ባለፈው ሳምንት እትማችን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሥራት አጸደ ወይን የዩኒቨርሲቲውን የምርምር ደረጃ እና የማኅበረሰብ ግልጋሎት በተመለከተ ያካፈሉንን ሀሳብ ማስነበባችን እና ቀሪውን ክፍል በዚህ እትም ልናስነብባችሁ በቀጠሮ መለየታችን ይታወሳል፡፡ እነሆ በቀጠሯችን መሠረትም ዩኒቨርሲቲውን ራስ ገዝ ማድረግን እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችን በተመለከተ ፕሬዝዳንቱ የሰጡንን ሀሳብ ይዘን ቀርበናል፡፡
መልካም ንባብ!
ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀዳሚውን ጉዞ ጀምሯል፤ ጎንደር ዩኒቨርሲቲስ ራስ ገዝ ለመሆን ምን አስቧል?
ዩኒቨርሲቲያችን በቀጣይ ራስ ገዝ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተቋማት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የራስ ገዝነት ሃሳብ ቀደም ሲል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ በሚጠራበት በንጉሡ ጊዜም የነበረ ነው፡፡ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በፊት ትልቅ ተቋማዊ ነጻነት ነበረው፡፡ ነገር ግን ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ዩኒቨርሲቲዎች ነጻነታቸው ተነፍጎ ቆይቷል፡፡ ለአብነት ነጻነት ከተነፈጉባቸው አንዱ የአካዳሚክ ዘርፍ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸውን ሥርዓተ ትምህርት ቀርጸው በማስተማር፣ መምህራንን ራሳቸው በመቅጠር እና በማሰናበት፣ ፋይናንስን በራስ መንገድ በማንቀሳቀስ ረገድ እና በሌሎች ማዕከላዊ ሆነው ዩኒቨርሲቲዎች መብቶቻቸው ተገድበው ቆይተዋል፡፡
መንግሥት አሁን የጀመረው ቀደም ሲል የነበረውን የዩኒቨርሲቲዎችን ተቋማዊ ነጻነት የመመለስ ሥራ ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች መፍለቂያ ነው፤ እኛን ሁሉ ያስተማረ ቀዳሚ ተቋም በመሆኑ በመጀመሪያ ወደ ራስ ገዝነት ማምራቱ ተገቢ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት በመግባቱም ብዙ ተሞክሮዎችን እያገኘንበት ነው፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ከራስ ገዝነት ጋር የተያያዙ ሰነዶችን በማዘጋጀት ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ አጋር አካላትም ትልቅ እገዛ እየሰጡ ነው፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ ኢምባሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሌሎች ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ የሆኑበትን ተሞክሮ ታሳቢ በማድረግ እገዛ እያደረገልን ይገኛል፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን ብዙ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል፡፡ ለአብነት ራስ ገዝ መሆን ጥቅም አለው ወይስ ጉዳት? የሚለውን የዳሰሳ ጥናት አድርገናል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ካለው ማኅበረሰብ ከ70 በመቶ በላይ ራስ ገዝ ብንሆን ከዚህ የተሻለ ደረጃ እንደርሳለን የሚል ምላሽ አግኝተናል፡፡ ጥናቱ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ ፍላጎት ያየንበት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ስለ ራስ ገዝነት መረጃ መለዋወጥ እና ግንዛቤ መፍጠር የቻልንበት ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ዘጠኝ የሚሆኑ ቡድኖች አቋቁመን ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስፈልጉ ደንቦችን ከተቋማችን አኳያ አዘጋጅተን በቅርቡ ለትምህርት ሚኒስቴር ልናስገባ ነው፡፡ ቡድኖቹ በአካዳሚክ፣ በምርምር፣ በማኅበረሰብ ግልጋሎት፣ በሆስፒታለል አገልግሎት፣ በሀገር በቀል ዕውቀት እና በመሳሰሉት የተቋቋሙ ናቸው፡፡ ደንቡ በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ውይይት