ባሕር ዳር ታዬ

0
161

የትውልድ ቦታቸው በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ ነው። የውልደት ዘመናቸውም ሰኔ 7 ቀን 1933 ዓ.ም ነው። ለቤተሰባቸው ታዛዥ እና ተወዳጅ ነበሩ፤ በዚህም “ወርቁ” በሚል ቅጽል ስም ይታወቃሉ:: በልጅነታቸው ፈጣን፣ ንቁ እና አዳዲስ ነገሮችን በመሞከር የሚታወቁት አቶ ታዬ ሞላ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በማንሳት በዚህ ሳምንት የዕውቀት ጎዳና አምድ ልናመሰግናቸው ወደናል::

ለትምህርት ልዩ ትኩረት ይሰጡ የነበሩት አባታቸው፣ የዛሬው አቶ ታዬ አራት ዓመት እንደሆናቸው የቤተክህነት ትምህርት እንዲከታተሉ አድርገዋቸዋል። ፊደል ከመቁጠር ጀምሮ ውዳሴ ማርያም፣ ዜማ፣ ዳዊት እና ግብረ ዲቁና እንደተማሩ የሕይወት ጉዞዬ በሚለው  የግለ ታሪክ መጽሐፋቸው አስፍረዋል::

አዳዲስ ነገሮችን በማወቅ ጉጉታቸው የሚታወቁት ባለ ታሪካችን ከአብነት ትምህርት በተጨማሪ አማረኛን አቀላጥፎ ለመናገር እና ለመጻፍ መደበኛ ትምህርት ለመማር ወሰኑ። የቤተክህነት መምህራቸው ከአካባቢያቸው መልቀቃቸው እና በወቅቱ በአቅራቢያቸው የመደበኛ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ከአባታቸው ተደብቀው ግንቦት 1 ቀን 1954 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ አመሩ። አዲስ አበባም የቤተክህነት ትምህርታቸውን በማስቀጠል አማርኛ የመጻፍ ፍላጎታቸውን እንዳሳኩ በ2016 ዓ.ም በጻፉት የግለ ታሪክ መጽሐፋቸው አስታውቀዋል::

የማንበብ እና የመጻፍ ፍላጎታቸውን እንዳሳኩ በ1955 ዓ.ም የልደት በዓልን ወደ ትውልድ ቀያቸው ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማክበር ሲያስቡ ለልብስ እና ለመጓጓዣ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት የቀን ሥራ መሥራትን ብቸኛ አማራጫቸው አደረጉ። የቀን ሥራ እየሠሩ የሚያገኙት ገንዘብ እንዳይጠፋባቸው ለአንድ ሰው በአደራ እየሰጡ ይቆጥቡ ነበር። ሥራ የሚሠሩበት ድርጅት በውኃ እጥረት ምክንያት ለጊዜው ሥራውን ሲያቆም ከባለ አደራው ገንዘባቸውን ተቀብለው ወደ ቀያቸው ለመመለስ አሰቡ:: ባላደራው ግን ገንዘባቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን እንደቀረ ግለ ታሪካቸው ያትታል:: በኋላም በወቅቱ በአዲስ አበባ ተማሪ የነበረውን አጎታቸውን እንዳገኙ እና እሱም ወደ ትውልድ ቀያቸው እንዲመለሱ እንደነገራቸው ያስታውሳሉ::

ጥቅምት 5 ቀን 1955 ዓ.ም የያኔው ታዳጊ የዛሬው አቶ ታዬ የስኬት ጉዞ ጅማሮ ሆኖ ይነሳል። ነገሩ እንዲህ ነው፣ የአቶ ታዬ የአጎት ልጅ (ድረስ) ከጅማ ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ። ድረስ እያሉ የሚጠሩት ይኸው የአጎታቸው ልጅ መተዳደሪያው መጽሐፍ ሽያጭ ነው። ይህ ግለሰብ ወዲያው እንደተገናኙ አቶ ታዬ በወቅቱ ሥራ እንዴት መጀመር እንዳለባቸው አማክሯቸዋል። በዚህ ወቅት በአንድ ብር ከ50 ሳንቲም ስድስት የቀን መቁጠሪያ በመግዛት እያዞሩ መሸጥ እንደጀመሩ ግለ ታሪካቸው ያስረዳል። ከሽያጩ የሚያገኙትን ገቢ በአግባቡ በመቆጠብ ከቀያቸው እንዲወጡ ያስገደዳቸውን መደበኛ የቀለም ትምህርት ጀመሩ። ቀን ትምህርታቸውን በመከታተል ማታ የቀን መቁጠሪያ ሥራቸውን አስቀጥለዋል። በኋላም የልብ ወለድ መጻሕፍት ወደ መሸጥ እንደተሸጋገሩ ግለ ታሪካቸው ያስረዳል። ሰኔ 10 ቀን 1956 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የመጻሕፍት አዟሪ ፍቃድ በማውጣት ሥራቸውን ሕጋዊ በማድረግ የንግዱን ዓለም በይፋ ተቀላቀሉ።

የመጻሕፍት ሽያጭ ሥራቸውን በማጠናከር ውጤታማ ለመሆን የጀመሩትን መደበኛ ትምህርት አምስተኛ ክፍል ላይ ለማቆም እንደተገደዱ በግለ ታሪካቸው ላይ አስፍረዋል:: በአዲስ አበባ ላይ ተዟዙሮ በመሸጥ ላይ ተወስኖ የነበረውን የመጻሕፍት ሽያጭ በክልል ከተሞች አስፋፉ:: ናዝሬት፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ጅጅጋ፣ ደሴ፣ መቀሌ፣ አስመራ እና ምጽዋ ድረስ የመጻሕፍት ሽያጭ ያከናውኑ ነበር።

በ1957 ዓ.ም ተራው የጎጃም እና የጎንደር ሆነ። መዳረሻቸውንም ባሕር ዳር አደረጉ። አቶ ታዬ “የሕይወት ጉዞዬ” ብለው በከተቡት የግለ ታሪክ መጽሐፋቸው በወቅቱ ባሕር ዳር በጣም ትንሽ ከተማ ነበረች። በወቅቱ ጥቂት ቤቶች የነበሩት በአሁኑ ወቅት ቀበሌ አራት እና አምስት በሚባሉ ቀበሌዎች እንደነበርም አስታውሰዋል። በያኔው ዘመን የተሻለ የሚባለው ሆቴል አባ አረጋ እንደሆነ እና ማረፊያቸውንም እዚሁ እንዳደረጉ ያስታውሳሉ። በወቅቱ ከአዲስ አበባ ይዘዋቸው የመጡትን መጻሕፍት በሆቴሎች፣ በትምህርት ቤቶች እና በተለያዩ ቦታዎች በማዞር ሽያጭ እንደጀመሩ አስታውሰዋል። በወቅቱ የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ የማንበብ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን እንደተረዱ እና የመጻሕፍት ሽያጫቸውን አጠናክረው እንዳስቀጠሉ ግለ ታሪካቸው ያስረዳል። ይሁን እንጂ ለአልጋ የሚከፍሉት ዋጋ ከሌሎች ከተሞች አንጻር ሲታይ ውድ መሆኑ አትራፊነታቸውን ሊገዳደረው እንደሚችል በመረዳታቸው አነስተኛ ቤት (ኪዮስክ) ተከራይተው መሥራት ጀመሩ:: ይህ ውሳኔያቸው ነው እንግዲህ ባሕር ዳርን ቋሚ መኖሪያቸው እንዲያደርጉ ያስገደዳቸው። የባሕር ዳር መታወቂያ እና የንግድ ፈቃድ በማውጣት ሥራቸውን አስፍተው ቀጠሉ። ከልብ ወለድ መጻሕፍት በተጨማሪ፣ የቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ደብተር እና ስክርቢቶ መሸጥ እንደጀመሩ አስታውቀዋል።

የቤት ኪራይ ዋጋ በየጊዜው መጨመር እና በተለያዩ ምክንያቶች በየጊዜው የተከራዩትን የሥራ ቤት እንዲለቁ መደረጋቸው በ1971 ዓ.ም የራሳቸውን ቦታ ገዝተው ቤት በመሥራት “ታየ ሞላ የመጻሕፍት መደብር” ወደሚል አሸጋገሩት:: የሥራ እንቅስቃሴያቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ በራሳቸው ቤት መሥራት ከጀመሩ በኋላ ለመሥሪያ ቤቶች፣ ለተማሪዎች፣ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሌሎች ድርጅቶች አስፈላጊ መሳሪያዎችን ማቅረብ ጀመሩ። ይህ የሥራ ዘርፍ በወቅቱ ብቸኛ ስለነበር መደብሩን ወደ ጽሕፈት መሳሪያዎች፣ የጽዳት እቃዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች አቅራቢ ወደሚል እንዳሳደጉት በግለ ታሪካቸው ገልጸዋል። በወቅቱ ተማሪዎች ከእርሳቸው ገዝተው በመማር ለቁም ነገር መብቃታቸው፣ የዘርፉ ሥራ በከተማዋ እንዲነቃቃ እና እዲስፋፋ ግምባር ቀደም መሆናቸውን ሲያስታውሱ ልዩ ስሜት እንደሚሰማቸው በግለ ታሪካቸው ላይ አስፍረዋል።

ትውልድ በማነጽ ሂደት ያደርጉት የነበረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በግለ ታሪካቸው ላይ የሰፈረው ጽሑፍ እንደሚያስረዳው፣ በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙት የጣና ሀይቅ እና የአፄ ሰርጸ ድንግል ትምህርት ቤቶች የሚፈልጉትን የትምህርት መገልገያ ለማሟላት በጀት ፈተና በሚሆንባቸው ወቅት በጀት ሲኖራቸው እንዲክፍሉ በማድረግ ከፍተኛ አበርክቶ ተወጥተዋል።

በአጠቃላይ አቶ ታዬ ሞላ በመንፈሳዊ እና ማኅበራዊ የልማት ተሳትፎ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ቤተ ክርስቲያናት እና ገዳማት የሚፈልጉትን ለማሟላት የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ፣ በግንባታ  እና በሌሎች ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ነዋሪው ከእርሳቸው የሚፈልገውን ሁሉ በደስታ በማድረግ የሚታወቁ ግለሰብ ናቸው።

አቶ ታዬ በ2012 ዓ.ም በድንገተኛ አደጋ ሕይወቱን ያጣውን ልጃቸውን ጨምሮ 11 ልጆች እንደወለዱ የአቶ ታዬ ሦስተኛ ልጅ የሆኑት ወይዘሮ ፋሲካ ታዬ ገልጸዋል:: በአሁኑ ወቅት በሕይወት የሚገኙት አሥር ልጆች በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሠማርተው በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል:: ሁሉም ልጆች ከአባታቸው ጠንካራነትን፣ በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ መሆንን፣ ሰው አክባሪነትን፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን መደገፍን፣ በማኅበራዊ እና የልማት ሥራዎች ንቁ ተሳታፊ መሆንን እንደተማሩ ተናግረዋል::

“የሕይወት ጉዞዬ” የተሰኘውን መጽሐፍ የገመገሙት ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን አቶ ታዬ ሞላ ምግበ አዕምሮ የሆኑትን መጻሕፍት እና ንዋያተ ቅድሳት በባሕር ዳር ከተማ ለሚገኙ ቤተ ክርሲቲያናት፣ ገዳማት እና ካቴድራሎች በማቅረብ ከተማዋን ከብዙ ደጋግ ሰዎች ጋር እንዳስተዋወቋት ጽፈዋል። ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ለሚገኙ የመጻሕፍት መደብሮች መሠረታቸው አቶ ታዬ መሆናቸውንም አንስተዋል። አንባቢ ትውልድ እንዲፈጠር ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋናን ችረዋል። አቶ ታዬ የሥራ ፍቅርን፣ የልማት ተነሳሽነትን፣ ትህትናን፣ አርዓያ መሆንን… ለሕዝቡ የሚያስተምሩ ታላቅ አባት ስለመሆናቸውም በመጽሐፉ ላይ ጽፈው ይገኛሉ።

በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሚሰሩት እና በቅርብ የሚያውቋቸው አቶ ምንተስኖት ዳምጤ በበኩላቸው ባለታሪኩ መረጃ በአግባቡ ተሰንዶ መያዝ እንዳለበት በጽኑ የሚያምኑ ሰው እንደሆኑ ተናግረዋል። ለዚህ አብነቶችን መመልከት ይቻላል። አቶ ታዬ ወደ ባሕር ዳር መጥተው ሥራ እንደጀመሩ ይከፍሉት የነበረው የግብር መጠን አራት ብር እንደነበር እና ለመጨረሻ ጊዜ በ2015 ዓ.ም የከፈሉት ግብር ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ እንደነበር ግለ ታሪካቸውን በሚያወሳው መጽሐፋቸው ጽፈዋል።  በያኔው ዘመን አንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ እንደነበር፣ እርሳቸውም በወቅቱ በባሕር ዳር ከተማ ከሚገኙ የንግድ ባንክ ደንበኞች መካከል ሦስት መቶኛ ሆነው የባንክ ሂሳብ መክፈታቸው መረጃን አደራጅተው ለመያዛቸው አስረጂ ነው።

እንደ አቶ ምንተስኖት ባለ ታሪካችን ጋዜጦችን እና የተለያዩ መጻሕፍትን እያዞሩ በመሸጥ ትውልዱ አንባቢ እንዲሆን፣ መረጃዎችን እና ማስታወቂያዎች በቀላሉ እንዲያገኝ ያደረጉ የዕውቀት አባት ስለመሆናቸው አንስተዋል። መጻሕፍትን በቅናሽ በመሸጥ፣ በማከራየት እና የማንበብ ፍላጎት ኖሯቸው የመግዛት አቅም ለሌላቸው ወገኖች መጻሕፍትን በነጻ በመስጠት ጉልህ አበርክቶ መጫወታቸውንም አስታውሰዋል። በያኔው ዘመን የባሕር ዳር እና አካባቢው ሕዝብ የትምህርት ቁሳቁስ ችግር ሆኖበት ከትምህርት ውጪ ሳይሆን ትምህርቱን አጠናቆ ሁሉም ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ የአቶ ታዬ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ትውልዱ መልካም ስብእናን ተላብሶ እንዲያድግ በመገሰጽ፣ ማንም ሥራ ሳይንቅ ከሠራ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚችል አርአያ የሆኑ ግለሰብ መሆናቸውንም  ገልጸዋል።

አቶ ታዬ ሞላ ለባሕር ዳር ከተማ ዕድገት እንዲሁም በትውልድ ስብእና ግንባታ ላይ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለሌሎችም በአርአያነት የሚጠቀስ በመሆኑ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የበኲር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አመስግኗቸዋል:: ዝግጅት ክፍላችንም ሆነ ድርጅታችን በአቶ ታዬ ሕልፈት የተሰማውን ሐዘን በመግለጽ ለቤተሶቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናቱን ይመኛል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here