የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል

0
160

በሀገራችን ያለው የኑሮ ውድነት የነዋሪዎች ፈተና ከሆነ ውሎ አድሯል። በኩር በተለያዩ ጊዜያት ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች እንዳሉት ግጭቱ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት አላስቻላቸውም። ምርትም ወደ ተጠቃሚው እንዳይደርስ አድርጓል። ይህ ሁሉ ተደማምሮ ታዲያ በምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በማስከተሉ ኑሮን ፈታኝ አድርጎታል።

በሌላ በኩል የአማራ ክልል ንግድ ቢሮ አሁናዊ የግብይት ሁኔታን ዋቢ አድርጎ እንዳስታወቀው የገበያ መረጋጋት ታይቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኑሮ ዉድነቱ እየከፋ መሄዱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ተናግረዋል። ይህን ያሉት ደግሞ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ በተካሄደበት ወቅት ነው። የፓርላማ አባሉም “የኑሮ ውድነቱ     ከፍቷል፣ የመንግሥት ሠራተኛዉ መኖር አቅቶታል፣ የኑሮ ዉድነቱን ማረጋጋት አልተቻለም” በማለት ምን እንደታሰበ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም “ምርት እና ምርታማነት እያደገ ሲሄድ የኑሮ ውድነቱም እየተሻሻለ ይሄዳል” ነው ያሉት።

የኑሮ ውድነት በዓለም ደረጃም ፈታኝ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ዓለም ላይ ያሉ ያደጉ ሀገራት ጭምር የኑሮ ውድነቱን ለምርጫ ቅስቀሳ እንደመወዳደሪያ እየተጠቀሙ እንደሆነ በማንሳትም ይህም ችግሩ ዓለም አቀፍ እና ሥር የሰደደ መሆኑን ነው ያስረዱት። “የኑሮ ውድነት በዓለም ላይ ስብራት፣ ጭንቀት እየሆነ ነው። የኢትዮጵያም ከዚህ የተለየ አይደለም” ብለዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ልማትን የሚያፋጥን መንግሥት በዚያውም የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ከባድ ይሆንበታል። ለልማት የሚያውለውን ገንዘብ ለኑሮ ውድነት መቀነሻ በድጎማ ስለሚያውለው ልማትን ለማፋጠን ፈተና እንደሚሆን ጠቁመዋል። ቢሆንም ግን ኢትዮጵያ ልማቷን ሳታቋርጥ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ያደረገችው ጥረት የተሻለ ውጤት ማስገኘቱን አክለዋል።

“ምርታማነትን ማሳደግ የሁሉ ነገር ቁልፍ ነው በሚል ሢሠራ ቆይቷል። ኢትዮጵያ ስትሠራው የቆየችው የኩታ ገጠም የስንዴ፣ የሩዝ፣ የፍራፍሬ፣ የጓሮ አትክልት፣ የተማሪዎች ምገባ፣ የማዕድ ማጋራት እና መሰል ሥራዎች ለውጥ አምጥተዋል” ብለዋል።

በሌላ በኩል “ምርት ተመረተ ይባላል፣ ግን ዋጋ አልቀነስም” የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸውም የምርት ዕድገት አለ ሲባል ምርትን ሁሉም ቦታ ማዳረስ እና የገበያ ሁኔታውን ማየት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። ይህም ሌላ ፈተና እንደሆነ በማንሳት በትኩረት የሚሠራበት መሆኑን አመላክተዋል።

የኑሮ ውድነቱን ለማስተካከል ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል። በዚህም  “የዋጋ ንረቱን ባለፈው ዓመት ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 23 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማብራሪያቸው።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የኑሮ ውድነቱ ዓለም አቀፋዊ ነው። ይህንኑ ሐሳብ የተጋሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንዳንድ ሀገራት ከ60 በመቶ በላይ የደረሰ የዋጋ ንረት መመዝገቡንም አብነት አንስተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በሀገራችን ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው የሌማት ትሩፋት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በተለይ ግብርና ላይ ጥገኛ የሆኑ የሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ምርታማነትን ማሳደግ የዋጋ ንረትን ለማስተካከል አይነተኛ መፍትሔ አድርገው ይተገብሩታል። በሀገራችንም የኑሮ ውድነቱን ለማስተካከል “ምርታማነትን ለማሻሻል እየሠራን ነው። በዘንድሮው ዓመት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብልጫ ያለው ምርት መሰብሰብ ተችሏል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት በሰብል ምርት አምና እንደ ሀገር 395 ሚሊዮን ኩንታል ተመርቷል። ዘንድሮ ደግሞ 507 ሚሊዮን ኩንታል ተመርቷል።

ምርታማነትን ለማሳደግ ከገጭት ነጻ አካባቢ መፍጠር ቁልፉ ጉዳይ ነው፤ በመሆኑም የሚታዩ ግጭቶችን እልባት መስጠት ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ወገን ዝግጁ ሆኖ ኃላፊነቱን ሊወጣ እደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለፓርላማ አባላት ባደረጉት ንግግር ሰላምን ለማስፈን መንግሥት ለንግግር ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here