ተደርጎበታል፤ በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ጸድቋል፤ በዩኒቨርሲቲው አመራር ቦርድ አጽድቀን ለትምህርት ሚኒስቴር ምናስገባው ይሆናል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ የመሆን የሽግግር መመሪያ ረቂቁ ደርሶናል፤ ከዚህ መመሪያ አንጻር የት ላይ ነው ያለነው? የሚለውን በአቋቋምነው ቡድን እያስጠናን እንገመግማለን፡፡ ይህን ካደረግን በኋላ የምንሠራቸው ብዙ ተግባራት አሉ፡፡ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ለመሆን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ማጸደቅ ይሆናል፡፡ ይህ ከጸደቀ በኋላ ስትራቴጂክ ፕላን እናዘጋጃለን፤ የተለያዩ መመሪያዎችን እናወጣለን፤ መዋቅሩን እንደገና እናደራጃለን፤ የመሠረተ ልማት ጉድለቶች ይሟላሉ፤ ራስ ገዝ ከሆንም በኋላ የማስተዋወቅ ሥራ ይከወናል፤ ተማሪዎቻችን መርጠውን እንዲመጡ እንሠራለን፡፡ ሂደቱ ፈታኝ ሊሆን ይችላል፤ ዩኒቨርሲቲው እነዚህን ፈታኝ ሂደቶች ለማለፍ በርትቶ መሥራት ይጠበቅበታል፤ ለዛ ዝግጁ ነን፡፡
ከፋይናንስ አኳያ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ምን እየሠራችሁ ነው?
ከፋይናንስ አኳያ ብዙ የጀማመርናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ በተለይ የዩኒቨርሲቲውን ኢንተርፕራይዝ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ አጸድቀን ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ ኢንተርፕራይዙ ወደ 10 የሚሆኑ ዘርፎች አሉት፤ የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡ ሁሉም ኢንተርፕራይዞች ከመማር ማስተማር ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በአንድ መልኩ ሀብት በማመንጨት ዩኒቨርሲቲው የበጀት እጥረቱን ይሸፍናሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሥራ እድል ይፈጥራሉ፤ ሰራተኛውን ደግሞ ኮብልሎ እንዳይሄድ ማቆያም ናቸው፡፡ የምንሰጣቸው ምርት እና አገልግሎቶች ደግሞ ለአካባቢው ማኅበረሰብ በጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ነው፡፡
እነዚህ የጀመርናቸው ሥራዎች የራስ ገዝ የመሆን ሂደት አካላት ናቸው፡፡ ራስን በገንዘብ ማጠናከር እና ከመንግሥት የምናገኘውን ድጎማ ሙሉ በሙሉ ማቆም ባይቻልም ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥራዎቻችንን እያጠናከርን የመንግሥትን ድርሻ ለመቀነስ ብሎም ለማቆም ጥረት ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ለምሳሌ ዩኒቨርሲቲያችን የአይሲቲ ማማከር አገልግሎትን ብንወስድ እንደማንኛውም የንግድ ተቋም ባለሙያዎቻችን ተወዳድረው ውል ይይዛሉ ያማክራሉ፤ በምህንድስናውም ደረጃ አንድ የማማከር አገልግሎት እንሰጣለን፤ ባለሙያዎቻችን ልምዳቸውን እያዳበሩ ነው። ገንዘብ እየፈጠሩ ነው፤ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ አሁን ያለው በቂ ላይሆን ይችላል ወደፊት ግን እያደገ እና እየጎለበተ የሚመጣ ነው፡፡
በግብርናው ዘርፍ ደግሞ ብናይ የአትክልት እና ፍራፍሬ፤ እንዲሁም ሌሎች ሰብሎች ምርምር እየተካሄደ፣ ምርታቸው ገንዘብ እያስገኘ ባለሙያውንም የአካባቢው ማኅበረሰብንም እንዲሁም ዩኒቨርሲቲውን እየጠቀመ ይገኛል፡፡ በሌሎች ዘርፎችም ተመሳሰይ ሥራዎች አሉ፤ የሚያበረታቱ ናቸው፤ ራስ ገዝ ለመሆን የምናደርገውን ጉዞም የሚያሳልጡ ናቸው፡፡
ራስ ገዝ ለመሆን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እና ግንኙነት ያስፈልጋል፤ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው በዓለም አቀፍ ትብብር ነው፤ በአሜሪካ መንግሥት፣ በዓለም የምግብ ድርጅት እና በዩኒሴፍ አማካኝነት ነው የተቋቋመው፤ ስለሆነም ከማንም በላይ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብርን በደንብ የሚረዳ ተቋም እና ማኅበረሰብ ነው ያለን፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ በአሁኑ ሰዓት በሀገር ውስጥም በውጪም ከ150 በላይ የሚሆኑ አጋሮች አሉን፤ እነዚህ አጋሮች ለተቋማችን ሰፊ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ለአብነት ጀርመኖችን ብንወስድ የቀድሞው ካርል ማርክስ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ናቸው የጎንደር የሕክምና ትምህርት ቤትን ከ43 ዓመታት በፊት የመሠረቱት፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ እና ብቁ የሕክምና ባለሙያዎችን እያፈራን ያለነው ጀርመኖች በከፈቱት መንገድ በመዝለቁ ነው፡፡
አሜሪካኖችን ብናይ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰጡን የመሳሪያ፣ የአቅም ግምባታ እና ሌሎች ድጋፎች አሉ፡፡ የተለያዩ ባለሙያዎችን በፈለግናቸው ጊዜ ይልኩልናል፤ የእኛን ባለሙያዎች እየወሰዱ ያሰለጥኑልናል፡፡ ትልቁ እና ዘመናዊው ህንጻችን የተሠራው በሲዲሲ ነው፡፡
በመሆኑም የአጋሮቻችን ሚና የማይተካ ነው፡፡ በርካታ መምህራን ፒኤች ዲ እና ማስተርሳቸውን በውጭ ሀገራት ተምረው ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እና አሠራር ቀስመው መጥተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲያችን አሁን ካለበት ደረጃ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡
በተለያዩ ፕሮጀክቶች የምናገኘው ገንዘብም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ የውጭ ምንዛሬ ለሀገር በማስገባት ጭምር ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ለምሳሌ ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የተባለውን ካናዳ ሀገር የሚገኝ ብቻ ብንወስድ ከ27 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ ነው ፕሮጀክቱ የያዘው፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ከ450 በላይ የሚሆኑ የአካል ጉዳተኞች የትምህርት እድል እንዲያገኙ አስችሏል፡፡
በሌላ በኩል 60 የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲያችን መምህራን በካናዳ ሀገር ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው፡፡ አዳዲስ የትምህርት መስኮችንም ነው ቀስመው ይዘው የሚመጡት፤ ለአብነት “ኦኮፔሽናል ቴራፒ” የሚባል ፕሮግራም ከፍተናል፤ ይህም ከሽምግልና ጋር ተያይዞ የሚመጡ በሽታዎችን ማከም ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲያችን ከአጋሮች ጋር በመሥራቱ ፕሮግራሙ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ተከፍቷል፡፡
በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
ዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ተኮር ነው፤ የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል ያለበት ጫና ከፍተኛ ነው፡፡ አብዛኛውን አማራ ክልል፣ ከፊል ትግራይ፣ ከፊል ቤንሻንጉል፣ ከፊል ሱዳን ሳይቀር ሪፈራል ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ በግብርና ዘርፍም ሕዝቡን እያገለገለ ነው። ዘር እናመርታለን፤ እናደርሳለን።
የእንስሳት ሕክምናችንም ብዙ አልተወራለትም እንጂ ጥሩ ነው። ማዳቀል፣ ወተት ማምረት፣ እንቁላል ምርት ጊደር እና ኮርማ ማቅረብ ከምንሰጣቸው አገልግሎቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የማኅበረሰብ ትምህርት ቤት አለን፤ ጥራት ያለው ትምርት በመስጠት ምሳሌ ነው በየጊዜው የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ከወጣቱ እና ከአርሶ አደሩ ጋር በአጠቃላይ ማኅበረሰብ ተኮር ናቸው፡፡
በመጨረሻም አሚኮን ጨምሮ ለዩኒቨርሲቲያችን እድገት እያገዙን ላሉ አካልት በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
እንግዳችን ስለነበሩ እናመሰግናለን!
እኔም አመሰግናለሁ!
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም