ስጋ ካለበት በርገር የበለጠ ተቀባይነት አግኝቷል፤ ተጠቃሚዎቹም ተበራክተዋል:: ይህ መሆኑ ደግሞ የደም ግፊት እና የኮሊስትሮል መጠንን ቀንሶ ነው የተገኘው – የተጠቃሚዎቹን የጤና ሁኔታ ከመዝገቡ ተቋማት::
ተመራማሪዎቹ እስከአሁን ባደረጉት ጥናትና ምርምር አትክልትና ጥራጥሬን መሠረት ያደረገ የስጋ ምትክ የሚያስገኘው ጠቀሜታ አብዛኛዎቹን አስማምቷል::
በማጠቃለያነት ለህትመት የበቃው ጥናታዊ ጽሑፍ ከፍተኛ አርታኢ በዌስተርን ዩኒቨርሲቲ የኒውሮሎጂ እና ክሊኒካል ፋርማኮሎጂ ፕሮፌሰር እና የሮባርትስ ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ዴቪድ ስፔንስ “ለልብና የደም ስር በሽታ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ስጋ እና የእንቁላል አስኳልን ጨምሮ ከመመገብ መገደብ አለባቸው:: ይህን ለማካካስ በእጽዋት ላይ የተመሰረቱ የስጋ ምትክን መመገብ ጠቃሚ ነው” ሲሉ ነው ያደማደሙት::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም