ሰላምን አጥብቆ የሚሻዉ…

0
145

ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲን የምትከተለው ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያጋጠማት ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ ድርቅ፣ የግብርና ግብዓት አቅርቦት እጥረት በወቅቱ ካለመቅረብ ጋር ተያይዘው በምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠሩ ነው፡፡ መፍትሄ ርቋቸው የቀጠሉ ግጭቶችም ሀገሪቱ በምግብ ራስን ለመቻል፣ የፋብሪካዎችን የጥሬ እቃ አቅርቦት ውስንነት በዘላቂነት ለመፍታት፣ ከምርት አቅርቦት ጋር ተገናኝቶ እየተፈጠረ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማስታገስ፣ የተትረፈረፉ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ችግሮችን ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት  እገደቡ መሆናቸውም ይታመናል፡፡

ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች ኢትዮጵያ ለእርሻ ምቹ ናቸው ብላ በለየቻቸው መሬቶቿ አልምታ የምግብ ዋስትናዋን በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንዳትገነባ፣ ይልቁንም ከ15 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታን እንዲሹ እንዳደረጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች ብቻ በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ላይ ያሳደሩት አሉታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ከ2015 ዓ.ም ሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ በአማራ ክልል የተፈጠረው እና ለአንድ ዓመት ያህል መቋጫ አጥቶ አሁንም ድረስ የቀጠለው ግጭት በዘርፉ ላይ ያደረሰውን ጉዳት ከመመልከት በፊት በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የደረሰውን ተጨባጭ ጉዳት እንደ መረጃ እንመልከት፡፡ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ጦርነቱ በርካታ የእርሻ መሬቶች ያለምርት እንዲከርሙ እና የተዘራው ሳይሰበሰብ የወፍ ቀለብ ሆኖ ቀርቷል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰሜኑ ጦርነት ባካለላቸው ዘጠኝ የአማራ ክልል ዞኖች  ሦስት ወራትን የፈጀ ጥናት አድርጓል። ጥናቱም በክልሉ ያሉ የግብርና ምርቶች፣ ቢሮዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ እና የእንስሳት ሀብት ልማት ኤጀንሲዎችን ዳስሷል::  የጥናት ውጤቱ  ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም ይፋ ሲደረግ ጦርነቱ በግብርና ዘርፉ ላይ 340 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ጉዳት ማድረሱ እንደተመላከተ የሪፖርተር ጋዜጣ የየካቲት 6 ቀን 2022 (እ.አ.አ) ዘገባ ያመላክታል፡፡

የሰሜኑ ጦርነት በሰላም ስምምነት ተጠናቆ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች ወደ አምራችነት እየተሸጋገሩ ቢሆንም ግጭቶች ግን አሁንም ቀጥለዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ዕድገቷን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት አደናቃፊ ሆኖባታል፡፡

የግጭቶች እልባት አለማግኘት በግብርና ዘርፉ ላይ ጉዳት በማድረስ እንዴት ሀገራዊ ዕድገትን ሊፈታተን ይችላል የሚለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡ ግጭት በባህሪው መንገዶች እንዲዘጉ፣ ክፍትም ቢሆን ደኅንነቱ የተጠበቀ ስለማይሆን የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ ተጓጉዘው ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዳይሆኑ ያደርጋል፡፡ አርሶ አደሩን ጨምሮ ሌላው ማኅበረሰብ ከቀየው እንዲፈናቀል በማድረግ ከምርት ውጭ ሆኖ እንዲከርም ያደርገዋል፡፡ የተመረተው ምርት በወቅቱ አይሰበሰብም፡፡ ይህም የምርት ብክነትን በማስከተል ምርታማነት እንዲቀንስ ምክንያት ይሆናል፡፡

የግጭቶች በግብርና ሥራዎች ላይ የሚያሳድሩት ጫናዎች አምራች እጆች ለልመና እንዲዘረጉ እና አስቸኳይ የምግብ ርዳታ እንዲሹም ያደርጋቸዋል፡፡ በግጭት እና በተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እጃቸውን ለእርዳታ የዘረጉ ወገኖችን  ለመደገፍ የምርት እጥረት ታክሎበት ሌላ ፈተና በመሆን ተጨማሪ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን ያስነሳል፤ ይህም ሀገራት ለመረጋጋት የሚያደርጉት ጥረት ግቡን እንዳያሳካ ያደርገዋል፡፡

ከባለፈው ዓመት (2015 ዓ.ም) ሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት በክልሉ በርካታ ጉዳቶችን እንዳደረሰ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በተለያዩ ጊዜያት ተናግረዋል፡፡ የልማት ሥራዎች በወቅቱ እንዳይጠናቀቁ፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲስተጓጎሉ፣ የግብርና ሥራዎች በተጠናከረ መንገድ እንዳይቀጥሉ እክል መፍጠሩ ተመላክቷል፡፡

መንግሥት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ሙሉ ትኩረቱን በልማት እና በመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ለማድረግ የተለያዩ የሠላም ጥረቶችን ከማድረግ ጎን ለጎን የግብርና ሥራውን ሳይስተጓጎል ለማስቀጠል በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡ የክልሉ ግብርና ቢሮ ለ2016/17 የምርት ዘመን አምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በዘር በመሸፈን 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ በመፈጸም ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ዕቅድ ይዞ እየተሠራ ነው፡፡ በአሲዳማነት የተጠቃውን መሬት ማከምም ክልሉ ባለፉት ዓመታት ያጣውን ምርታማነት ለመመለስ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ ከቢሮው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

ይሁን እንጂ በክልሉ ተፈጥሮ አንድ ዓመትን ያስቆጠረው ግጭት የግብርና ግብዓትን ከጅቡቲ ወደብ ወደ ሀገር ውስጥ ከማስገባት ጀምሮ ለአርሶ አደሩ በወቅቱ እና በበቂ መጠን ለማሰራጨት ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡ በኲር ጋዜጣም ግጭቶች በግብርና ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደር የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ፣ ሀገራዊ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገቱም በሚፈለገው ልክ እንዳይሄድ ሊያደርጉ እንደሚችሉ በመጠቆም መፍት አመላካች ዘገባዎችን ስትዘግብ ቆይታለች፡፡

በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ነዋሪዉ አርሶ አደር ፍሬው ንብረቴ በዘንድሮው ዓመት ሁለት ነጥብ አምስት ሄክታር ማሳን በበቆሎ፣ በጤፍ፣ በስንዴ እና በገብስ ለመሸፈን እየተሯሯጡ መሆናቸውን ለበኲር ጋዜጣ በስልክ ተናግረዋል:: በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ግን በምርታማነታቸው ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ስጋታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ግጭቱ በግብዓት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩ በዓመቱ የሚያስፈልጋቸውን የአፈር ማዳበሪያ ለማግኜት ስጋት ውስጥ እንዳስገባቸው የባለፈውን ዓመት ችግር መነሻ አድርገው ተናግረዋል፤ አቅርቦቱም አርሶ አደሩ በሚገኝበት ቀበሌ ድረስ አለመሆኑ ለተጨማሪ ወጪ እና የጉልበት ኪሳራ እየዳረጋቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር መፍትሔ አለማግኘት ግብዓት ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እና ወደ አርሶ አደሩ ለማሰራጨት የሚደረገውን ጥረት እየፈተነው ነው መባሉ ደግሞ በዓመቱ ለማግኘት የፈለጉትን ሁሉንም የአፈር ማዳበሪያ ለማግኘት ስጋት እንደሆነባቸው ጭምር ገልጸዋል፡፡ ክረምቱ ከገባ በኋላ ደግሞ ተሽከርካሪዎች በጭቃ ስለሚያዙ  ግብዓት በወቅቱ እንዳይደርስ ሊከለክል ይችላል የሚል ተጨማሪ ስጋት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡ ሁሉም ወገን ለሰላም ልዩ ትኩረት በመሥጠት ሰላምን ማስፈን እንደሚገባ ያነሱት አርሶ አደሩ፣ ይህ ከሆነ ደግሞ የግብዓት አቅርቦቱ በፍጥነት ተደራሽ ይሆንልናል ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል::

የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ግብዓት በማጓጓዝ ሂደት ላይ አሳድሮት የነበረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደነበር በቅርቡ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብዓት አቅርቦት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሙሽራ ሲሳይ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ ባለፈው ዓመት ያጋጠመው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት እና መዘግየት ዘንድሮ እንዳይደገም ግዥው ቀድሞ መፈጸሙን አስታውቀዋል፡፡

የጸጥታ ችግሩ ጭነት የያዙ ተሽከርካሪዎች ከአንድ ወር በላይ መንገድ ላይ እንዲቆዩ አድርጓል፡፡ ያም ሆኖ የአፈር ማዳበሪያ የአርሶ አደሩ ስጋት እንዳይሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ሥብሠባ ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ ተገኝተው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ኢትዮጵያ 15 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እንደምታስገባ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከ13 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ እየተሠራጨ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ሁለት ሚሊዮን የሚሆው ወደ ጅቡቲ ወደብ እየተጓጓዘ ይገኛል፤ “ካለፈው ዓመት አንጻር አስደናቂ ሥራ ተሰርቷል፤ ነገር ግን አሁንም ፍጹም ሥራ አይደለም” ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ግጭቱ በክልሉ ሕዝብ ምጣኔ ሐብታዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ እያሳደረ ካለው አሉታዊ ተጽዕኖ ለመውጣት መንግሥት ልዩነቶችን በንግግር፣ ውይይት እና በድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ለዚህም ሁለቱን ወገኖች የሚያቀራርብ የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ተቋቁሞ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ ካውንስሉም ሁለቱም ወገኖች ሰላማዊ አማራጮችን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ግጭቶ እልባት ሲገኙ ሀገር ልማት ላይ ትኩረቷን ታደርጋለች፤ ዕድገቷንም ታረጋግጣለች፤ ዜጎች በኢትዮጵያ የትኛውም አካባቢ ኢትዮጵያዊ አርማን ተላብሰው ሐብት ማፍራት ይችላሉ፡፡  ኢትዮጵያ ተፈናቃይ የሌለባት፣ የዕርዳታ ድርጅቶችም የሀገሪቱ ዜጎች ለሀገራዊ ዕድገት የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ እንጂ የዕለት ደራሽ ምግብ ለማቅረብ ኢትዮጵያን ተመራጭ አያደርጉም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል በርካታ ሀገራት እንደደገፏት ገልጸው ከጥቂት ዓመታት በኋላ እርዳታ የምንፈልገው እህል ሳይሆን ማሽን እንደሚሆን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here