የኮሪያዎቹ ታሪክ

0
216

ኮሪያ በሰሜን ምስራቃዊ የእስያ ጠረፍ ላይ የምትገኝ ባህረ ገብ ሀገር ናት። በኮሪያ ረጅም ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የያዘው አንዱ ጉዳይ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ  ነው።  ከሩሲያ በስተደቡብ ፣  ከቻይና በስተምስራቅ፣ እንዲሁም ከጃፓን ሰሜን ምእራብ በኩል ትገኛለች። በእነዚህ ጎረቤት ሀገራት ያሉ ክስተቶች በኮሪያ ላይ የራሳቸው ተፅእኖ ያላቸው ሲሆኑ ኮሪያም ከጎረቤቶቿ ጋር ባህላዊ እና ቴክኖሎጅያዊ እመርታዎችን በመጋራት እንደ ባህላዊ ድልድይ በመሆን ወሳኝ ሚና ትጫወታለች።

ቅድመ ታሪኳ እንደሚያስታውሰን ከአካባቢ ወደ አካባቢ የሚሰደዱ ሕዝብ የኮሪያን ባህረ ገብ በዋናው የእስያ ምድር እና በጃፓን መካከል እንደ   ድልድይ አድርገው ይጠቀሙባት ነበር። ቀደምት ሰፋሪዎቿ ምግብ በማደን እና ፍራፍሬ በመልቀም የሚተዳደሩ ከፊል ዘላን ሕዝብ ነበሩ።  የሰፈሩባቸው አካባቢዎችም በወንዞች አቅራቢያ በጠረፋማ ስፍራ ነበር።

በ1992 ቅድመ ዓለም እርሻ ላይ የተሰማሩ የድንጋይ ማጭድ የፈጠሩ የቴክኖሎጂ እውቀት ያላቸው ማህበረሰቦች መከሰት ጀመሩ። ቀደምት የቻይናውያን ሰነዶች በርካታ የጎሳ ተኮር መንግሥታት በማንቹሪያ እና በኮሪያ ባህረ ገብ አካባቢ ተመስርተው እንደነበር ይገልፃሉ። በኮሪያ ታሪክ ውስጥ የሦስት ስርዎ መንግሥታት ማስታወሻ ላይ ኢርዮን የተባሉ መነኩሴ እንደፃፉት ታንጉም የሚባል መሪ የመጀመሪያዋን የኮሪያ አስተዳደር ጥንታዊን የኮለን ሥረወ መንግስትን በ2325 ቅድመ ዓለም አቋቁሞ እንደነበር ፅፈዋል።

ቻይናውያን በምስራቅ እስያ የበላይነታቸውን እያጠናከሩ በነበረበት ወቅት ሰሜናዊውን ወሰናቸውን ለመጠበቅ በ207 ቅድመ ዓለም አካባቢ የታላቁን የቻይና ግንብ ገንብተው ነበር። በቻይናው የሀን ስርወ መንግሥት ወቅት ቻይናውያን በኮሪያ ባህረ ገብ ውስጥ ድንበር ጠባቂ ማህበረሰቦችን ለመገንባት ወታደሮቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ይልኩ ነበር። የአካባቢው ሕዝብ የቻይናን አገዛዝ ተከላክለው ነበር፣ ነገር ግን ቻይናውያኑ ማህበረሰቦች የተሻሻሉ ቴክኖሎጅዎችን እና የቻይናውያንን የስልጣኔ መገለጫዎችን አስተዋወቋቸው።

የኮሪያን ታሪክ ከስሩ ለመረዳት የሦስቱን ስርወ መንግሥታት ዘመን በወፍ በረር ቃኘት አድርጎ ማለፍ ይገባል።

በሦስቱ የኮሪያ ስርወ መንግሥታት ዘመን (ከቅድመ ዓለም 53 እስከ 668) በኮሪያ ልሳነ ምድር ሦስት ስርወ መንግሥታት ተነስተው ነበር። እነርሱም ኮግርዮ ፣ ፒየቼ እና ሲላ ይባላሉ። እነዚህም ጥብቅ ማህበራዊ አደረጃጀቶችን የሚጠቀሙ ወታደራዊ ስርወ መንግሥታት ነበሩ።

በእነዚህ ሦስት ስርወ መንግሥታት ዘመን የቡድሂዝም እምነት ኮሪያ የደረሰበት እና በመጨረሻም ከኮሪያ ወደ ጃፓን የተሻገረበት ታሪክ የተመዘገበበት ነው። በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የቡድሂስት ግሮቶ በሲላ መዲና አቅራቢያ በ743 ዓ.ዓ ላይ ተገንብቷል። ሲላ በየብስና በባህር ንግዷ የታወቀች ነበረች። በአንድ ወቅት የሲላ ነጋዴዎች በቻይና እና በጃፓን መካከል ያለውን የባህር መስመሮች የተቆጣጠሩበት ጊዜ ነው።

በቻይና የሱንግ ስርወ መንግሥት ስልጣን በያዘበት ወቅት፣ ሲላ በኮርያ ስርወ መንግሥት ተተካ (910 እስከ 1384) ። ይህም ወቅት የሸክላ ቁሳቁሶች የተፈጠሩበት ጊዜ ነበር።

በኮርያ ስርወ መንግሥት ወቅት በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ትሪፕቲያካ ኮሪያና በመባል የሚታወቀው የእንጨት ማተሚያ ቴክኖሎጂ የተፈጠሩበት ነው።

ጄኔራል ይ ሶንግ ግየ የመጨረሻውን ኮለን የሚባለውን ከ1384 እስከ 1902 ዓ.ም ድረስ የነገሰውን የኮሪያውያን ስርወ መንግሥት መስርቷል። ይህም ወቅት የቻይናው ሚንግ ስርወ መንግሥት ቻይናን የገዛበት ዘመን ነው። የኮሪያ መዲና ሴኡል የነበረችበት እና የከተማዋ የመጀመሪያ የሆነው ህንፃ የኮንፊሺያውያን ትውልድ መነሻ የሆነው የቾንግሚዮ ቅዱስ ስፍራ ነበር። ይህ የህንፃ ሁሉን አካታች  (ኮምፕሌክስ) ትልቁ የዓለም ሕንፃ የሚያካትት እና በዩኔስኮ የዓለም የቅርስ ዝርዝር ውስጥ የተካተተ ነው። በ1436 ዓ.ም ሀንጉል የሚባለው የኮሪያውያን የፊደል ስርዓት ተፈጥሯል። ይህም እስከዛሬ ጥቅም ላይ ውሎ የሚገኝ እና በምክንያታዊነቱ እና በቀላልነቱ ትልቅ ክብር ያገኘ ግኝት ነው። ኮሪያ መፃህፍትን ለማተም ከ1226 ዓ.ም ቀደም ብሎ ተንቀሳቃሽ የብረት ማተሚያ  በመስራት ቀዳሚ ናት፡፡ ይህም ዮሐንስ ጉተንበርግ በጀርመን መፅሐፍ ቅዱስን በተንቀሳቃሽ የብረት ማተሚያ  ካተመበት 200 ዓመታት በፊት ነበር።

በማንቹሪያ እና በኮሪያ ባህረገብ ላይ ሦስት ትላልቅ መንግሥታት እና በርካታ ትናንሽ መንግሥታት  ከአንደኛው ክፍለ ዘመን ቅድመ ዓለም ጀምሮ እየተዳመሩ በአራተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ወደ ሦስት ስርወ መንግሥታት አድገዋል። ሲላ፣ ጎግሪዮ እና ባአይክጂ ይባላሉ። ሳምጉክሳጊ ወይም የሦስቱ የኮሪያ ስርወ መንግሥታት ታሪክ የሚባለው ቀደምት ታሪካዊ ሰነድ እንደሚያስቀምጠው ሲላ ስርወ መንግሥት ከ49 ቅድመ ዓለም  ጎግሪዮ ስርወ መንግሥት ከ29 ቅድመ ዓለም እንዲሁም የቢያኤክጄ ስርወ መንግሥትን ደግሞ ከ18 ቅድመ ዓለም እንደሚጀምር ተገልጿል። ቡድሂዝም እና ኮንፊሽያኒዝም ከቻይና እና መካከለኛው እስያ በመጡ ሚስዮናውያን አማካይነት እስከ አራተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ባሉት ጊዜያት እንደገቡ ይነገራል። እነዚህ እምነቶች ጎሳ ተኮር መንግሥታትን ወደ ተማከለ ስርወ መንግሥታት በማሸጋገር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

እነዚህ ሦስት መንግሥታት እስከ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ሌሎችን እየዋጡ እና በባህረ ገቡ ላይ የበላይነት ለመቀዳጀት ተፋልመዋል።  የሦስቱ ስርወ መንግሥታት ተቀናቃኝ ስርወ መንግሥታትም ነበሩ፤  እነርሱም በሰሜን በኩል የባዮ ስርወ መንግሥት እና በደቡብ የጋያ ስርወ መንግሥት ነበሩ።

የጃፓን ወረራ እና ነፃነት

በቀጣናው ሀያል እና በጦርነት ብዙ የሚባልላት ጃፓን ጎረቤቶቿን የመውረር እንቅስቃሴ ጀምራ ነበር። ጃፓን በተለያዩ ጊዜያት ከሩሲያ እና ከቻይና ጋር ካደረገቻቸው ጦርነቶች በኋላ በ1902 ዓ.ም ኮሪያን ወርራ ቅኝ ያዘች እና በሀገሪቱ ላይ ጭካኔ የተሞላ ወታደራዊ አገዛዝ አስቀጠለች።

በ1800 ዎቹ ኮሪያ ባህታዊ መንግሥት ወይም ሀገር እስከመባል ደርሳ ነበር። ምክንያቱም ወደቦቿን ለንግድ እንድትከፍት ከምእራባውያን የሚደረግባትን ግፊት ተከላክላ በማስቀረት እራሷን ዝግ አድርጋ ስለነበር ነው። ይሁን እንጂ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ በጃፓን ወታደራዊ የመስፋፋት ወረራዎች ሰለባ ከመሆን አልዳነችም። በወቅቱ ሀይለኛ እና በጦርነት የተካነችው ጎረቤት ሀገር ጃፓን ከቻይና እንዲሁም ከሩሲያ ጋር ያደረገቻቸው ጦርነቶች  ለኮሪያ መጪውን ጊዜ አስጊ ያደረገ ነበር። እናም ከእነዚህ ጦርነቶች በኋላ በ1902 ዓ.ም ኮሪያ በጃፓን ቁጥጥር ስር ወደቀች። አስከፊው የጃፓን ቅኝ አገዛዝ ዘመን እስከ 1937 ዓ.ም ድረስ የዘለቀ ነበር። በዚህ ወቅት በኮሪያ ላይ አስከፊ የቅኝ አገዛዝ ስርአት ተጫነባቸው ሀገሪቱ በገጠማት የኢኮኖሚ ድቀት እና አሳዛኝ የባህል ቀውስ  ሕዝቡ በችግር ማቀቀ።

በአካዳሚ ኦፍ ኮሪያን ስተዲስ በታተመው ኮሪያ ኢን ዘ ወርልድ በተሰኘ መፅሃፍ ላይ እንደተገለፀው ኮሪያውያን ይህን ሕገ ወጥ የሀይል ወረራ እና ጨካኝ ምህረት የለሽ የጃፓንን አገዛዝን የመታገል እንቅስቃሴ አደረጉ። የመከላከል እንቅስቃሴው በአንደኛው የዓለም ጦርነት እና ብሔራዊ የራስን እድል በራስ መወሰን በሚለው የዊድሮ ዊልሰን መርሆ በታወጀበት ወቅት እና በእስያ ባሉ ቅኝ ግዛቶች ውስጥ እያደገ በመጣው የብሔርተኝነት ትግል ተፅእኖ ያለበት ነበር።

ይቀጥላል….

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here