በ2004 ዓ.ም ክረምት አጎቴ ቤት ሳለሁ ነው፤ቀን ሰባት ሰዓት ላይ በረዶ የቀላቀለ ኃይለኛ ዝናብ ጣለ። የከብቶች በረት ቆርቆሮ በነፋስ ተነቅሎ የበቆሎው ማሳ ውስጥ ሦስት ያህል ቆርቆሮዎች ተገኙ። የአጎቴ ሚስት ቤት ውስጥ ያለውን ብረት እና ቢላዋ ከቤት እያወጣች ዝናቡ ላይ ትጥላለች። የዛፉ ቅጠል በበረዶ ተበሳስቷል።
ትላልቁ ዛፍ ተንጋሎ ስሩ ተነቅሎ ወድቋል። ግግር የበረዶ ክምር መሬቱን አልብሶታል።ቤቱን ለመንቀል ታግሎ ታግሎ ዝናቡም፤ በረዶውም አንድ ጊዜ ጸጥ አለ። አጎቴ “የዛሬው በረድ የጤና አይደለም” ብሎ ምን እንደተፈጠረ ማሰብ ጀመረ። ሐምሌ ስድስት ቀን ነበር። “የአቦን በዓል የሻረው ሰው በረድ አስፈጀን” በማለት አጎቴ በሐሳብ ተውጦ ሳለ “አያ ተገኘ” የሚል የጥሪ ድምጽ ከውጪ ተሰማ። ጎረቤቱ አያ ዳኛው ነበር። አጎቴ ተደናግጦ ወጣ። “አደራህን ማነው አቦን የሻረው? ከእናንተ ማህበር ዛሬ ማነው በርበሬ ሲተክል የዋለ?” ብሎ ሲጠይቅ አያ ዳኛው “አይ አያ ተገኘ በረዶው እኮ በዓል በመሻራችን አይደለም። ብር ወንዝ የበላው ገበያተኛ ሬሳ አንተ በርበሬ ማሳ ዳር ወድቋል እኮ” ሲለው አጎቴ ክው አለ። ተደናግጠን ከተራራማው ቤታችን ቁልቁል እየተንደረደርን ስንሄድ ብር ወንዝ ዳር ክያ ዛፉን ከብቦ ሰው ተሰብስቧል።
እጁን አገጩ ላይ የጫነ፤ አፍንጫውን በፎጣ አፍኖ የያዘ ሰው ተሰብስቧል። ረጂሙ የክያ ዛፍ ላይ የቆሳሰለ ሰውነት እግሩ የተላላጠ፤ ዝንብ የወረረው ሬሳ ይታያል። ፊቱ ስለተላላጠ መለየት አይቻልም። አለፍ ብሎ ቁምጣ ሱሪው ዛፍ ላይ ተሸንቁሯል። “እግዞ እግዞ መዓት” ይላል ሰው ሁሉ። አጎቴ የሟቹን ቁምጣ በከዘራው ገለጥ እያደረገ ኪሱን መፈተሽ ጀመረ። ወረቀት ተገኘ። መታወቂያው ነበር። ፎቶውም ስሙም አይታይም። ተላልጧል። “እስኪ አንብበው ምን ይላል?” አለኝ አጎቴ “ቋሪት ወረዳ” አልሁት “ሌላስ የለውም?” አጎቴ ጠየቀኝ። ወረቀቱ ስለተጎዳ ፊደላቱን ገጣጥሜ ለማንበብ ያደረግሁት ሙከራ አልተሳካም።
“አይ ተፈርዶ በቃ የቋሪት ሰው ነው፣እኋ ሙላት በልቶት ነዋ” ብሎኝ ከዚህ በፊትም እንዲህ አይነት ድርጊት እንደሚፈጸም ያስታውስ ጀመር። ሟቹን ሰው በቃሬዛ አውርደን በፎጣ ተጠቅልሎ ወደ ደጋማው ሚካኤል ደብር ለቀብር ጉዞ ተጀመረ። ብር ወንዝ ቋሪት ወረዳ ውስጥ ይነሳል። ገነት አቦ ከተማ ሲደርስ ጣሊያ የሚባል ወንዝ ይቀላቀለውና ሌሎችን ገባሮችን ይዞ እየጎለመሰ ይመጣል። ጅጋ ከተማ ሲደርስ በጫፉ ያልፋል። እስከዚህ ድረስ ምንም ድምጽ የለውም።
ለምለሙን መሬት እየቀረደደ፣ ትላልቁን ዛፍ እየገነደሰ፣ ሳር ቅጠልን እያግበሰበሰ በዝምታ ቁልቁል ይጓዛል። ሙላት እና ጉድለቱን ለመለየት ወንዙ አሸዋ እንጂ ድንጋይ ስለሌለው ያስቸግራል። ጉዞው ድምጽ አልባ ነው ዝም ብሎ እንደ እባብ መሰስ። “ኧረ ይድፋት፤ ቀላል ናት ይችንማ እሻገራታለሁ” ብሎ እንደቀልድ የሚገባን ሰው አሳስቆ ይበላል። ብር ወንዝ በጣም በመሙላት የሚታወቅ፤ ክረምት የሚይዝ የሚጨብጥ የሌለው ጉልበተኛ ነው።
ከደጋማው ቋሪት፣ ወደ ጃቢ ጠህናን ከዚያም ወደ ደንበጫ ወረዳ ሲመጣ ከአስፓልት ወደ ሸለቆነት ይለወጣል። ብር ወንዝ ጅጋ ከተማን እንዳለፈ ጉዞው ፈጣን፣ ጠመዝማዛ፣ ኃይለኛ በፏፏቴዎች የሚታጀብ ይሆናል። የዛሬው ሟችም በዚህ የውኋ ሙላት እየተላጋ፣ ድንጋይ እና እንጨት እየተቀባበለው ከመንዝ ማዶ በሚገኘው ዝብዳም ሚካኤል ቀበሌ ነው የተገኘው። ብር ወንዝ እዚህ ላይ ክረምት ለመሻገር አይደፈርም። ወዲህ እና ወዲያ ማዶ ሆኖ መተያየት እንጂ። ትላልቅ ቋጥኝ እና ድንጋይን ስለሚያልፍ ብዙ ፏፏቴዎችን ፈጥሯል። በፏፏቴው ድምጽ ሙላት እና ጉድለቱ ይታወቃል። ብር ወንዝ በሐምሌ አደገኛም ጉልበተኛ ነው። የክረምቱ አንዱ ትዝታዬ ይህ ነው። ወደ ኋላ ደግሞ ተመልሼ የክረምት ትዝታዬን ላስቃኛችሁ።
የ4ኛ ክፍል ተማሪ ነበርሁ። ጅጋ ከተማ ደንበጫ በር የሚባለው ሰፈር መስመር ዳር የቀበሌ ቤት እናቴ እና እህቶቼ ጋር ነበር ምኖረው። ምስጋን የሚባል ሚስቱ ጠላ የምትሸጥ ጎረቤታችን ጋሪ ነጂ ነበር። እነ ምስጋናን ቤት ሁለት ትላልቅ ድምጽ ማጉሊያዎች ያሉት የሚገጣጠም ትልቅ ቴፕ ነበር።
የኤፍሬም ታምሩ ዘፈኖች ውስጤ የተሰነቀሩት የዚያን ጊዜ ነው። ክረምት ነው፤ ብምም ብምም፤ ብዝዝ ብዝዝ የሚል የምስጋን ቴፕ ድምጽ ጆሮዬ ላይ ውሎ ያመሽብኛል። የክረምት ትንሽ ድምጽ ከርቀት ትሰማለች። ከርቀት የሚቆላ የጠላ እህል (ደረቆት) በነፋስ ተሳፍሮ መጥቶ የመብላት ምኞትን ይጨምራል። የመንደር ቡና ሲቆላ፤ የሩቅ ሰፈር ሰው ቆሎ ሲቆላ ሽታው ልብን ሰውሮ ጨጓራን ርሀብ ይለቅበታል። ኤፍሬም ቀኑን ሙሉ ሲዘፍን ውሎ፣ ማታውን ያመሻል። ቀን ሲጥል፣ መድኃኒቴ እና ቢልልኝ ሙዚቃዎች ዛሬም ያንን የጅጋን የሚቆላ ቡና፣ ቆሎ፣ የመንገድ ላይ ድንች ጥብስ፣ የባህር ዛፍ ቅጠል ሽታ፣ የጎረቤታችን ጠላ ቤት የሚቀመጠውን አባ አሰፋን ሲጋራ ጭስ ያስታውሰኛል። በክረምት ትንሽ ድምጽ ይጎላል። የሩቅ ሰፈር ጩኸት ቅርብ ሆኖ ይሰማል። አየር ይታፈናል።ከተማው በጭስ እና በጉም ይሸፈናል።የመኪናው ሞተር ጭስ ይጎላል።
በሀገራችን ካሉት አራት ወቅቶች ከመኸር፣ በጋ እና በልግ፤ ክረምት የምንለው ወቅት የበለጠ ያስፈራኛል። ጭቃው፣ ዝናቡ፣ ብርዱ ጭንቀት ይለቅብኛል። አያቴ ክረምቱን ክፉኛ ይፈራው ነበር። የጠሉት ይወርሳል እንዲሉ ሞቱ በ1995 ዓ.ም ነሀሴ ወር ነበር። አባቴን ክረምት ባይኖር ስል አንድ ቀን ስጠይቀው “አሳብ የለሽ ሳር ትበላ መስሎሃል” ብሎ ገሰጸኝ። ምግብ ሁሉ የሚመረተው በክረምት አይደለም ወይ እያለኝ ነው።
ነገሮች ሁልጊዜ ሲጀምሩ እና ሲያልቁ አስቂኝ ናቸው። ሲያልቅ አያምር ብንልም ሲጀመርም እንዲያው ነው። በመስከረም ትምህርት ስንጀምር እንድ ሁለት እያልን ሕዳር አካባቢ ከብትም፣ ወፍም ሲጠብቅ የከረመው ተማሪ ተሰባስቦ ትምህርቱ ወደ ሙሉ መስመሩ ይገባል። እንደገና ደግሞ ሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ ተማሪው አንድ ሁለት እያለ መበታተን ይጀምራል። ሰኔ 30 ተማሪው ሁሉ በናፍቆት ይበታተናል። አንድ ሁለት ብሎ እንደተሰባሰበ ሁሉ እንድ ሁለት እያለ ይለያያል። ተማሪውከመምህሩ፣ ከጓደኛው፣ ከሚያፈቅረው፣ ከተጣላው ሁለት ወር ተለያይቶ ይከርማል። ክረምቱ አሰልቺ ነው። የገጠር ልጅ በስራ ስለሚጠመድ ክረምቱን ይጠላዋል፤ በዓይን ፍቅር የተነደፈ ታዳጊ ከልጅቷ የመለያያው ጊዜ በመሆኑ አምርሮ ይፈራዋል። የሚዋደዱ ጓደኞች እስከሚገናኙ ድረስ በናፍቆት ይቆዝማሉ። በጠብ የተፈላለጉ ወጣቶች ቂማቸውን ለመርሳት ጊዜ ያገኛሉ ወይም ተዘጋጅተው ይመጣሉ። ክረምቱ ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25 ድረስ ያለውን ጊዜ ቢይዝም እንኳን ላፈቀረ ወጣት ሁለት ዓመት ያህል ይረዝማል። ክረምቱ በትምህርት አዕምሯቸው ተይዞ ለነበሩ ረፍት የሚሰጥ በመሆኑ የመዝናኛ ቦታ ያገኛሉ። ክረምቱን እወደዋለሁ የሚሉ ቢኖሩም የሚጠሉትም ብዙ ናቸው።
ክረምቱን የተጣሉ ባልና ሚስት እንኳን ቢኖሩ ሽማግሌ ገብቶ “ውኃ ሙላት ይጉደል፤ የቤቱ ባለቀበት፣ የውጩ ባልደረሰበት አትለያዩ፣ አብራችሁ ቆዩ” ብሎ ይሸመግላል። ኤፍሬም ታምሩ” ብርዱ እየበረታ በግንቦት በሰኔ፤ ምነው በክረምት ትርቂያለሽ ከዓይኔ” ሲል የሚገልጸው ይህንን ሐሳብ ይመስላል። ክረምት ርድ፣ ነፋስ፣ ወጀብ፣ መብረቅ፣ ዶፍ፣ ነጎድጓድ፣ ጎርፍ እና ውኋ ሙላት አይለዩትም። የፍርሀት ስሜቱን የሚፈጥርብንም ይህ ይመስለኛል። ብዙ ሙዚቃዎቻችን ይህንን ስሜት በራሳቸው መረዳት ገልጸውታል። ክረምቱ ፍርሀት ሲለቅባቸው፤በናፍቆት ቤት ውስጥ ሲቆዝሙ፤ናፍቆት እንደጭጋጉ ሲበረታባቸው ፤ፍቅር አንጀታቸው ድረስ ዘልቆ ገብቶ ሲያስጨንቃቸው እናያለን። አበበ ቀበታ “ክረምት ያልፋል” በሚለው ዘፈኑ
“አስገመገመ ክረምቱ
ሐምሌ ነሀሴ ነው ወራቱ
አልችለውም ብርዱን ጉብል ስሚኝ
ተይ ነይ እና አካርሚኝ” ይላል።
ክረምቱ ገና ሲጀማምር ውሃው ይሞላል፤ ምንጩ ያረሰርሳል፤ ጅረቱ ይጎለምሳል። ደረቁ ርጥብ ይሆናል። “የክረምት መሻገሪያህን በጋ ተመልከተው” የሚባለውም ክረምት በአንድ ጊዜ ድብልቅልቅ ስለሚል ደረቁ ላይ ቆመህ ርጥቡን ዘመን አቅድ ለማለት ነው። አበበ ቀበታ በበጋው ወራት ከልጅቱ ደጅ ድረስ ይሄድ ነበር። ሲከተላት ሲያሳድዳት ኖሯል። እንደ በጋው ወቅት ሁሉ ክረምቱን እየተከተላት ሄዶ ግባ ባትለውም ደጇ በጥገኝነት ጓሮ እያደረ ለመቀጠል አልቻለም። ከፍቅር ስሜት ጋር አንጀትን የሚሰረስር ብርድ አለበት። ሰማዩ ያረገዘውን ዝናብ እና ቅዝቃዜ አልችለውምና አብረሽኝ ኑሪ የሚለው ለዚህ ነው።
ከደሳሳ ቤቴ ከጨላለመችው
ቅዝቅዝ ካለችው
እንደምን ክረምቱን አሳልፈዋለሁ
ነይ ባንቺ እድናለሁ
የድህነት ኮሳሳ ቤት ውስጥ ናፍቆት ታክሎበት ክረምቱ ማሳለፍ ይከብዳል። ጉም እና ዝናብ ዙሪያውን አጨልሟት፤ ዝናብ እና ጠፈጠፍ ውስጧን አቀዝቅዞት አንድ ሰው ብቻውን አይችልም “ነይ ባንቺ እድናለሁ” የሚላት በዚህ ቅዝቃዜ ውስጥ ምን ያህል ሙቀት ይዛለት ብትመጣ ይሆን? እኔስ እዚህ ቤት ውስጥ እሱን ፍለጋ የምትመጣው ጉብል የበለጠ ከእሱ በላይ አሳዘነችኝ። እሱ እሷን በማግኘቱ ከሕመሙ ቢድን እሷን ግን ቅዝቃዜ የሚበላት ይመስለኛል። ማገዶውን ደርድሮ እሳት ማግዶ ቢያነድም ደሳሳ ጎጆው አትሞቅም። ያለእርሷ ምንም መፍትሔ የለውም። ሰውነቱ በብርድ እየተንቀጠቀጠ፤ጥርሱ እየተጋጨ ወደ ብቸኝነት የቅዝቃዜ ጎጆው ደጋግሞ ይጠራታል።ብርዱን ለመቋቋም አቅም እንደሌለውም በመናዘዝ ይለምናታል። እሷ ግን ልቧ የራራለት አትመስልም። “የሚያልፍ ዝናብ አይምታህ፤የሚሞት አሩግ አይርገምህ” ይባል የለ። አበበ እባክሽን ነይ ብሎ ተናግሮ ምናልባት ብትቀሪ እንተዛዘባለን ሲል እንዲህ ይላታል።
ብርዱም ያልፋል፣ክረምት ያልፋል
ነይ ብዬሽ ብትቀሪ ሆድ ትዝብት ያተርፋል
የመስፍን በቀለ ነይ በክረምት ሙዚቃ የዘጠናዎቹ ልጆች ውብ የክረምት ትዝታ ነው። እኔም በዚህ ዘመን የልጅነት ጊዜዬ ተጣጥሞ አልፏል። ገና ሙዚቃው ሲጀምር ሽው የሚለው የዝናብ ድምጽ የቅዝቃዜ ስሜትን ይለቅብኛል። ልጆች ሆነን ሐምሌ እና ነሀሴን በጭቃ በመንሸራተት፤ ብይ በመጫዎት፤ በአኩኩሉ፤ ድንቢ ለድንቢ በመባባልም ጊዜያችንን እናሳልፍ ነበር። ሌባ እና ፓሊስም እንጫዎት ነበር። በተለይ ቅዳሜ ቀን ፍኖተ ሰላም ገበያ ከሩቅም ከቅርብ በሚመጣ ገበያተኛ መውጫ እና መግቢያ የሚጠፋበት ቀን ነበር። የእናቴን ዘንቢል ይዤ ከኋላዋ እከተላለሁ። የከተማዋ መሬት እና መንገድ እልም ያለ ቀይ አፈር ጭቃ ነው። ሸርተት ካሉ ዱብ ነው።
ማራቶን ሚባል ጎማ ጫማ ፋሽን ነበር። ከጫማው በተጨማሪ ቦይ የሚል ሱሪ እና ኮት ለብሻለሁ። የከተማው ዙሪያ ሴቶች ከአባሰም ቀበሌ ያመረቱትን ሸንኮራ ይዘው በቅርጫት በቅርጫት ተሸክመው ይጓዛሉ። የአህያ ጋሪው መንገዱን ዝግት አድርጎታል። “እሄውልህ ወዲያ አትመልከት፤ እኔ ምቆምባትን እየተከተልህ ደረቅ ደረቋን እርግጥ” እናቴ አጓጓዜን እየነገረችኝ ነው። ርጥበቱ አንሸራቶ እንዳይጥለኝ እያስጠነቀቀችኝ ነው። ጤፍ መሸጫው አካባቢ ደርሰናል።በቆሎውም፣ዶሮውም፣ገብስና ሽንብራው በአንድ አካባቢ ይሸጣል። አርሶ አደሩ ከቤቱ ያመጣውን እህል ቅጠል እያነጠፈ ርጥብ መሬት ላይ አስቀምጦ ይሸጣል። ዝናብ ቢመጣም ከጥላ ውጪ ሌላ መጠጊያ የለውም። ቀደም ብዬ ያየሁት ሸንኮራ ልቤ ውስጥ ቀርቷል። “ኧሯ አይዞህ፣አይዞህ ማሙሽ” የሚል ብዙ ድምጽ ተከታተለኝ። የያዝሁት ዘንቢል ወደ ፊት ፤ለጤፍ መግዧ የያዝሁት የማዳበሪያ ከረጢት ወደ ኋላ፤ አንድ እግሬ ወደ ፊት ሌላው ወደ ኋላ ተዘበራርቆ ርጥብ ጭቃ ላይ ወድቄያለሁ። “አንድ እጄን ይዛ እያነሳችኝ እናቴ “አይ ሌሊቴ እየነገርሁህ፤እንዲያው ምን ይሻልሃል” ብላ ተቆጣችኝ። ጭቃው ጅንስ ሱሪዬን እና ኮቴን አጨማልቆብኛል። በተለይ ሱሪዬ ተበላሽቷል። ስጓዝ የሚያየኝ ሰው “ኧሯ” ይለኝና ይገረማል። አይዞህ “ክረምት ያልወደቀ ቡ’ ነው” ብሎም የሚያጽናናኝ አለ።
… ይቀጥላል!
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም