የመጫረሻዎቹ አራት ቡድኖች

0
134

በመካከለኛው አውሮፓዊቷ ሀገር ጀርመን ለአንድ ወር ያህል ሲካሄድ የነበረው ግዙፉ የአውሮፓውያን እግር ኳስ ድግስ ተጠናቋል። በዚህ 17ኛው የእግር ኳስ መድረክ ያልተጠበቁ ድራማዊ ክስተቶች ታይተው አልፈዋል። ታላላቆቹ የእግር ኳስ ሀገራት ደክመው ከመንገድ ቀርተዋል። ያልተጠበቁት ደግሞ ጥሎ ማለፉን ተሻገረው ተመልክተናል። በመጨረሻም የበረቱት ምርጥ አራት ብሄራዊ ቡድኖች መካከል ራሳቸውን አስገብተዋል፤ ስፔን፣ ፈረንሳይ ፣ እንግሊዝ እና ኔዘርላንድስ።

የዘንድሮው የጀርመኑ የአውሮፓ  ዋንጫ  በግቦች የተንበሸበሽ አልነበረም ማለት ይቻላል።  ይሁን እንጂ በአማካይ  በየጨዋታው ከሁለት ግቦች በላይ መቆጠሩን ቁጥሮችን ጠቅሶ የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል። የፍጻሜ እና የደረጃ ጨዋታዎችን ሳይጨምር 50 ጨዋታዎች ተደርገዋል፤ 114 ግቦች ደግሞ ከመረብ አርፈዋል።  በርካታ ድንቅ ድንድንቅ ግቦችንም የተመለከትን ሲሆን   እስከ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ድረስ፤ ጀርመን ስኮትላንድን አምስት ለአንድ  ያሸነፈችበት ውጤትም ትልቁ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል። በየጨዋታው ከ52 ሺህ በላይ ተመልካች ሰቴዲየም ገበቶ ጨዋታውን ተመልክቶታል፡፡

17ኛው የአውሮፓውያኑ የእግር ኳስ ድግስ ልብን በሚያሞቁ ትንፋሽን በሚያስውጡ አስደናቂ ድራማዊ ክስተት ታጅቦ ነው የተጠናቀቀው። ልብ አንጠልጣይ የዘጠና ደቂቃ ፌሽታ እና ቅስም ሰባሪ ሀዘንም በጀርመኑ መድረክ ታይቷል። በሽርፍራፊ ሰከንድ ግቦች እና መለያ ምቶች ታላላቅ ብሄራዊ ቡድኖች ሳይቀሩ ከውድድሩ ውጪ ሆነው ዐይተናል። በኦፕታ አናሊስት ቀደም ብሎ ብዙ ግምት የተሰጣቸው ብሄራዊ ቡድኖች በመድረኩ ጉልበታቸው ዝሎ ተመልክተናል። ብዙ ግምት ያልተሰጣቸው ብሄራዊ ቡድኖች ግን ግምቶችን ፉርሽ አድርገው ራሳቸውን ምርጥ አራቱ ቡድን ውስጥ አስገብተዋል።ፖርቹጋላዊው ተከላካይ ፔፔ በአውሮፓ ዋንጫው ታሪክ ሩብ ፍጻሜ ድረስ የተጫወተ በእድሜ ትልቁ ተጫዋች ሲሆን የመድረኩ ክስተት ላሚን ያማል ደግሞ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ሆኗል።

የ39 ዓመቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ደግሞ በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች አንድም ግብ ሳያስቆጥር ከጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ ተሰናብቷል። ይባስ ብሎ ከስሎቬኒያ ጋር በነበረው የጥሎ ማለፍ  ጨዋታ መደበኛ ዘጠና ደቂቃ አልቆ የተሰጠውን መለያ ምት ሳይጠቀምበት አምክኖታል። ይህም ለብሄራዊ ቡድኑ መሳተፍ ከጀመረበት 2004 እ.አ.አ ጀምሮ ግብ ሳያስቆጥር የወጣበት ውድድር ሆኖ ተመዝግቧል። ሮናልዶ በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች 15 ጊዜ የግብ ሙከራ ማድረጉ አይዘነጋም።

አንድሪ ኦናናን፣ ኬቨን ዲብሮይነን፣ ሮሚዮ ሉካኩን፣ ጀርሚ ዶኩን እና የመሳሰሉትን የያዘው የቤልጄየም ብሄራዊ ቡድን ሩብ ፍጻሜ እንኳ መቀላቀል ተስኖት አንገቱን ደፍቶ የጀርመንን ምድር ለቋል። አንድም ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫን ማሳካት ያልቻሉት ቤልጀየማዉያን አሁንም ሌላ ተጨማሪ ዓመታትን ተስፋ በማድረግ ነው የተሰናበቱት።

በአውሮፓ ዋንጫ የጀርመንን ያህል በመድረኩ ልምድ ያለው ብሄራዊ ቡድን የለም። እስካሁን በአጠቃላይ ከተደረጉ 17 የመድረኩ ምዕራፎች በ14ቱ በመሳተፍ ቀዳሚ ነው። በጠኙ ደግሞ ግማሽ ፍጻሜ ሲደርስ ልክ እንደ ስፔን ብሄራዊ ቡድን ሦስት ጊዜ ዋንጫውን ወስዷል። ለወትሮ ግማሽ ፍፃሜ መድረስ የማይቸገሩት ጀርመኖች ዘንድሮ ግን በደጋፊያቸው ፊት አቅም አንሷቸው ከመንገድ ቀርተዋል። በሩብ ፍጻሜው በስፔን ሁለት ለአንድ ተሸንፈው በሀገራቸው የበይ ተመልካች ሆነዋል። አስተናጋጅ ሀገር ዋንጫውን ካነሳ 40 ዓመታትን ተቆጥረዋል። ውድድሩ ሲጀመር ይህንን እርግማን ለመስበር ቆርጠው የተነሱት ጀርመናውያን የጁሊያን ኔግልስማን ታክቲክ እና ቀመር ባለመስራቱ ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ለብሄራዊ ቡድኑም የመጨረሻውን ጨዋታ ያደረገው የመሀል ሜዳው ሰው ቶኒ ክሩስ በመጥፎ ትዝታ ጫማውን ሰቅሏል።

የ2020 የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊዋ ሀገር ጣሊያን ከአራት ዓመታት በፊት ያሳየችውን ድንቅ አቋም መድገም ተስኗት ከውድድሩ በጊዜ ተሰናብታለች። ጣሊያን በጥሎ ማለፉ በስዊዘርላንድ ሁለት ለባዶ ተሸንፋ ነው ከውድድሩ የተሰናበተችው። በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ጆርጂያ ደግሞ በመጀመሪያ ተሳትፎዋ አስደናቂ የተባለውን ጊዜ አሳልፋለች።

የናፖሊውን የፊት መስመር ክቬቻህ ካቫርስቲኬሊያህን የያዘችው ጆርጂያ ከምድብ ስድስት ምርጥ ሦስተኛ ሆና ነበር ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለችው። የመድረኩ እንግደዋ ሀገር በጥሎ ማለፉ ግን በስፔን ክፉኛ ተደቁሳ ከውድድር ውጪ ሆናለች። የጆርጂያ ብሄራዊ ቡድን ጥሎ ማለፍ ድረስ በመጓዙ ከሀገሪቱ ቢሊየነር ቢዚና ኢቫኒሺቪሊ የዐስር ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ተበርክቶለታል።

ወጣት ኮከቦችን ከአንጋፋ ተጫዋች ጋር አጣምሮ የያዘው የስፔን ብሄራዊ ቡድን ለዐይን ሳቢ እና ማራኪ እግር ኳስ በመጫወት በዚህ መድረክ ከተመለከትናቸው ቡድኖች ውስጥ ቀዳሚው ነው። ብሄራዊ ቡድኑ ከዚህ በፊት ሦስት ጊዜ የመድረኩን ዋንጫ ያሳካ ሲሆን በጀርመኑ የእግር ኳስ ድግስ ሩቅ ይጓዝል ብሎ ግን ማንም የጠበቀው አልነበረም።ይሁን እንጂ የመጨረሻዎቹ ሁለት ቡደኖች አንዱ መሆን ችሏል፡፡ ሁሉንም የምድብ ጨዋታዎች ያሸነፈ ብቸኛው ብሄራዊ ቡድንም ነው። በጥሎ ማለፉ ጆርጂያን በቀላሉ አራት ለአንድ በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ተሻግሯል።

