ራስን የማሸነፍ ፋይዳ

0
218

‘ርግጥ ነው ሰዎች ስንባል በተፈጥሯችን ማሸነፍን እንጂ መሸነፍን አንሻም፤ ሽንፈት ውርደት መስሎ ስለሚታየን:: ይህን ስንል ግን ከመሸነፍ ይልቅ ማሸነፍን የመሻት ተፈጥሯዊ ባሕርያችን መጥፎ ነገር ነው ማለታችን እንዳልሆነ መገንዘብ ያሻል::

ሆኖም እዚህ ላይ የምንዘነጋው አንድ ቁም ነገር አለ፤ ሌሎችን ለማሸነፍ በቅድሚያ ራስን የማሸነፍን አስፈላጊነት መረዳት:: ራስን ለማሸነፍ ደግሞ ጣታችንን ቀስረን የሰዎችን ስህተት ለመንቀስ ከመነሳታችን በፊት እኛም ፍጹም እንዳልሆንን ተገንዝበን ወደ ራሳችን መመልከት፣ ተመልክተንም ስህተታችንን መለየት፣ ለይተንም ማረም ይጠበቅብናል::

ጣታችንን ወደ ሌሎች ከመቀሰራችን በፊት ወደ ራሳችን በመመልከት ድክመታችንን ለይተን ማረምን ከቻልን፣ በእኛ ድክመት የተነሳ የተጎዳ ወገን ካለም በሠለጠነ ሰው ወግ ዝቅ ብለን የተጎዳውን ሰው “ሳላውቅ በስህተት፣ እያወቅሁ በድፍረት ላደረስኩት በደል ይቅርታ እጠይቃለሁ!” በማለት በትህትና ይቅርታ ከጠየቅን፣ እንዳስፈላጊነቱም መካስ ባለብን ልክ ከካስን ማንም ከእኛ ጋር ትግል ገጥሞ ሳያሸንፈን ራሳችን ከራሳችን ጋር ዘክረን መክረን ራሳችንን በቅድሚያ  ድል ነሳን ወይም ራሳችንን ገዛን ማለት ነው::

ከራስ ጋር ዘክሮ መክሮ ስህተትን ቀድሞ ማረም  ደግሞ የታላቅ ብሎም የሠለጠነ ሰው መታወቂያ ነው:: ቀድመን ወደ ራስ መመልከትን፣ ተመልክቶም ስህተትን ወይም ድክመትን ወይም ጥፋትን ማረምን ለሰዎች ምሳሌ ሆነን አሳይተናልና በሰዎች ዘንድ ክብርን እና ተደማጭነትን እናገኛለን::  ከዚህ በኋላ እኛ ለሰዎች ምሳሌ ሆነን ስለታየንም የሌሎችን ስህተት ነቅሰን በማውጣት “ወዳጄ ብዙ ጠንካራ ጎኖች ቢኖሩህም፣ በጠንካራ ሥራዎችህ ብትታወቅም ጥንካሬዎችህን እንዲሁም መልካም ሥራዎችህን ሊያደበዝዝ ምናልባትም ሊያጨልም የሚችል ይህን መሰል ስህተት፣ ጥፋት ወይም ድክመት አለብህ፤ እባክህ አርመው!” ብንል ተሰሚነት ይኖረናል:: ብንናገርም ሆነ ከሰው ስህተት ብንፈልግ፣ ያንን ስህተት እንዲያርምም ብንመክር፣ ብንዘክር አንሳቀቅም:: አንገታችንን አቅንተን፣ ደረታችንን ነፍተን መናገር ስለምንችል፣ አርአያነት ከእኛ ጋር ስለሆነች ተሰሚነት በማግኘታችን በራስ የመተማመን ስሜታችን ከፍ ስለሚል ራሳችንን ቀድመን ድል እንደነሳነው ሁሉ ሌሎችን ማሳመን፣ አሳምነንም ከገቡበት ስህተት ወይም ድክመት ማውጣት ስለምንችል የሚያጣሉንን ችግሮች በቀላሉ ፈትተን በሰላም በፍቅር፣ በስኬት ጎዳና እጅ ለእጅ ተያይዘን አብረን እንጓዛለን::

ይህን ሁሉ አድርገን ምናልባት የሚሞግተን ቢመጣ እንኳን “ርግጥ ነው ብዙ ጠንካራ ጎኖች አሉህ፤ በጠንካራ ሥራዎችህም ትታወቃለህ:: ሆኖም ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም እና እኔ እንዳደረግሁት ወደ ራስህ ተመልከት፤ ተመልክተህም ጥንካሬዎችህን እና መልካም ሥራዎችህን ሊያደበዝዙ፣ ምናልባትም ሊያጨልሙ የሚችሉ ስህተቶችህን ወይም ድክመቶችህን አርም” በማለት ራሳችንን አብነት አድርገን በሠለጠነ ሰው ወግ በመነጋገር  ችግሮቻችንንም በመተማመን በጋራ ልንፈታ  እንችላለን::

ባንጻሩም ደካማ ጐናችንን ዐውቀንም ሆነ ሳናውቅ በመሸፋፈን፣ የራሳችን የሆነውን እና ልናርመው ግድ የሚለንን ድክመት ወይም ጥፋት ኅሊናችን ሳያጣው ወደ ሌሎች በመግፋት  ለሌሎች ጥንካሬ ዕውቅና በመንፈግ በመልካም ተግባሮቻቸው ላይ አመድ በመነስነስ አሸናፊ ሆነን ለመገኘት በነቢብም ሆነ በገቢር ትግል ስንጀምር ያኔ የውድቀታችን ወይም የተሸናፊነታችን መጀመሪያ ይሆናል::

የዚህ ምክንያቱ ደግሞ እኛ ከእኛ በተጻራሪነት  ቆሞ ሊያጠፋን ቆርጦ የተነሳ የመሰለንን ሰው በዚህ ደረጃ ስንፈርጀው እሱም የተጓዝንበትን መንገድ ያህል ምናልባትም ከዚያ በላይ ተጉዞ ይፈርጀናል፤ “እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ፤ ጥፋቱ ያንተ ነው!” በሚል ስንሞግተውም እሱም በተራው ድክመቱን ኅሊናው እየነገረውም እንኳን ቢሆን የተነሳንበት መንገድ የሾህ አጥር ስለሚሆንበት እሱም የሾህ አጥሩን ያጥርና “እኔ ጥፋት የለብኝም፤ ጥፋቱ የራስህ ነው!” በማለት ሽንጡን ገትሮ ይሞግተናል:: የሙግታችን መቋጫም መቃቃር ብሎም ፊት መዟዟር፣ ምናልባትም ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችላል::

በጥቅሉ ማንም ይሁን ማን የሚመልስልን የሰጠነውን ነው:: እንክርዳድ አስታቅፈን “እኛ እንክርዳድ ብናስታቅፍህም አንተ ስንዴ መልስልን!” ብንለው ዓለም የሰጥቶ መቀበል መድረክ ናትና “በጄ!” አይልም፤ ጣታችንን እየቀሰርንበት ጣትህን ሰብስብ ብንለውም ጣቱን  ከመቀሰር አይመለስም::  የቱንም ያህል መልካም ባሕርይ ቢኖረን፣ የቱንም ያህል ላገር ለወገን የሚጠቅም መልካም ነገር ብንሠራ መልካም ባሕርያችንም ሆነ ጠቃሚ ተግባራችን አይታየውም ወይም አይዋጥለትም:: በተደጋጋሚ ሲኆን እንደምናስተውለው መልካሙን ባሕርያችንን መጥፎ ገጽታ እያላበሰ፣ መልካም ሥራችንን እያንኳሰሰ ስለ እኛ መናገርን ልማድ ያደርገዋል::

ያሳለፍነውንም ሆነ እያሳለፍን ያለነውን  ዘመናችንን  ስንፈትሽ ከዚህ በላይ ያብራራነውን መልክ ይዞ እናገኘዋለን:: ድክመቶች ያሉብንን ያህል ለሀገር፣ ለወገን የሚጠቅሙ ብዙ መልካም ነገሮችን እየሠራን የመጣን መሆናችን ባይካድም ለዚህ መልካም ተግባራችን ዕውቅና በመስጠት፣ በመደናነቅ ፋንታ ዓይናችን የሚያየውን፣ ኅሊናችን የመዘገበውን ጥሩ ነገር እየደፈጠጥን እየተወነጃጀልን፣ ከመወነጃጀል አልፈንም የጋራ ሀብታችንን ስናጠፋ፣ ርስ በርሳችን ስንጠፋፋ ዓመታትን አሳልፈን ተቀብለናል::

“በዚህ ሂደት ማን አሸናፊ ሊሆን ይችላል?” ብለን በሰከነ መንፈስ ብንጠይቅ መልሱ “ማንም!” የሚል ይሆናል:: ከታሪክ እንደተማርነው፣ ደርሰንበትም እንዳስተዋልነው እውነትን ሳይዙ አሸናፊነት የለምና ድልን እንደናፈቅን የናፈቅናትን ድል ሳንመታ ወይም ሽንፈታችን ሳይታወጅ ርስ በርስ እየተጠፋፋን እንቀጥላለን::

እንደ ጥንቱ በፍቅር ተቃቅፈን፣ እየተደጋገፍን፣ እየተመካከርን ችግሮቻችን እየፈታን በለውጥ ጎዳና መራመድ     የሚገባን ያንዲት ሀገር ልጆች ነን:: ስለሆነም  እንደ አባቶቻችን ጀግንነታችን፣ ቀረርቶአችንም ሆነ ፉከራችን የሚያምረው ብንጣላም፣  ብንፋቀርም፣ ብናለማም ሆነ ብናጠፋ እቅፍ ድግፍ አድርጋ የያዘችንን  ውዷን ሀገራችንን ጦቢያን ሊወር፣ ሊደፍር፣ እኛን ልጆቿን ሊያስገብር፣ ሀብት ንብረቷን ሊመዘብር… ከሚመጣ የውጪ ወራሪ ኃይል ጋር ገጥመን ድል ስናደርግ እንጂ እኛ ያንዲት ሀገር ልጆች ርስ በርሳችን ገጥመን እየተጠፋፋን አቅማችን እየተቀነሰ  ሲሄድ አይደለምና ከገባንበት የጥፋት ጐዳና ፈጥነን መውጣት ወቅቱ የሚጠይቀን ግዴታችን ነው::

 

 

(ቦረቦር ዘዳር አገር)

በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ

በhttp:// www.ameco.et/Bekur

በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here