የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል። ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ መልኩ ከተጀመረበት 1990 ዓ.ም ወዲህ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሊጉን ዋንጫ ያሳካ ዘጠንኛው ክለብ ሆኖ ተመዝግቧል። አዲስ አዳጊው ክለብ ፕሪሚየር ሊጉን በተቀላቀለበት ዓመት ዋንጫውን ያሳካ ሦስተኛ ክለብም መሆን ችሏል።
ከዚህ በፊት ሀዋሳ ከተማ በ1996 ዓ.ም እና ጅማ አባ ጅፋር በ2010 ዓ.ም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በመጡበት ዓመት ዋንጫውን ማሸነፋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ንግድ ባንክ 64 ነጥቦችን በመሰብሰብ ነበር፤ የውድድር ዓመቱን በበላይነት ያጠናቀቀው። መቻል በአንድ ነጥብ አንሶ ሁለተኛ እና ኢትዮጵያ ቡና ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ሻሸመኔ ከተማ እና ሀምበሪቾ ዱራሜ ደግሞ ሊጉን መቋቋም ተስኗቸው በመጡበት ዓመት ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ወርደዋል።
ሻምፒዮኑ ክለብ በ1975 ዓ.ም እንደተመሰረተ የታሪክ ማህደሩ ያስነብባል። ይሁን እንጂ የእድሜውን ያህል በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስኬታማ ግን አይደለም። የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳካው ንግድ ባንክ ክለቡ ከስድስት ዓመታት በኋላ ነበር፤ ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው።
በ2009 ዓ.ም ወደ ከፍተኛ ሊግ ከወረደ በኋላ ክለቡ ፈርሱ እንደነበረ አይዘነጋም። እንደገና ድጋሚ የተቋቋመው ክለብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠንካራ እና ተፎካካሪ በመሆን የሊጉን ዋንጫ ወስዷል። ንግድ ባንክ ዘንድሮ ካደረጋቸው 30 መርሀግብሮች 19ኙን አሸንፏል። ይህ ቁጥራዊ መረጃም በ2016 ዓ.ም በርካታ ጨዋታዎችን ካሸነፉ ሁለት ክለቦች መካከል አንዱ አድርጎታል።
በውድድር ዓመቱ አራት ጨዋታዎችን ብቻ የተሸነፈ ሲሆን አነስተኛ ጨዋታዎችን የተሸነፈ ቀዳሚው ክለብም ያደርገዋል። 57 ግቦችን በተጋጣሚው መረብ ላይ ሲያስቆጥር 27 ግቦች ደግሞ ተቆጥረውበታል። ካስቆጠሯቸው ግቦች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት 28 ግቦች፤ በሦስት ተጫዋቾች ብቻ መቆጠራቸውን ቁጥራዊ መረጃዎች ያሳያሉ። አዲስ ግደይ፣ ሳይመን ፒተር እና ባሲር ሁመር በጋራ 28 ግቦችን በጋራ ከመረብ ያገናኙ ተጫዋቾች ናቸው።
በሁሉም የሜዳ ክፍል በወጥ አቋም መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾችን መያዙ ያስመዘገበው ውጤት እና ቁጥራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። የክለቡ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑል ሰገድ በፕሪሚየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ባሰለጠነበት ዓመት የመጀመሪያውን ዋንጫ ማሳካት ችሏል። አሰልጣኙ በ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ መድንን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካሳደገው በኋላ መሰናበቱ ይታወሳል። ከዚያም በኋላም ንግድ ባንክን በመረከብ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማሳደግ ሻምፒዮን ማድረግ ችሏል።
የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እስከመጨረሻው ሳምንት መርሀግብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ የውድድር ዓመቱን ያጠናቀቀው መቻል ነው። መቻል ከሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንድ ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ 63 ነጥቦችን በመሰብሰብ ነው ዓመቱን የጨረሰው። ክለቡ ባሳለፍነው ዓመት በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እየተመራ ደካማ አቋም ማሳየቱ አይዘነጋም።
የተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከመጀመሩ በፊት አሰልጣኝ ገብረ ክርስቶስ ቢራራን፣ ሽመልስ በቀለን እና ሌሎችንም የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾችን በማስፈረም ነበር ዓመቱን የጀመረው። ቢሆንም መቻልን ተፎካካሪ ይሆናል ብሎ የገመተው እንዳልነበር የሚታወስ ነው። አሰልጣኝ ገብረ ክርስቶስ ቢራራ ግን ተፎካካሪ ቡድን ገንብተው አሳይተዋል።
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ አስፈሪ የፊት መስመር እና ጠንካራ የኋላ ክፍል ከነበራቸው ቀዳሚ ክለቦች ተርታም ይሰለፋል። መቻል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከኢትዮጵያ ቡና ቀጥሎ ጠንካራ የፊት መስመር የነበረው መሆኑ ያስቆጠራቸው ግቦች ማሳያ ናቸው። በአጠቃላይ 47 ግቦችን ከመረብ ሲያገናኝ 27 ግቦች ደግሞ ተቆጥረውበታል።
ኢትዮጵያ ቡና ባሳለፍነው የክረምቱ የዝውውር ወቅት በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈርም ነበር የውድድር ዓመቱን የጀመረው። የውድድር ዓመቱንም በዋንጫ ታጅቦ ያጠናቅቃል የሚል ቅድመ ግምት አግኝቶ እንደነበር የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ግምቶቹ ፉርሽ ሆነው ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ቡናማዎቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሊጉ ተፎካካሪ እየሆኑ መምጣታቸው ግን አይካድም። በተለይ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የንግድ ባንክ እና የመቻል ጠንካራ ተፎካካሪ መሆናቸውን አስመስክረዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከንግድ ባንክ ቀጥሎ ጠንካራ የፊት መስመር የገነባ ክለብ እንደነበረ ቁጥሮች ይናገራሉ።ምንም እንኳ ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ቢያጠናቅቅም በኢትዮጵያ ዋንጫ፤ ወላይታ ዲቻን በማሸነፍ የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ተሳትፎውን አረጋግጧል።
የአምናው ሻምፒዮኑ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮም ለዋንጫ ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ቡድኖች መካካል ቀዳሚው ነበር። ፈረሰኞቹ ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው አጨራረሳቸውን ያሳምራሉ ተብለው ነበር። በእርግጥም አንጋፋው ክለብ በመጀመሪያው ዙር ውድድር በዋንጫው ፍክክር እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። በኋላ ግን ቀስ በቀስ እየተንሸራተተ የውጤት ቀውስጥ ገጥሞታል። በዚህ ምክንያትም ከአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጋር ተለያይቷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ የወትሮ ጠንካራ ጉልበቱ ከድቶት ስድስተኛ ሆኖ ነው ዓመቱን የጨረሰው።
ባሕር ዳር ከተማም ባሳለፍነው ዓመት ያሳየውን ምርጥ አቋም ዘንድሮም እንደሚደግምው ደጋፊዎች እምነት አሳድረው እንደነበር ይታወሳል። የውድድር ዓመቱ ከመጀመሩ በፊትም ለዋንጫ ከታጩ ቡድኖች መካከል ነበር። የጣናው ሞገድ በ2015 ዓ.ም የክረምቱ የዝውውር ወቅት የተለያዩ ሥፍራ ተጫዋቾችን በማስፈረም እና ቡድኑን በማጠናከር ዓመቱን ቢጀምርም እንዳሰቡት ሳይሆን አመቱን ጨርሰዋል። ምንም እንኳ ከመጀመሪያው ዙር የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ወደ መሪዎች መጠጋት የሚያስችለውን ውጤት ቢያስመዘግብም ሊጉ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሳምንታት ሲቀሩት የአቋም መውረድ ገጥሟቸዋል። ዓመቱንም አራተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል።
ልክ እንደ ባሕር ዳር ከነማ ሁሉ ፋሲል ከነማም ለዋንጫ ቅድመ ግምት የተሰጠው ቡድን እንደነበር የሚታወስ ነው። አፄዎቹ በክረምቱ የዝውውር ወቅት አሰልጣኙን ጨምሮ ጌታነህ ከበደን፣ ጋቶች ፓኖምን እና የመሳሰሉትን በርካታ ተጫዋቾችን ማስፈረማቸው የሚታወስ ነው። ፋሲል ከነማ አጀማመሩ አስከፊ ባይሆንም አጨራረሱ ግን አላማረም። አፄዎቹ ልክ እንደ አምናው ደካማ አቋም በማሳየት ዓመቱን ጨርሰዋል፤ በደረጃ ሰንጠረዡ አምስተኛ ደርጃን ይዞ አጠናቋል።
