የኪሊማንጃሮ ብሔራዊ ፓርክ

0
156

የኪሊማንጃሮ ብሔራዊ ፓርክ በምስራቅ አፍሪካ በታንዛኒያ ሰሜናዊ ድንበር በኬኒያ አዋሳኝ ላይ ይገኛል:: የአፍሪካ ጣሪያ የሚል ስያሜ የተሰጠው የኪሊማንጆሮ ተራራ  የከፍታው ጣሪያ 5 ሺህ 895 ሜትር ተለክቷል:: የተራራው አናት በበረዶ የተሸፈነም ነው::

የኪሊማንጃሮ ብሔራዊ ፓርክ በጉብኝት መዳረሻነት በህትመት መተዋወቅ የጀመረው በ1973 እ.አ.አ ሲሆን በይፋ ለጐብኚዎች የተከፈተው ደግሞ በ1977 እ.አ.አ ነው:: ብሔራዊ ፓርኩ በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ጥበቃ ድርጅት በ1987 እ.አ.አ ለመመዝገብ በቅቷል::

የብሔራዊ ፓርኩ አጠቃላይ ስፋት 1,712 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል:: ወደ ፓርኩ ለመድረስ በተሽከርካሪ ወይም በአውሮፕላን መጓዝ የሚቻል ሲሆን የፓርኩ ዋና ጽ/ቤት ከሞሺ ከተማ 41 ኪሎ ሜትር ወይም ከኪሊማንጃሮ አውሮፕላን ማረፊያ 86 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል::

የኪሊማንጃሮ ብሔራዊ ፓርክ ሁለት የዝናብ ወቅቶች አጭሩ ጥቅምትና ሕዳር ሲሆን በተራራው ግርጌ ዝናብ በጣም የሚጥልበት እና የተራራው ጫፍ በበረዶ የሚሸፈንበት ከታኅሳስ እስከ መጋቢት ያሉት ወራት ናቸው::

ወደ ተራራው ጫፍ ለሚወጡ ጐብኚዎች ምቹ ወራት ከሰኔ እስከ መስከረም እንዲሁም ከታህሳስ እስከ መጋቢት ያሉት ናቸው:: ይህ ወቅት ሌቱ ቀዝቀዝ ብሎ ቀኑ ጥርት ያለ በመሆኑ ለጐብኚዎች የሚመከር ወቅት ነው:: ተዘዋውሮ በተራራው ዙሪያ ያሉ ድንቅ ተፈጥሯዊ አቀማመጥን ለመቃኘትም ያስችላል- የአየር ንብረቱ:: ከተራራው ግርጌ እስከ ጫፉ ለመድረስ ለጐብኚዎች አጠቃላይ ከአምስት እስከ ዘጠኝ ቀናትን ይወስዳል::

ብሔራዊ ፓርኩ አራት ቀጣናዎች ወይም ክልሎች አሉት:: በእያንዳንዱ የተለያዩ እፅዋት እና እንስሳትም ይገኙበታል::

የመጀመሪያው ሞንታና ደን /Montana frost zone/ በሚል ይታወቃል::

ይህ ከ1 ሺህ 800 ሜትር እስከ 3,000 ሜትር ከፍታ ያለው፣ ርጥበታማው ቀጣና ሲሆን 2000 ሚሊ ሜትር ዝናብ የሚያገኝ ነው:: በአጽዋት የተሸፈነ በአእዋፍ መገኛነቱ የተለየም ያደርገዋል::

በዚህ ቀጣና 1 ሺህ 200 የእጽዋት ዝርያዎች እንደሚገኙ በአብዛኛው እንደየወቅቱ የሚረግፉ የአበባ ዝርያዎች ደምቀው የሚታዩበት ነው:: ከዱር አራዊት ዝንጅሮ፣ ጐሽ፣ ዝሆን፣ ነብር ተበራክተው ይታያሉ::

ሁለተኛው ከፊል አልፓይን ክልል ሲሆን ከ3,000 ሜትር እስከ 4,000 ሜትር ከፍታ ያለውን የሚያካትት ነው:: በብዛት እስከ ሦስት ሜትር ቁመት የተለካ የጅብራ ተክል ተበራክቶ ይታይበታል::

ከአእዋፍት የአበባ ማር ለቃሚ ወፍ እና “ላሜር ጌር” ወይም ቅልጥም ሰባሪ መናኸሪያ ቀጣና ነው:: በዚህ ቀጣና 55 የተለያዩ የሳር ዝርያዎች ተመዝግበውበታል::

የመጨረሻው አርክቲክ ዞን ከ5,000 ሜትር ከፍታ በላይ ያለው ነው:: በዚሁም ክልል የዱር ውሻ የበረዶ ላይ ነብር በ1920 እ.አ.አ መኖራቸው ታውቆ ተመዝግበዋል::

ለንባባችን በመረጃ ምንጭነት ዲስከቨር አፍሪካ፣ታንዛኒያ ቱሪዝም እና ታንዛኒያ ፓርክ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here