በሩብ ፍጻሜው ደግሞ የውድድሩ አጋፋሪዋን ሀገር ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ምርጥ አራት ቡድኖች መካክል አንዱ መሆን ችለዋል-ሰፔኖች። በዚህ የአውሮፓ ዋንጫ የ16 ዓመቱ ላሚን ያማል ለስፔን ያበረከተውን አስተዋጽኦ አንድም ታዳጊ ተጫዋች ያደረገ የለም። ታዳጊው የእግር ኳስ ኮከብ ግቦችን አስቆጥሯል፤ በርካታ ግብ የሆኑ ኳሶችን ደግሞ ለቡድን ጓደኞቹ አቀብሏል።

ያማል በአንድ የውድድር መድረክ አምስት ግብ የሆኑ ኳሶችን ለቡድን ጓደኞቹ አመቻችቶ በማቀበል አዲስ ክብረወሰን ይዟል። ከ1996 እ.አ.አ በኋላ በዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ጨዋታ በአንድ ውድድር በርካታ ግብ የሆኑ ኳሶችን በማቀበል ቀዳሚ ተጫዋች መሆን ችሏል። ስፔን ባሳለፍነው ዓመት የ2022 የኔሽንስ ሊግ ዋንጫ ማሳካቷ አይዘነጋም።

በዓለም እና በአውሮፓ ዋንጫ በተደጋጋሚ ፍጻሜ በመድረስ የሚታወቀው የኔዘርላንድስ ብሄራዊ ቡድን በጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ ልክ እንደ ስፔን በሄራዊ ቡድን ምርጥ አራት ውስጥ ይገባል ተብሎ አልተገመተም። ብርቱካናማዎቹ አጀማመራቸውም ቢሆን ደካማ እንደነበር አይዘነጋም። ምርጥ ሦስተኛ ቡድን በመሆን ነበር ጥሎ ማለፍ የደረሱት።

በጥሎ ማለፉ ሮማኒያን ሦስት ለባዶ እና በሩብ ፍጻሜው ደግሞ ተርኪዬን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜ ገብተዋል። በዚህ መድረክ ሳትጠበቅ ሩቅ የተጓዘችው ተርኪዬ በወጣት ኮከቧ አርዳ ጉለር በመታገዝ  ብርቱካናማዎችን በእጅጉ ፈትና እንደነበር አይዘነጋም።  የሊቨርፑሉ አጥቂ ኮዲ ጋክፖ ሊቨርፑላውያን በአንፊልድ የሚፈልጉትን ዓይነት ድንቅ ብቃቱን ለኔዘርላንድስ እያሳየ ይገኛል፡፡ ተጨዋቹ በአምስት ጨዋታዎች አራት ግቦችን ሲያስቆጥር አንድ ግብ የሆነ ኳስ ለጓደኞቹ አመቻችቶ አቀብሏል።

አምበሉ እና የኋላ ደጀኑ ቨርጅል ቫንዳይክም ሌላኛው የቡድኑ የጀርባ አጥንት ተጫዋች ቢሆንም ሜዳ ላይ ብዙ ስህተቶችን የሠራ ተጫዋች ነው። ግን ደግሞ በርካታ የአየር ላይ ኳሶችን ማሸነፉን ቁጥሮች ይናገራል።  ጀርመን በጂኦግራፊያዊ የመሬት አቀማመጧ ለብዙ የአውሮፓ ሀገራት ቅርብ በመሆኗ በግማሽ ፍጻሜው እንግሊዝ ከኔዘርላንድስ በነበረው ጨዋታ 80 ሺህ ተመልካች  ከኔዘርላንድስ ብቻ  በባቡር እና ሌሎች መጓጓዣዎች ተጉዘው ሀገራቸውን መደገፋቸውን ቢቢሲ አስነብቧል።

በዲዲየር ዴሾ የሚመራው ብሄራዊ ቡድን  ሜዳ ላይ የተጠበቀውን ያህል ሳያሳይ ግማሽ ፍጻሜ መድረሱ ብዙዎችን አስገርሟል። የጨፈገገው እና አሰልቺው የዲዲየር ዴሾ በጀርመን የታየው የእግር ኳስ ፍልስፍና ውጤታማ አልነበረም። በብዙ የተጠበቀው እና በኮከቦች የተሞላው የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን በክፍት ጨዋታ አንድ ግብ ብቻ አስቆጥሮ ጉዞው ግማሽ ፍጻሜ ድረስ ብቻ ሆኗል። በራስ መረብ ላይ እና በፍጹም ቅጣት ምት በተቆጠሩ ግቦች ግማሽ ፍጻሜ ድረስ የተጓዘውን ቡድን አልጋ ወራሾቹ ስፔናውያን ኮከቦች ከውድድሩ ውጪ አድርገውታል።

ኬሊያን ምባፔን፣ ንጎሎ ካንቴን፣ አንቷን ግሪዝማንን፣ ኦስማን ደበሌን እና የመሳሰሉትን ባለተሰጥኦዎች የያዘው የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ከእንግሊዝ ቀጥሎ በኦፕታ አናሊስት የዋንጫ ቅድመ ግምት ተሰቶት እንደነበረ አይዘነጋም። ከምድብ ጨዋታው ጀምሮ የፈዘዘው ቡድኑ ሁለተኛ ሆኖ ነበር ጥሎ ማለፍ የደረሰው። በጥሎ ማለፉም የቤልጂየምን ብሄራዊ ቡድን አንድ ለባዶ በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜ ገብቷል። በሩብ ፍጻሜው ከፖርቱጋል ጋር የተገናኘ ሲሆን በመለያ ምት ቀጣዩን ዙር ተቀላቅሏል።

በግማሽ ፍጻሜው ግን እንደ ተረብ የሚናደፉትን ወጣት ስፔናውያን ባለተሰጥኦ ማቆም ባለመቻሉ ሁለት ለአንድ ተሸንፈዋል። በዚህ መድረክ በብዙ የተጠበቀው አዲሱ ጋላክቲኮ ኬሊያን ምባፔ ሀገሩን መታደግ አልቻለም።  ተጫዋቹ በሁለቱ የዓለም ዋንጫዎች እና በኔሽንስ ሊጉ ያሳየውን ድንቅ እንቅስቃሴ  መድገም ሳይችል የአውሮፓ ዋንጫውን አጠናቋል። ምባፔ በፈረንሳይ ፖለቲካ መሳቡ፣ በደረሰበት የአፍንጫ ጉዳት ምክንያት ባጠለቀው የፊት ጭምብል ምቾት ማጣቱ ለአቋሙ መውረድ በምክንያትነት ተነስቷል።

በአውሮፓ ዋንጫው ከተሳተፉ ሀገራት መካከል ተሰጥኦ ያለው ስብስብ በመያዝ እንግሊዝን የሚስተካከላት እንደሌለ መረጃዎች አመልክተዋል። ጥልቀት ያለውን ስብስቧን ከግምት ውስጥ ያስገባው ኦፕታ አናሊስትም ለዋንጫ ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት መካከል በቀዳሚነት አስቀምጧት ነበር። ይሁን እንጂ እንግሊዝ በአውሮፓ ዋንጫው በየጨዋታው  ደካማ የተባለውን አቋም አሳይታለች። እንዲያውም  ሦስቱ አናብስት ምርጥ አራት ቡድኖች መካከል ብቻ ሳይሆን የመጨረሻ ሁለት ቡድኖች መካክል መገኘቷ ብዙዎችን አስገርሟል።

ምድቡን በበላይነት ያጠናቀቀችው እንግሊዝ በጥሎ ማለፉ ስሎቫኪያን ሁለት ለአንድ አሸንፋለች። ሩብ ፍጻሜ ላይ ከስዊዘርላንድ ጋር የተገናኘችው እንግሊዝ መደበኛው ዘጠና ደቂቃው በአንድ አቻ ውጤት በመጠናቀቁ እንግሊዝ መለያ ምቱን ማሸነፍ ችላለች። በግማሽ ፍጻሜው ደግሞ ከኔዘርላንድ ጋር ተገናኝታ፤ ሁለት ለአንድ አሸንፋ ለፍጻሜ ደርሳለች።  ስፔንን እና እንግሊዝን ያገናኘው የ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በስፔን አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here