በአጠቃላይ ግን የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከባለፈው ዓመት አንፃር ዘንድሮ በሁሉም ረገድ የተሻለ እና ጠንካራ ፉክክር የታየበት መሆኑን የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ ወገኔ ዋልተንጉስ (ዶ.ር) ከአሚኮ ብኲር ሰፖርት ዝግጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። ዘንድሮ ብዙ የተሻሻሉ ነገሮች መኖራቸውን በግምገማችን ተመልክተናል ብለዋል የቦርድ ሰብሳቢው፤ወገኔ (ዶ.ር) መሽሻል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ግን አልሸሸጉም።
ከአምናው በተሻለ መልኩ ዘንድሮ በጥሩ መንገድ ውድድሮች ተከናውነዋል፤ ይህም ትልቅ ስኬት እንደሆነ ገልፀዋል። ይሁን እንጂ ከዚህም በላይ ውድድሮችን ማዘመን ይገባናል ሲሉ አብራርተዋል። የድሬድዋ ስቴዲየም በሙሉ አቅሙ ውድድሮችን ማስተናገድ መቻሉ፣ የኃይል መቆራረጥ ችግር መቀረፉ፣ የመጫዎቻ እና የመለማመጃ ሜዳ ጥራት እና እጥረት ችግሮች መቀነሱ፣ የስፖርታዊ ጨዋነት መሻሻል እና የጎላ የዳኝነት ችግሮች አለመስተዋሉ ፕሪሚየር ሊጉ ስለመሻሻሉ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
ይህም የሊጉን ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገው የቦርድ ሰብሳቢው ወገኔ ዋልተንጉስ (ዶ.ር) ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት በሀዋሳ ስቴዲየም ዝናብ ሲዘንብ ጨዋታዎችን ለማከናወን ይቸገሩ እንደነበር የገለጹት የሊጉ አክሲዮን ማህበር ቦርድ ሰብሳ፤ ዘንድሮ ግን ያሁሉ ተሻሽሎ ተመልክተናል ብሏል። 16ቱም ክለቦች እና ሁሉም ከተሞች የራሳቸውን ሜዳ ቢኖራቸው ክለቦች ደጋፊያቸው ፊት መጫወት የሚያስችላቸው አጋጣሚ ይፈጠራል፤ በተጨማሪም እንግልትን እና አላግባብ ወጪን ያስቀራሉና ሊያስቡብት ይገባል ተብሏል።
የሀገራችን ክለቦች እና ተጫዋቾች ፕሮፌሽናል አስተሳሰብ ሊኖራቸው እንደሚገባም ነው ወገኔ (ዶ.ር) የጠቆሙት። ውድድሮች የሚጠናቀቁበት አግባብ ትክክል አይደለም፤ የሊጉ መጨረሻ ሳምንታት መርሀግብሮች ብዙ ጊዜ ክለቦች በሙሉ አቅማቸው እንዳማይጫወቱ የሊጉ አክሲዮን ማህበር ደርሼበታለሁ ብሏል። ታዲያ ችግሩን ለመቅረፍ በቀጣይ ዓመት የሕግ ማዕቀፍ ሊኖረው እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል።
“ አሸናፊው እና ወራጁ ክለብ ከተለየ በኋላ የክለቦች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በሚገባው ልክ አይሆንም፤ ማሰብ ያለባቸው ግን የእነርሱን ፉክክር በቴሌቭዥን መስኮት የሚመለከት በርካታ ደጋፊ እና ተመልካች ስለሚኖር የሚፈለገውን እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርባቸዋል” የሚል ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል ወገኔ (ዶ.ር)።
ከዚህ ባሻገር አንድ አንድ ክለቦች የውድድር ዓመቱ ሳይጠናቀቅ ለተጫዋቾቻቸው እና ለአሰልጣኞቻቸው እረፍት የሰጡ ክለቦች እንዳሉም ተጠቁሟል። ለአብነት ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ፋሲል ከነማ፣ ባሕር ዳር ከነማ፣ ሀዋሳ ከነማ እና ኢትዮጵያ መድንን የመሳሰሉ ክለቦች ፕሪሚየር ሊጉ ሦስት እና ሁለት ጨዋታ ሲቀረው ለተጫዋቾች ብሎም ለአሰልጣኞች እረፍት እንደሰጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ዓይነት ድርጊት በየትኛውም የዓለማችን ሊግ የማይታይ አሳፋሪ ድርጊት በመሆኑ መታረም እንደሚገባው የፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አሳስበዋል።
የሀዋሳ ከተማው አጥቂ አሊ ሱሌማን በ20 ግቦች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ አጠናቋል። የኮከብ ተጫዋች እና አሰልጣኝ ምርጫ ደግሞ ከጥቂት ቀናት በኋላ ይደረጋል፡፡ ዘንድሮ በወረዱት ሻሸመኔ ከተማ እና ሀምበሪቾ ዱራሜ ምትክም አርባ ምንጭ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደጋቸው ቀደም ብለው ማረጋገጣቸው አይዘነጋም። በቀጣይ የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19 ክለቦች እንደሚፎካከሩ የሊጉ አክሲዮን ማህበር መረጃ ያመለክታል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም